>

የአብን ነገር፡ ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ እንዳይሆን!!! (ሲሳይ መንግስቴ)

የአብን ነገር፡ ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ እንዳይሆን!!!
ሲሳይ መንግስቴ
* “የአማራ ብሔረተኝነት ጽንፈኛና አክራሪ ሆኖ ነው መቀንቀን ያለበት” የሚለው ያልተገራ አቀራረባቸው ከሌሎች ቀደምት አክራሪ ብሔረተኛ ድርጅቶች ትምህርት አለመውሰዳቸውን ሲያመለክት በሌላ በኩል አቀራረባቸው የአማራ ህዝብ ከኢትዮጵያዊነት ስነ ልቦና ጋር ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ያላገናዘበ ነው፡፡
እስካሁኗ ስአት ድረስ አብንንና አመራሩን አስመልክቶ በአዎንታም ሆነ በአሉታ ለመጻፍ ፍላጎት አልነበረኝም፣ ምክንያቴ ደግሞ ገና በማደግ ላይ ያለ ልጅ ስለሆነ ቸኩሎ ማመስገንም ሆነ መውቀስ የእድገት ግስጋሴውን ይበልጥ ይጎዳው እንደሆነ እንጂ አይጠቅመውም ብየ ስለማምን ነው፡፡
አሁንም ቢሆን ለማሞገስ ወይም ለመውቀስ አይደለም ስለአብን ለመጻፍ ብዕሬን አንስቼ ከወረቀት ጋር ያገናኘሁት፡፡ ይልቁንም የማንቂያ ደወል ይሆነው ዘንድ አንዳንድ ነጥቦችን አንስቼ በአካሄዱ ላይ እንዲያስብበት ለማድረግ በማሰብ ነው ይህችን መጣጥፍ ለመለጠፍ የተገደድሁት፡፡
ሁሉም ሰው እንደሚገነዘበው የአማራ ህዝብ ትልቅ ህዝብ ነው፣ መሬቱም ሰፊና ለም በመሆኑ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ይታመናል፡፡ አህዛዊ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በግብርናው ዘርፍ 33 በመቶ የሀገሪቱን ምርት ይሸፍናልና፡፡
እናም እኔን ጨምሮ ማንም ጠነኛ የሆነ ሰው ይህን ታላቅ ህዝብና ክልል የሚመጥን ከአንድ በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲኖሩ ይፈለጋል፣ ቀደም ሲል ብአዴን በነበረበት ውስጣዊ ችግር ምክንያት የአማራን ህዝብ አይወክልም በማለት እንጮህ ነበር::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ብአዴንም በተወሰነ መልኩ እየተሻሻለ በመምጣቱና አብንም ተመስርቶ ወደ ስራ በመግባቱ ተስፋችን መለምለም ጀመረ፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአብን አመራሮችና አባላቱ እያሳዩት ያለው ጽንፈኛ አካሄድ ይህንን ተስፋችንን እንዳያጨልምብን እየሰጋሁ ነው፡፡
ለምን ካላችሁ በአንድ በኩል የአማራ ብሔረተኝነት ጽንፈኛና አክራሪ ሆኖ ነው መቀንቀን ያለበት የሚለው ያልተገራ አቀራረባቸው ከሌሎች ቀደምት አክራሪ ብሔረተኛ ድርጅቶች ትምህርት አለመውሰዳቸውን ሲያመለክት በሌላ በኩል አቀራረባቸው የአማራ ህዝብ ከኢትዮጵያዊነት ስነ ልቦና ጋር ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ያላገናዘበ ሆኖ ስላገኘሁት፡፡
