>
5:13 pm - Sunday April 20, 1141

ታማኝ በየነ በአማራነቱ ተደራጅቶ መታገል የማይፈልግባቸው 7 ምክንያቶች! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው) 

ታማኝ በየነ በአማራነቱ ተደራጅቶ መታገል የማይፈልግባቸው 7 ምክንያቶች!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
*  አንዲት ሀገር ወይም ማኅበረሰብ እንደ ታማኝ በየነ ዓይነት ከባድ አቅም ወይም ተሰጥኦ፣ ለቃል መታመን (commitment) ፣ ጽናት፣ ቁርጠኝነት፣ ትጋት ያለው ከያኔን የምትታደለው በሐምሳና በመቶ ዓመታት አንዴ ብቻ ቢሆን ነው እንጅ እንደልብ የሚገኙ አይደሉም፡፡
                * * *
ከያኔና ስሉጥ (Activist) ታማኝ በየነን የማያውቅ ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብየ አልገምትም፡፡ ስለዚህ ታማኝ በየነን በስም ማስተዋወቅ አይጠበቅብኝም ማለት ነው፡፡ እኔ የታማኝን ሥራዎችና እንቅስቃሴዎች የማውቃቸው በአብዛኛው በታሪክ ነው፡፡ ይሄም የሆነበት ምክንያት ታማኝ እስከ ደርግ ውድቀት ጊዜ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ምርዓየ ኩነት) በኅብረ ትርኢት፣ በተውኔት (በቴአትር) ቤትና መሰል መድረኮች ላይ እየታዩ ዕውቅና ያተረፈባቸውን ሥራዎቹን እንዳልከታተል ያኔ እኔ ያለሁት ትውልድ ሀገሬ ላይ ማለትም ጎንደር ስለነበርና እንደሚታወቀው በዚያ ዘመን ቴሌቪዥን እጅግ ውድና በሀገር ውስጥ ገበያም የማይገኝ ስለነበረ፣ በጥቂት ባለሀብቶች ቤት ካልሆነ በስተቀር ቴሌቪዥን (ምርዓየ ኩነት) በየቤቱ ስላልነበረ እኔም ከድሀ ቤተሰብ እንደመገኘቴ ቲቪ ስላልነበረን፤ በጣት የሚቆጠሩ ቴሌቪዥን ያላቸው ሰዎች በሰፈራችን ቢኖሩም ኅብረ ትርኢት የሚታይበት ሰዓቱ ምሽት 3ሰዓት ስለነበረና በዚያ ሰዓት ደግሞ ባለ ቴሌቪዥኖቹም ሆኑ ወላጆቻችን አይፈቅዱልን ስለነበረ፣ እንደ ታላላቆቻችን በቀበሌ ክበቦች፣ በመዝናኛ ሥፍራዎች፣ በቡና ቤቶች በመሳሰሉት ሥፍራዎች እንዳልከታተልም ያኔ እኔ ገና ኩታራ ስለነበርኩና ከቤተሰብም አይፈቀድልኝ ስለነበረ በተለይም ደግሞ እድገቴ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት በመሆኑ በነዚህ ምክንያቶች የታማኝን ሥራዎች ለማየትና ለመከታተል ባለመቻሌ ነበር፡፡ ይሁንና የታማኝን ዝና ግን እሰማ ነበረ፡፡
የወያኔ ሥልጣን ላይ መውጣት ካሳጣን በርካታ ነገሮች አንዱ ዓይኖቻችንን ማለት ከያኔያንን በስደት መነጠቃችን ነው፡፡ ከያኔያን ማለት እነማን መሰሏቹህ ድምፃዊ ወይም አቀንቃኝ (የዘፈን፣ የመዝሙር፣ የምህሌት…..) ፣ ተወዛዋዥ ወይም ዳንኪረኛ፣ የዘፈን መሣሪያ ተጫዋች፣ አቀናባሪ፣ ገጣሚ፣ ደራሲ፣ ጸሐፌ ተውኔት፣ ተዋናይ፣ አዘጋጅ፣ ወገኛ ወይም ወግ አዋቂ (ኮሜዲያን) ባጠቃላይ በዘልማድ ኪነጥበብ በምንለው የሥነኪን ዘርፍ የተሠማራ የኪነት ባለሞያ ሁሉ ማለት ነው፡፡
ወያኔ የኪነጥበብን አቅምና ጉልበት፣ ለሀገርና ለኅብረተሰብ ያለባትን ተፈጥሯዊ ጥሪ፣ ኃላፊነት፣ ግዴታ፣ ዓላማና ግብ ጠንቅቆ ያውቃልና ከያኔያን በዚህ የኪነጥበብ ተፈጥሯዊ ጥሪ፣ ኃላፊነት፣ ግዴታ፣ ዓላማና ግብ እየተገፉ ሥራቸውን መሥራት ከቻሉ አንባገነናዊና ኢፍትሐዊ ጥቅሙና ፍላጎቱ እንደሚጎዳበት፣ ማድረግ የፈለገውን የጥፋት ሥራና ግፍ ማድረግ የሚችልበትን ዕድል እንዳያገኝ እንደሚያደርጉት ስለሚያውቅ የሀገሪቱን ኪነት ደብዛ ለማጥፋት በርትቶ በመሥራቱና ከያኔያንን መፈናፈኛ አሳጥቶ መሥራት እንዳይችሉ በማድረጉ፣ በማሳደዱም ጥርግ ብለው ለመሰደድ ተገደዱና ተሰደዱ፡፡
ከያኔያን ማለት ለአንድ ሀገር ዓይን ማለት ናቸው፡፡ የአንድን ሀገር ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የሚያነቃቁት፣ የሚያጣፍጡት፣ የሚያዋዙት፣ የሚያንቀሳቅሱት፣ የሚያተጉትና በውጤቱም ዕድገት፣ ብልጽግና፣ ሥልጣኔ እንዲመጣ የሚያደርጉት ሌላ ማንም ሳይሆኑ ከያኔያን ናቸው፡፡ በምንም ነገር ላይ ቢሆን ከሃይማኖት ተቋም እስከ ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) ፣ ከግብርና እስከ ሳይንስ (መጣቅ) ኪነ ጥበብ ወይም ሥነ ኪን በሁሉም ዘርፍ የማትገባበት ቦታ የለም፡፡ በሁሉም መስክ ላይ ኪነት ያላትን ድርሻ፣ አስተዋጽኦ፣ ጉልበት፣ አቅምና ሚና ያህል ሌላ ምንም ነገር የለውም፡፡ አንዲትን ሀገር ያለ ኪነት (ጥበብ) እና ከያኔያን እናስብ ከተባለ የተወረረ ሀገርን በተወረረበት ቅጽበት ያለውን ዐውድ ማሰቡ የሚኖረውን ሁኔታ ይገልጽ ይሆናል ብየ አስባለሁ፡፡ ሁሉም ነገር ቀጥ፣ ፀጥ፣ ረጭ ብሎ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የማይኖርበት፣ መጥፎ ