>

ብሄርተኝነትና የመንጋነት ባህሪው!!! (ሙክታር ኡስማን)

ብሄርተኝነትና የመንጋነት ባህሪው!!!
የጅጅጋ ዩኒቨርስቲ መምህር ሙክታር ኡስማን
 
ብሄርተኝነት እንኳን ፖለቲካዊ ቁመና ሰጥተነው ይቅርና እንዲሁም #የመንጋነት ባህሪው ለአመራር አስቸጋሪ ነው።
የብሄር ፖለቲካ እንዲሁ አንድ ተራ የፖለቲካ አማራጭ ብቻ አድርጎ መመልከት ተገቢ አይደለም። ሶማሊያን ያፈረሰ፣ ርዋንዳን ያጨራረሰ፣ ጀርመን አይሁድንና አውሮፓን ያመሰበት፣ በሀገራችንም 27 አመት ሞክረነው በተግባር ውጤቱን ያየነው ነው። ሰዎች ተወልደው ካደጉበት አካባቢ ተፈናቅለዋል፣ ተገድለዋል፣ ታስረዋል፣ ንብረታቸው ተዘርፏል፣ ሴቶች ተደፍረዋል፣ በአደባባይ ተቃጥለዋል፣ በገፍ እንደ ተራ እቃ ተጭነው ተራግፈዋል!!! ከዚህ በላይ ምን ማስረጃ ነው የምንፈልገው? ሰው እንደግለሰብ መብቱን በማክበር የሰው ስብስብ የሆነውን የብሄር ማንነት መብቱ የማይከበርበት አንድም ምክንያት የለም! ሰው መብቱ ሲከበር እንኳ የራሱ ተምሳሌት የሆነውን ሰው ቀርቶ ስለእንስሳትና ህፅዋት ስለ አከባቢና ህዋ ጨምሮ ተከራክሮ ተሟግቶ የህግ ጥበቃ የሚያሰጥ ፍጡር ነው። ከፖለቲካ በፊት ሰው መሆን ይቀድማል። ሰው ግዝፈትና ረቂቅነቱን በመጠቀም በምናበ ሰፊነቱ እንኳ ለብሄር አባላቱ ቀርቶ ለሀገሩ እና ለአለም ማህበረሰብ የሚተርፍ ነው።
አንድ ፅንሰሀሳብ በተግባር ተሞክሮ ከተፈተሸ በሃላ ወደ እውቀት ደረጃ አድጎ አጠቃላይ ግንዛቤ ይወሰድበታል። ብሄርተኝነት በእኩልነትና በዴሞክራሲ ለመምራት መሰረተሀሳቡ በራሱ ከባድ ያደርገዋል። ሰው መሆንን፣ በጋራ በአንድ የመብት መደላደል ላይ የሚያቆመንን ኢትዮጵያዊነት ይነጥቀናል። ሌሎች ሀገሮች በብሄር ተደራጅቶ ፖለቲካን መከናወን በህግ የሚከለክሉት ወደው አይደለም።
ብሄርተኝነት እንኳ በፖለቲካ ተቋማዊ ቁመና ሰጥተነው ይቅርና እንዲሁ የመንጋነት ባህሪው ለአመራር የሚያስቸግር ነው። የሰው ልጅ እድገት ከሀገር ዜግነት ወደ አለማቀፍ ዜግነት እየተቀየረ ህዋን ሲያስስ እኛ ዘመናዊው አለም ጥንት ትቶት ያለፈውን ሃላቀር በጎጥና መደርተኝነት ተሰባስቦ ፖለቲካን መተግበር መመለሳችን የሚያሳፍር ነው።
Filed in: Amharic