>
5:13 pm - Sunday April 18, 8849

የኢንጂነሩ ሞት፦ ግድያ - ክስተት - አደጋ - እራስ ማጥፋት - ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምን አሉ? (ለናኦሜ እና ለኒኪታ)

የኢንጂነሩ ሞት፦ ግድያ – ክስተት – አደጋ – እራስ ማጥፋት – ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምን አሉ?
ማስታወሻ – memori
ለናኦሜ እና ለኒኪታ
(ነሐሴ 21 ቀን 2010)
አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ በፓርላማው ከተሾመ አምስት ወራት ሊሞሉት ሦስት ቀናት ብቻ ይቀሩታል፡፡ በስልኬ ላይ በጫንኳቸው ከአንድም ሦስት አፖች መሠረት እናንተም የተፀነሳችሁት እርሱ መጋቢት 24 ቀን 2010 ሥልጣኑን ከመረከቡ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ ነው፤ ሆኖም የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሲደረግ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱ የማይቀር እንደሆነ ታውቆ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለሀገሩ ወፍራም ተስፋ በልቡ ያሳደረበት ሳምንት ነበር፡፡
ውድ ልጆቼ፣ ወደፊት ስለሀገራቹ ስትጠይቁ ከአብይ ጎን ለጎን የምትሰሟቸው አያሌ ስሞች እና ግለሰቦች አሉ፡፡ በዚች አምስት ወራት ውስጥ የተፈጠሩት ክስተቶች እና ድርጊቶች አሸን ናቸው፤ እንደ አግባቡ ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር እያገናኘሁ ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡ ለዛሬ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትላንት በስቲያ ከጋዜጠኞች ለቀረቡለት ጥያቄዎች ያስገረመኝን አንድ ምላሽ ላጫውታችሁ፡፡
እንጂነር ስመኘው በቀለ የተባሉ ሰው ነበሩ፡፡ እኚህ ሰው ምናልባትም በእናንተ ዘመን ግንባታው ተጠናቆ ያልተቆራረጠ ብርሃን የምታጣጥሙበትን ታላቁን የኅዳሴ ግድብ በሥራ አስኪያጅነት ከጅማሮው አንስቶ ይመሩ ነበር፡፡ መስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ሐምሌ 19 ቀን 2010 ሞተው ተገኙ፡፡
ያን ዕለት እኔ ጠበቃ፣ አቃቤ ሕግ፣ ጋዜጠኛና ሌላም ሌላም ከሆኑ ጓደኞቼ ጋር በጉዳዩ ስንነታረክ ቆየን፤ እራሱን ገደለ፣ ለውጡን የማይፈልጉት ገደሉት እና አብይ አስገደለው የሚሉት መከራከሪያዎቻችን ነበሩ፡፡ በኋላ ግን ፖሊስ ግራ ጆሮ-ግንዳቸው ላይ በጥይት ተመትተው መሞታቸውንና ሽጉጥ በቀኝ እጃቸው አካባቢ መገኘቱን ሲነግረን እራሳቸውን ገደሉ የሚለውን መከራከሪያ ለጊዜው ውድቅ አደረግነው – ጆሮ-ግንድ፣ ለዚያውም የግራ በሚል፡፡
