>

ከኢትዮጵያዊያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) የተሰጠ መግለጫ!!!

ከኢትዮጵያዊያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) የተሰጠ መግለጫ!!!
 
* በሐገራችን ሕዝባዊ መንግስትን እውን የማድረግ ከባድ ኃላፊነት በአገዛዙ የውስጥ ሽኩቻ ላይ ብቻ እንዲወሰን መፍቀድ ትልቅ ሀገራዊና ታሪካዊ ስህተት ነው!!!
የኢትዮጵያ ህዝብ  ለሃያ ሰባት አመታት በተለይም ላለፉት ሶስት ዓመታት የግፍና የጭቆና ዘመን አክትሞ በሃገራችን ነፃነትና እኩልነት እንዲሰፍን በፅናት ታግሏል። በትግሉም ወቅት ለነፃነትና ለእኩልነት የሚያስፈልገውን የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ግፍና ጭቆናን እንደማይሸከም በደሙ አረጋግጧል። ይህ ከባድ ዋጋ ከተከፈለ በኋላ  የህሊና እስረኞች ተፈተዋል፣ ተቋማዊ ባይሆንም አንፃራዊ ሃሳብን የመግለፅ የነፃነነት ድባብ ሰፍኗል፡፡ ይሁን እንጅ የሀገራችን ቁልፍ ችግሮች እንዴት እንደሚፈቱ ግልፅ የመፍትሄ አቅጣጫ ሳያስቀምጥ ኢህአዴግ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ በሚፈልጉና አገዛዙ “በተለመደው መንገድ ይቀጥል” በሚሉ ኃይሎች መካከል ከባድ ሽኩቻ ውስጥ እንደገባ አዲስ ጠቅላይ ምንስትር ሰይሞ እያዘገመም ቢሆን በተዳከመ ቁመና በስልጣን ለመቀጠል የወሰነ ይመስላል። ይሁን እንጅ የሃገራችን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግሮች ለዘመናት የተከማቹ በመሆናቸው እንኩዋን ለተዳከመና በህዝብ ለተጠላው ኢህአዴግ ይቅርና ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ብንተባበርም  ለአጣዳፊ ችግሮቻችን መልስ ለመስጠት ብዙ ብልኃትና ትግስት ያስፈልገናል።
ችግሮቻችንን ለመፍታት በህዝብ ፈቃድ ከሚፀድቅ ህገመንግስት ጀምሮ ነፃ የዳኝነት አካል፣ ከመንግስት ተፅዕኖ የተላቀቀ መገናኛ ብዙሀን፣ ነጻ የሙያና የሲቪክ ማህበራት፣ ገለልተኛ የምርጫ አስፈፃሚ አካልና ሌሎችን ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን ቁልፍ የሆኑ ተቋማትን እስከመገንባት ይደርሳል። በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን መፃኢ እድላቸንን በተባበረና በተቀናጀ መልኩ ለመወሰን ለዘመናት የተሰሩ የፖለቲካ ወንጀሎችን ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ለመስጠት የእርቅና የሽግግር ጊዜ ፍትህ ማስፈፀሚያ ስልት መቀየስ ይኖርብናል። ከላይ የዘረዘርናቸው ሥራወች ኢትዮጵያን ከአገዛዝዝ ወደ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ቁልፍ ተግባራት ናቸው ብለን እናምናለን። ነገር ግን ኢህአዴግ ሁሉንም የሀገራችን ችግሮች እራሱ በመሰለው መንገድ መፍትሄ ለመስጠት የሚያደርገው ሙከራ ሃገራችን የምትገኝበትን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ስለሆነ ወቅቱ የሚጠይቀውን ዘላቂ መፍትሄ ያመጣል ብለን አናምንም።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ህዝብ በመራራ መስእዋትነት የደረሰበትን የለውጥ ተስፋ በዘላቂነት የተጨበጠ ለማድረግ የዚህ ተስፋ ጭላንጭል ባለቤት የሆነው ህዝብ በተለይም የኢትዮጵያ ወጣት እጣ ፈንታውን ራሱ ከመወሰን ይልቅ በኢህአዴግ የውስጥ ሽኩቻ አሸናፊ ሆኖ በሚወጣው ቡድን በኩል ብቻ የሚፈለገው ለውጥ ይሳካል ብሎ መጠበቅ ትልቅ ሀገራዊና ታሪካዊ ስህተት ነው ብለን እናምናለን። ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረውን የነፃነትና የእኩልነት ትግል መነሻውና መድረሻው በግልፅ በታወቀ አጀንዳ ትግሉን አጠናክሮ በመቀጠል ኃላፊነቱን በራሱ እንዲወጣና መፃኢ ዕድሉን እንዲወስን ጥሪያችንን እያስተላለፍን ድርጅታችን ኢሃን የህዝብ ጥያቄ በሕዝብ በተመረጠ መንግስት እውን እስኪሆን ድረስ ትግሉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
ጳጉሜ 01 ቀን 2010 ዓ. ም
አዲስ አበባ
Filed in: Amharic