የዚህ አይነት አቀራረብ ደግሞ በአንድ በኩል የአማራን ህዝብ በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ በጥርጣሬ አይን እንዲታይ የሚያደርጉ መግለጫዎችንና አስተያየቶችን ያካተቱ መሆናቸው ለምሳሌ የአብን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የሆነው ክርስቲያን ታደለ ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጠው መግለጫ ላይ አማራ የሰው የውሀ ልክ ነው ማለቱ::
ሌላኛው የአብን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ጋሻው መረሻ ደግሞ አማራ ኢትዮጵያን የፈጠረ በመሆኑ ኢትዮጵያ ፈጣሪዋን ልታክብር ይገባታል ማለቱ ወዘተ. የዚህ ስሜታዊ አቀራረብ ማሳያዎች ናቸው፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሌላኛው የአብን አመራሮችና አባላት ችግር ደግሞ የሰላ ትችትና የተለየ ሀሳብ ለማስተናገድ ያያ ያህል ዝግጁ ያለመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡
በዚህ ረገድ የተወሰኑ ምሳሌዎችን በማንሳት ለማስረዳት ከተፈለገ የወሎውን የግጥም አድባርና የባለቅኔው ሙሉጌታ ተስፋየ ወራሽ እንደሆነ የማምነበት መንግስቱ ዘገየ አብኖች የወሎን ህዝብ ስነ ልቦናና ህብር ያገናዘበ አካታች አቀራረብ ይኑራችሁ በማለቱ ብቻ አብንን ለማዳከም ነው በሚል የተሳሳተ አረዳድ በአብን ሰዎች ሲወገዝ ተመልክተናል፡፡
እንዲሁም የአብን አመራሮች በተፈናቃዮች ስም የሰበሰባችሁትን ገንዘብ በተለይም ሙሉቀን ተስፋው ከአሜሪካ የላከውን ብር ለተፈናቃዮች በወቅቱ አድርሱላቸው ብሎ በመሞገቱና ወሎየ በመሆኑ ብቻ በምነን መልኩ ሊታሰብ በማይችል ሁኔታ የኦነግ ተላላኪ በሚል ፍረጃ ትንታጉን ጽሀፊማ ጠንካራውን የላስታ ባላባት ብሩክ አበጋዝን አይንህን ላፈር ለማለት ሲረባረቡ ለማየት በቃን፡፡
ሰሞኑን ደግሞ የአብን ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለ ጫኔ ታማኝ በየነ አማራነትን ትተህ ስለኢትዮጵያ የምትሰብክ ከሆነ ወደ ክልላችን እንዳትመጣ የሚል መልክዕክት ማስተላለፉ በእርግጥም አብንን ፍየል ከድረሷ ቅጠል መበጠሷ የሚያስብለው ይመስለኛል፡፡ ታማኝ በየነ ላለፉት 27 አመታት በጽናት የታገለለትንና ከፍተኛ የሆነ መስዋዕትነት የከፈለለትን መርህ አሁን ላይ ድረስህ ተው ማለት በራሱ ትክክል አይሆንም፡፡
ከዛም አልፎ የእኛን ሀሳብ የማትደግፍ ከሆነ ወደ ክልላችን አትምጣ ማለት ደግሞ የከፋው ችግር ነው፣ ለመሆኑ አብኖችን ማን ይሆን አማራው ወደ ትውልድ አካባቢው እንዲመጣ ፈቃጅና ከልካይ ያደረጋቸው? ማን ትክክለኛ አማራና ለአማራ ጥቅም የቆቆ፣ ማን ደግሞ ትክክለኛ አማራ ያልሆነና አማራን የሚጎዳ ሀሳብ የያዘ ነው በማለት የመበየን ስልጣንስ ማን ሰጣቸው?
ስለሆነም የአብን አባላት በአጠቃላይና አመራሩ በተለይ ሰከን ብላችሁ አሁን ያለውን የሀገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታና የአማራን ህዝብ ስነልቦና ለመገንዘብ ብትሞክሩ ጥቅሙ ለእናንተ ብቻ ሳይሆን ለአማራ ህዝብና ክልልም ጭምር ነውና በሰከነ መልኩ ውስጣችሁን ለመፈተሸና አላስፈላጊ ስሜቶችን ለማስወገድ ሞክሩ፣ አርቲስት ይሁኔ በላይስ ሰከን በሉ አይደል ያለው፡፡
Filed in: Amharic