ይህ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አየር ላይ ነበር፤ ወደ አሜሪካ እየሄደ፡፡ እርሱ መሬት ሳይወርድ ወሬው እና መላ-ምቱ ጦፍዋል፦ አብይ የዛን ሰሞን አንድ ስብሰባ ላይ «ግድቡ በአስር ዓመትም አያልቅም» ማለቱን አስመልክቶ ኢንጂነሩ የዚያን ቀን መግላጫ ሊሰጡ ነበር፤ ስለተመዘበረ ገንዘብ እና ስለመዝባሪዎቹ መረጃ ይፋ ሊያደርጉ ነበር፤ ሌላም ሌላም ተባለ፡፡ በሰዓታት ውስጥ አዲስ አበባ፣ ጎንደር እና ሌሎች ከተሞች ላይም ሰልፎች ተደረጉ፦ ፍትህ ለኢንጂነር ስመኘው ተባለ፤ ‘የቀን ጅቦች’ ይታሰሩ፣ ይሰቀሉ ተፎከረ፤ አብይ ደመላሻችን ተዘመረ፡፡ ሁሉም ሚዲያ፣ በተለይ የመንግስት የሆኑትና ንክኪ ያላቸው ክስተቱ ግድያ ብቻ ሳይሆን ገዳዮቹም በስም የሚታወቁ እስኪመስል ድረስ ለቀናት በኢንስትሩመንታል ሙዚቃ አጅበው ሰበኩን፡፡ ውድ ልጆቼ፣ እንደኔ ዓይነት ኢሕአዴግ አልቆለታል ብሎ ለውጡን የደገፈ ሰው አንዳንዴ ተስፋ ሲቆርጥ የነበረው በእነዚህ ሚዲያዎች ሁናቴ ነበር – ኢሕአዴግ ከነ ጆሮ-ሰርሳሪ ፕሮፓጋንዳው ቁልጭ ብሎ መኖሩ ሲታየን፡፡
ታዲያ አብይ አሜሪካ ገብቶ ምን አለ? ሀዘኑን ገለፀ፤ ግን በዚያ ቢበቃ ጥሩ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በአደባባይ ሰው እንደሚገደል፣ ገዳዮቹ ኢንጂነሩን መግደል/ማቆም ይችሉ እንደሆን እንጂ ግድቡን በጭራሽ ማቆም እንደማይችሉ ተናገረ፡፡ እንግዲህ ጉዳዩ ገና ምርመራ ላይ ነው፤ አብይ ምን አስቸኮለው? ኡጋንዳ የሚኖር ወዳጄን ጠየኩት፡፡ የለውጡ ደጋፊ ነው ወዳጄ፣ ሆኖም እንዲህ አለኝ «አብይ ዋና consumer እኮ ነው፤ he is capable of consuming every occurrence.»
እውነቱን ነው፤ እንዲህ ዓይነት ንግግር ያደረገው ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ ሰኔ 16 ቀን 2010 መስቀል አደባባይ ለእርሱ እና ለለውጡ በተደርገ ሰልፍ ላይ የእጅ ቦንብ ተወርውሮ ሲፈነዳ፣ በደቂቃዎች ውስጥ በቀጥታ ቴሌቪዥን መግላጫ ሰጠ፡፡ ተገቢ ነበር፤ የእርሱን ደህንነት ሕዝቡ በፍጥነት ማወቅ ነበረበት፡፡ ሆኖም ሌሎች ቅድመ-እውነታዎችን አከለበት፦ ድርጊቱን የፈፀሙት እውቀታቸውን እና ሙያቸውን ተጠቅመው እንደሆነ በመናገሩ ለውጡን ገሸሸ አደረጉ በተባሉትና ከለውጡ በፊት የመንግስትን መዋቅር በተለይ የፀጥታ እና የወታደራዊ ክፍሉን ሲቆጣጠሩ በነበሩት የህወሓት ሰዎች ላይ ሕዝቡ ጥርጣሬውን አጠናክሮ እንዲቀጥል መንገድ ከፈተ፡፡ እሱ ብቻ አይደለም፤ በድርጊቱ የተወሰኑ ሰዎች መሞታቸውንም በደቂቃዎች ውስጥ የነገረን አብይ ነው፡፡ ሆኖም በቦምብ ፍንዳታው የተጎዳ የመጀመሪያው ወጣት ህይወቱ ያለፈችው ከድርጊቱ ከሰዓታት በኋላ ነበር፡፡ ሁለተኛውን ሞት የሰማነው በነጋታው ነው፡፡ ማለትም አብይ መግለጫ ሲሰጥ የሞተ ሰው አልነበረም። ስለሟች ቁጥር አብይን ተሳስተው ያሳሳቱት ሰዎች ይኖሩ ይሆናል፤ በዚያ ፍጥነት የገዳዮቹን ፕሮፋይል ለመተንተን መብቃቱ ግን ችኩልነት ብቻ ሳይሆን ዋነኛ ኮንሲዩመርነቱ ነበር፡፡
