>

ከቅድም ሀያቴ መንደር አፈናቀሉኝ !!! (ሚልዮን አየለች)

ከቅድም ሀያቴ መንደር አፈናቀሉኝ !!!
ሚልዮን አየለች
ዛሬ ወደ አዳማ ለጉዳይ እየሄድኩ አንዲት በእድሜ ጥቂት ቀደም ያሉ እናት ሶስት ሆኖ ከሚይዘው ወንበር ላይ እኔና እሳቸው ተቀምጠንበት እየሄድን ነበር፡፡ ሁሉ ጊዜም የመኪና መንገድ ሲሄድ እንደ ልምድ ያደረኩት አጠገቤ ካለው ሰው ጋር ከማወራ ይልቅ ያለኝን ሰአት መፀሐፍ እያነበብኩበት እጓዛለሁ፡፡ በአጋጣሚ ከያዝኩት መፀሀፍ ያነቃኝ አብረውይ የተቀመጡት እናት ከመኪናው ረዳት ጋር ሶማሊኛ በተቀላቀለበት ኦሮሚኛ በላዩም በአማርኛም እየተጨቃጨቁ ነበር የእናትየው ሙግት ይህንን ሁሉ ለምን እክፍላለሁ አልከፍልም ነበርና እንደተለመደው የዋጋ ክርክር ብቻ መስሎኝ ወደመፀሀፌ ተመለስኩ በመሀል ግን አጠገቤ የተቀመጡት እናት ‹‹ተፈናቅለን ብንመጣም እኮ ሀገራችን ነው›› ብለው መረር ያለቃል ሲናገሩ ሙሉ ለሙሉ መፀሀፌን ማንበብ ትቼ ረዳቱንም አጠገቤ የተቀመጡት እናትንም ማረጋጋት ጀመርኩ ሁሉም የሚኒባሱ ተሳፋሪ ይህን ጊዜ ረዳቱ ላይ በመጮኽ ዋጋም ባያስቀንሱም የእናታችንን መረጋጋት መለሱ፡፡ እናታችን እያልኩ እንድጠራቸው ያስገደደኝ ከዚህ በኋላ የነገሩኝ ታሪክ እና አሁን እየደረሰባቸው ያለው ጉዳይ እንደ ወላጅ እናቴ ስላዘንኩኝ ነው፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው
የመጡት ከሰበታ ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ ነው እየሄዱ ያሉት ደግሞ እናታቸውን ሊጠይቁ ወደ አዳማ ነው ይህ ነገር እንደዚህ ሊሆን የቻለው ብለው ሲነግሩኝ፡፡ ‹‹ ከዛሬ አመጥ በፊት በተከሰተው በኦጋዴን(ሶማሌ) ክልል ውስጥ በተነሳ ግጭት ምክንያት ብሔርሽ ኦሮሞ ነውና ከዚህ መውጣት አለብሽ ተብዬ ቤተሰባችንን ሁሉ ንብረታችንን አቃጥለው እና ዘርፈው ከብቶቻችንን ነድተው አባረሩን እኛም እስከዛ ጊዜ ድረስ ሌላ ብሔር ሌላ አመለካከት ያለ አይመስለኝም ነበር እኔ ተወልጄ ያደኩት እዛው አከባቢ ነው ልጆችም ወልጄ ያሳደኩት እዛው ነው አይደለም እኔ አባቴ እና እናቴ ተወልደው ያደጉት እዛው ነው ምን ይሄ ብቻ ሀያቴም እኮ ተወልዶ ያደገው በዛው ክልል ውስጥ ነው ቋንቋውን ባህሉን ኑሮውን እናውቀዋለን ሀብት፤ዘመድ፤ወዳጅ አፍርተንበታል ወደዚህች ከተማ ከዘራችን ቀድሞ የመጡት ቅድመ ሀያታችን ናቸው በወቅቱ ታሪኩን እንደነገሩን ሚኒሊክ ሀገር እያቀና በነበረበት ጊዜ ብዙ ወታደሮች በየቦታው ተበትነው ሀገሪቷ ስትሰፋ የሰፈሩ ናቸው አሁን እንደሚሉት ቅድም ሀያቴ ከሸዋ የመጡ የአማራ ተወላጅ ናቸው እኔ ስለ ዘር ማውራት አሁን ነው ያየሁት እኛ ማን ማን ነሽ ተባብለን አናውቅም ሀያቴ እዚሁ ነው አግብቶ ትዳር የያዘው አባቴም እንደዚሁ ታዲያ እኔ እንዴት ሀገርሽ አይደለም ተብዬ እሰደዳለሁ›› ውስጣቸው የነበረውን ቁጭት እና ብሶት ከመጻፍ በላይ ነው እልህ ሀገር ማጣት ከረጂነት ወደ ተረጂነት መሸጋገር ብዙ ብዙ ይሄ አይነት ብዞት ይዘው ከታክሲው እረዳት ጋር ባይጨቃጨቁ ይገርመኝ ነበር፡፡
ከሚኒባሱ ከወረድን በኋላ ውስጤም ይህቺ ሀገር ማረፊያዋ የት ነው እንዴት ቅድም ሀያት እና ሀያት ተቆሮ ዘር እንማዘዛለን የተዋሃደ የተጋመደ ማህበረሰብ ገመዱን ምፍታት ጠነኝነት ነው ወይ?  ጥያቄ ብቻ፡፡
Filed in: Amharic