>
5:13 pm - Friday April 19, 4419

ድሉ እንዴት ተገኜ? ጃዋር መሐመድ ያልገባው ነገር!!! (መሀመድ አሊ መሀመድ)

ድሉ እንዴት ተገኜ?
ጃዋር መሐመድ ያልገባው ነገር!!!
መሀመድ አሊ መሀመድ
አሁን (በአንፃራዊነት) ድል ተገኘ ከተባለ አስኳሉ ምንድነው? የድሉ አስኳል የዶ/ር አብይ አህመድ በኢህአዴግ ሊቀመንበርነትና; ቀጥሎም በጠቅላይ ሚኒስትርነት መመረጥ ነው። ለዚህ ደግሞ ቁልፍ ድርሻ የነበረው የብአዴን ሁለንተናዊ ድጋፍ; በተለይም ክቡር አቶ ደመቀ መኮነን በመጨረሻው ሠዓት የወሰዱት አቋም/እርምጃ ነው? ይህ መናበብና መደጋገፍ እንዴት ሊፈጠር ቻለ?
ለዚህ ቅድሚያ ባለውለታነቱን (credituን) መውሰድ ያለባቸው ለማ መገርሳና ገዱ አንዳርጋቸው መሆን አለባቸው። በተለይ ክቡር አቶ ለማ መገርሳ ቀደም ሲል ለብዙ አሥርተ ዓመታት የተቀነቀነውንና የትም ሊያደርስ ያልቻለውን የተበዳይነት ትርክት በመቀየር ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን ማቀንቀን መጀመራቸው የትግሉን እመርታ ከፍ አድርጎታል። በዚያም ሳይወሰኑ አባይን ተሻግረው ባህርዳር ላይ ከገዱ ጋር የአንድነት ቃል ኪዳን ማሰራቸው ወሳኝ እርምጃ ነበር። የውስጥ አርበኛው ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም ወደሳቸው የተለጋችውን ኳስ ተቀብለው ጨዋታውን ለግብ አብቅተውታል። ከነሱ ጀርባ ዶ/ር አብይና ክቡር አቶ ደመቀ በጨዋታው ውስጥ ቁልፍ ሚና እንደነበራቸው መገመት አያስቸግርም።
ይህ ባይሆን ኖሮ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆኖ ሊመረጥ የሚችለው ማን ነበር? አሁን የተፈጠረው ሁኔታስ የመፈጠር ዕድሉ ምን ያህል ነበር? የ”ቄሮ”ና የ”ፋኖ” እንቅስቃሴስ ግቡ ምን ይሆን ነበር? ያ ባይሆን ኖሮ የኢትዮጵያን ህዝብ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ (ዲያሰፖራውን ጨምሮ) ማንቀሳቀስ ይቻል ነበር ወይ? ይህን ታኣምር የፈጠረው ምንድነው? ሌላ ምንም ሳይሆን እነዶ/ር አብይ ያቀነቀኑት ኢትዮጵያዊነት ነው። እናም አሸናፊው ኢትዮጵያዊነት ነው።
ይሁንና በዚህ ውስጥ “ቄሮ”ና “ፋኖ” የነበራቸውን ሚና ማሳነስ አይቻልም። ትግሉ ብዙ መስዋዕትነትና ዋጋ እንደተከፈለበት ግልፅ ነው። ማሰሪያውና ለግብ ያበቃው ግን ኢትዮጵያዊነት ነው። እዚህ ላይ የለማ መገርሳን “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ተኣምራዊ አገላለፅ ማስታወስ ብቻ ሳይሆን በሚገባው ደረጃ መዘከርም ተገቢ ይሆናል።
ያም ሆኖ እንደጃዋር መሐመድና ታማኝ በየነን የመሳሰሉ; ለህዝብ ጉዳይ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ታዋቂ አክቲቪስቶች በትግሉ ውስጥ የነበራቸውን የላቀ አስተዋፅኦና ብሔራዊ ጀግኖቻችን መሆናቸውን ለአፍታም አንዘነጋም።
ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!!!
Filed in: Amharic