ውድ ናኦሜ እና ኒኪታ፣ ሰኔ 16 ሁለት ኢትዮጵያዊያን ህይወታቸው አልፏል፤ ብዙዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ አሳዛኝ ቀን ነበር፡፡ ከለውጡ በፊትም ሆነ በኋላ ብዙ ሰው ሞቶብናል፤ አሳፋሪ ክስተቶችንም ታዝበናል፤ በሌላ ጊዜ እንመለስባቸው ይሆናል፡፡
እንግዲህ አብይ ምርመራቸው በፖሊስ እጅ ባሉ ሁለት ክስተቶች ላይ ያደረገውን ንግግር አንብባችኋል፡፡ ከትናንት በስቲያ ስለምርመራዎቹ ውጤት መዘግየት ሲጠየቅ የመለሰውን ስታነቡ ግር ይላችኋል፡፡ የኢንጂነር ስመኘው እና የሰኔ 16ቱ ጉዳይ አሳዛኝ እንደሆነ ገልፆ፣ አብይ ይህንን አለ፦
«እንደዚህ ዓይነት ነገር ቀድሞ ሳይጣራ ለሕዝቡ ማሳወቅ የሚኖረውን አደጋ ያው ታውቁታላችሁ፡፡ አንደኛ በሙያ የተደገፈ መሆን አለበት፤ ሁለተኛ እውነተኛ መሆን አለበት፡፡ በየጊዜው የሚቀያየር ኢንፎርሜሽን መሆን የለበትም፡፡ በዚህ ምክንያት የሙያው ውጤት እስኪገኝ መታገሱ ስለሚሻል ነው . . . እንደዚህ ዓይነት ጉዳይ ለባለሙያው መተው ጥሩ ስለሆነ፡፡»
በአንድ በኩል ገና ምርመራ ላይ ስላለ ጉዳይ ይሄኛው ምላሹ አግባብ ያለው ስለሆነ አብይ እየበሰለ እየመጣ ነው ማለት ያስችለን ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል የኢንጂነሩን ሞት በወቅቱ በይፋና በሚሊዮኖች ሕዝብ ፊት ‘ግድያ’ ብሎት፣ በሳምንታት እድሜ ውስጥ ‘ክስተት’ እና ‘አደጋ’ በሚሉት ቃላት ብቻ ሲገልፀው ማየት ፖሊስ የደረሰባቸውን ማስረጃዎች መሠረት ያደረገ ይመስላል፡፡ ይህ ደግሞ በቀደም አንድ ሰው ሹክ ያለኝን ነገር በድጋሚ እንዳጤነው አድርጎኛል፡፡
ስለዚህ ሰው ወደፊት ብዙ የምፅፍላችሁ አለኝ፤ በአጭሩ ግን አሁን በኢትዮጵያ ለተጀመረው ለውጥ ምክንያት በሆነው ‘Oromo Protest’ ላይ ቁልፍ ሚና ነበረው፡፡ እናም የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር፣ አቶ ደብረጺዮን የኢንጂነሩን ሞት እንደ መስዕዋት መግለፃቸውን እያውራሁት ሳለ፣ «Dude…the guy killed himself» አለኝ፡፡ እንደ እኔና እንደ ጓደኞቼ ቁንፅል ትንታኔ፣ ይህ ሊሆን የመቻሉ ዕድል ጠባብ ነው፡፡ ስለዚህም መሠረቱ ምን እንደሆን ጠየኩት፣ «reliable source» ሲል መለሰልኝ፡፡ ከዚህ ሰው ማንነት አንፃር የሚለውን አለማመን ቢከብድም፤ አልተዋጠልኝም ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ሁለት ሰዓት ተኩል በፈጀው የትናንት በስቲያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ፣ የኢንጂነር ስመኘው ጉዳይ በድጋሚ ተነሳ፡፡ አንዲት ጋዜጠኛ የኢንጂነሩ ሞት እና እርሱ ከመሞታቸው አስቀድሞ ስለግድቡ መንጓተት የተናገረው ግንኙነት እንደነበራቸው ተደርጎ የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱን አስታውሳ፣ ስለሁኔታው እንዲያብራራ ጠየቀችው፡፡ እንደቀድሞው ስም አልባ ገዳይ፣ ሦስተኛ ወገን በመጥቀስ ያነሳቻቸው ሁለቱ ሁኔታዎች እንደማይገናኙ በቀላሉ ይመልሳል ብዬ ጠብቄ ነበር፡፡ ሆኖም በምላሹ ሦስተኛ ወገን አልተነሳም፤ ስለግድቡ መዘግየት አግባብ ባለው አመክኒዮ አብራርቶ፣ የተደረገው ግምገማም ሆነ በግድቡ ግንባታ ላይ የሚሳተፉ ተቋማት ኮንትራትን የማቋረጥ ውሳኔ ለኢንጂነር ስመኘውም ጭምር የሚያግዝ መሆኑን፣ መቶ በመቶ እሱን የሚደግፍ እርምጃ መወሰዱን ገለፀ፡፡ እንዲህም ሲል ቀጠለ፦
«ኅዳሴ ግድብን ከጎበኘሁ በኋላ ድጋሚ በአካል አልተገናኘንም፤ በዚህ ጉዳይ የግል ስሜቱን አላቅም፡፡ ከአሜሪካ ስመለስ ቤተሰቦቹ ጋር ደውዬ ነበር፤ በሀዘን ላይ ስለነበሩ እኔም በምስራቁ ጉዳይ ስለተያዝኩኝ በአካል አልተገናኘንም፤ በስልክ ካደረግነው ውይይት እና የማፅናኛ ቃላት ባለፈ እንደዚህ ዓይነት ስሜት ለመነጋገር ዕድል አላገኘሁም፡፡ ወደፊት ዕድል አግኝቼ በደምብ የሚያውቅ ሰው ሲኖር ላወያየው እሞክራለሁ፡፡ የተወሰነው ውሳኔ ግን የእርሱን ሀሳብ እና ድጋፍ ወደ ፍሬ የሚቀይር ነው፡፡»
በተለይ ይህ የተቀነፈው ንግግሩ፣ የኢንጂነሩ አሟሟት ‘ክስተት’ ወይም ‘አደጋ’ ከመሆኑ ባሻገር ሌላ ነገር እንድናስብ ያደርገናል፡፡ ማስረጃዎች ሁሉ ስመኘው እራሱን ስለማጥፋቱ የሚያስረዱ እየሆኑ መጡ እንዴ? «Dude…the guy killed himself» ያለኝ እውነት ይሆን እንዴ? ምክንያቱም አብይ ግድቡን በሚመለከት የወሰዳቸው እርምጃዎች ለኢንጂነር ስመኘው ጥቅም ሲባልም ጭምር መሆኑ ስለምን ደጋግሞ ማስረገጥ ፈላገ? ግምገማዎቹ ኢንጂነሩን ሊያስከፉትም ሆነ እራስ ወደማጥፋት ሊያስደርሱት የሚችሉ ተደርገው እንዳይታዩ ለማስረዳት የሚሞክር የሚመስለው ለምን ይሆን ታዲያ? በጉዳዩ ላይ የግል ስሜቱን አላቅም ሲል ኢንጂነሩ በአብይ ውሳኔዎች የተስማማና የተደሰተ ስለመሆኑም ጭምር አለማወቁን ይጠቁመናል፤ አጠራጣሪ ቢመስልም፡፡
ውድ ናኦሜ እና ኒኪታ፣ አሁን እያሳሰበኝ ያለው ኢንጂነር ስመኘው እራሳቸውን እንዳጠፉ ፖሊስ መግለጫ ሲሰጥ ኢቲቪ መግለጫውን ምንተፍረቱን ያስተላልፈው ይሆን፤ እነዚያ ሰልፍ የወጡት ትንታግ ወጣቶች ውጤቱን ይቀበሉት ይሆን፤ እነዚያ ቀብር ላይ ገዳዮችን በስም እየዘረዘሩ ‘ይሰቀሉልን’ ሲሉ የነበሩት ሀዘንተኞች ምን ይሉ ይሆን፤ የግድያውን ልብ አንጠልጣይ ትርክት በፌስቡክ ሲያስነብብ የነበረው ግለሰብ እና አንባቢዎቹ ምን ይሉ ይሆን፤ ገዳይ ተብሎ በዚያው ትርክት ላይ መሪ ገፀ-ባህሪይ ተደርጎ የሰነበተው የህወሓት (ወይም እንደአግባቡ የትግራይ) አክቲቪስት እንዴት እግሩን አንስቶ ይስቅ ይሆን? ከሁሉም ከሁሉም የኢንጂነሩ ሦስት ልጆች ምንኛ ልባቸው ይሰበር ይሆን?
እኔ ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ ኩም ብል እና ለእናንተም ሌላ ማስተካከያ ማስታወሻ ባስቀር ይሻለኛል፡፡ ለአሁን በዚህ አበቃሁ፡፡
Filed in: Amharic