>

የአገር ባለውለታ የቀድሞው ሰራዊት አስታዋሻችን ክብር ይገባሀል!!! (ሻምበል እዮብ አባተ)

የአገር ባለውለታ የቀድሞው ሰራዊት አስታዋሻችን ክብር ይገባሀል!!! ሻምበል እዮብ አባተ
ነሐሴ 27 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ‹‹ሚሊኒየም›› አዳራሽ፤  በታዋቂው ኢትዮጵያዊ የኪነ-ጥበብ ሰው፣ የኢትዮጵያውያን መብትና የኢትዮጵያዊነት ልዕልና ተሟጋች ታማኝ በየነ የአቀባበል ሥነ-ሥርዓት ላይ፤ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት የአክብሮት ስጦታቸውን ከማበርከታቸው በፊት፤ በወኪላቸው በሻለቃ ሽፈራው ወንድማገኝ አማካይነት ያሰሙት ንግግር ሙሉ ቃል፡-
 ‹‹በየደረስክበት ሁሉ የተበደለው የኢትዮጵያ ሕዝብና የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት ድምፅ ሆነህ ለመብታችንና ለክብራችን ቆመህ በፅናት የተከራከርከው፣ህመማችንን የታመምከው፣ ኃዘናችንን የተካፈልከው፣ ቁስላችን የተሰማህና ሸክማችንን የተሸከምከው፤ በተራብንና በተጠማንበት፣ አስተዋሽ ወገን አጥተን ልባችን በተሰበረበት ወቅት ከጎናችን ለነበርከውና ዛሬም ያለኸው የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ! … የተከበርከው ወንድማችን ታማኝ በየነ! ክቡራንና ክቡራት ዕንግዶች!
 ‹‹… በቅድሚያ ከ22 ዓመታት የስደት ኑሮ በኋላ … ኃያሉ እግዚአብሔር! እንኳን እጅግ ለምትወዳት እናት ሃገርህ ምድር አበቃህ! እንኳንም በደህና መጣህ! … በማለት፤ በየትኛውም የኢትዮጵያ ማዕዘን የምንገኝ የ ቀድሞ ሠራዊት አባላት የተሰማንን ልባዊ ደስታ ልንገልጽልህ እንወዳለን፡፡
 ‹‹ማንም ባለሰበውና ባልጠበቀው ጊዜና ሥፍራ፤ በአሜሪካ ግዛት በዋሽንግተን ዲሲ መዲና በተዘጋጀው መድረክ ላይ፤ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት እንደ ውለታ-ቢስ ተቆጥረው ተበትነው መቅረታቸው እንደ እግር እሳት በሚለበልባቸው በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው እና በጣም በምናከብራቸው በተወዳጁ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዐብይ አሕመድ ፊት ሆነህ ‹የቀድሞን የኢትዮጵያ ሠራዊት ይቅርታ ልንጠይቅ ይገባል!!› በማለት በድምፅህ ድምፃችንን በማሰማትህ!… የተረሣውን ስማችንን በማንሳትህ፣ በወቅቱ በመላው ኢትዮጵያና በዓለም ዙሪያ ተበታትነን የምንገኘውን የቀድሞ ሠራዊት አባላት በሙሉ፤ የተሰማንና በዕንባ የታጀበ፣ በሲቃ የተመላ የደስታ ስሜት በዚህ መድረክ ለመግለጽ ይከብደናል፡፡
 ‹‹በዛሬው ዕለት በአጭሩ የተሰማንን የደስታ ስሜት ለማንፀባረቅ ከመፈለግ ውጭ ብዙ ነገር ለማለት አንፈልግም፡፡ ታማኝ!!… … በተገኘህባቸው መድረኮች ሁሉ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ መብት ተሟጋችና የኢትዮጵያ የቀድሞ ሠራዊት ተቆርቋሪ ሆነህ ለፈፀምከው ወደር የሌለው ተግባር ማስታወሻ ይሆን ዘንድ፤ የቀድሞ ሠራዊት አባላት አነስተኛ ስጦታ ልናበረክትልህ ከፊትህ ተገኝተናል፡፡ ታማኝ!! … … አንተ የክፉ ቀንና የክፉ ዘመን ባለውለታችን ነህ! ከልብህ አስታዋሻችን ነህ! ስለዚህም ከልባችን እንወድሃለን!!… በመሆኑም፡-
 ‹‹ ትናንት ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት፣ ለሕዝቧና ለሰንደቅ ዓላማዋ ክብር ሲሉ፤ … አቀበቱን ወጥተው ቁልቁለቱን በወረዱት፣ ተራራውን ባቋረጡት፣ በአየር ላይ በረው እንደጧፍ በነደዱት፤ የጨው ባሕር ቀዝፈው… ተዝለፍልፈው በሰጠሙት፤ … በሐሩር በተቃጠሉት፣ በቁር በተንዘፈዘፉት፤ በረሃ ለበረሃ ሽቅብ ቁልቁል ብለው … አሸዋ ለብሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው ባለፉት፤ ገደል ለገደል በተንከራተቱት፤ … ኢትዮጵያን ብለው በየጦር ሜዳው በተራቡት፣ በተጠሙትና በታረዙት፤ የአገራቸውንና የሕዝባቸውን አደራ ተቀብለው፤ ክረምት ከበጋ፣ ቀን ከሌሊት በባዘኑት፤አጥንታቸውን በከሰከሱት፣ ደማቸውን ባፈሰሱት፣ አካላቸውን አጥተው በየጥሻውና በየፈፋው በወደቁት፤ እናት አባቶቻቸው፣ ሚስት ልጆቻቸው ተበትነው!… … ማረፊያ አጥተው በየጎዳናው ጠርዝ በላስቲክ ቤት ዓመታትን ባሳለፉት፤ ውለታ መላሽ ባለማግኘት ቅስማቸው በተሰበረው፣ ኃዘን በደቆሳቸው፣ አስታዋሽ አጥተው የትም ወድቀው በቀሩት፤ ውድና መተኪያ የሌላት አንዲት ሕይወታቸውን ቤዛ አድርገው በሰጡት፤ … በተሰደዱት፣ የደረሱበት ባልታወቀው፣ አንጀታቸው አርሮ!… አቅላቸውን ስተው በየጎዳናው ወድቀው በቀሩት፤… … በሚያኮራ ጀግንነት በጦር ሜዳ በተሰዉት፣ ዛሬ በሕይወት በሌሉት እና በእግዚአብሔር ታምራት የመከራውን ዘመን ተሻግረን ይህን ጊዜ ለማየት በበቃነው በእኛ የመጨረሻዎቹ… …
 ‹‹ በቀድሞው የኢትዮጵያ የምድር ጦር ሠራዊት ስም፣ በቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሠራዊት ስም፣ በቀድሞው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ሠራዊት ስም፣ በቀድሞው የኢትዮጵያ ፖሊስ ሠራዊት ስም፣ ዕድሜና የጤና ችግር ሳይገድባቸው በአዛውንት አቅማቸው ለሃገራቸው ክብር ሲሉ በወደቁት በቀድሞው የኢትዮጵያ አባት ጦር ጀግኖቻችን ስም፣ አገራቸውን ለዓመታት በነፃ ባገለገሉት በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች፤ በቀድሞው የኢትዮጵያ ሚሊሺያ ሠራዊት ጀግኖቻችን እና በአንበሶቹ በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ዘማቾች ስም፤ እንዲሁም የዘወትር ወታደራዊ ግዳጃቸውን በመፈፀም ላይ እንዳሉ በምርኮ ተይዘው በመማቀቅ ላይ በሚገኙ ወንድሞቻችን ስም!…. የተዘጋጀውን ሽልማት ስናበረክትልህ፤ ወደር የሌለው ደስታ ይሰማናል፡፡
 ‹‹ በየትኛውም መድረክ እኛን የቀድሞ ሠራዊት አባላትን እንዳስታወስከን ሁሉ፤ እግዚአብሔር አንተንና ቤተሰብህን ያስተውስ! የኢትዮጵያ አምላክ ውለታህን ይክፈልህ!….  ታ… ማ… ኝ! እንወድሃለን! በሕይወት ዘመናችን ሁሉ በጎነትህን እናስታውሳለን፡፡ ምንግዜም አንረሳህም!
 ‹‹በመጨረሻም በቀድሞው ሠራዊት ሁሉም ኃይሎች ስም፤ የተዘጋጀውን አነስተኛ ስጦታ … የቀድሞው አለቃችንና የጦር ሜዳው ጀግና ሜጄር ጄነራል መርዳሣ ሌሊሣ … እኛን በመወከል ለኢትዮጵያዊው ፈርጥ ለአርቲስት ታማኝ በየነ እንዲሰጡልን በታላቅ አክብሮት እና በትኀትና እጠይቃለሁ፡፡
‹‹ ጥንታዊቷና ገናናዋ ኢትዮጵያ፤ ዛሬም ሆነ ወደፊት በጀግኖች ልጆቿ መስዋዕትነት ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች!!!  ኃያሉ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!!!››
  / አጭር ማስታወሻ፡- የጽሁፉን ረቂቅ ያዘጋጁት  ሻምበል እዮብ አባተ እንዳለ ናቸው። ነሐሴ 27 ቀን 2010 ዓ.ም ጄነራል ካሣዬ ጨመዳና ሌሎች የቀድሞ ሠራዊት ባልደረቦች በታማኝ የአቀባበል ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሚሊኒየም አዳራሽ ተገኝተዋል፡፡/ 
ምንጭ:- ሰለሞን ለማ ገመቹ
Filed in: Amharic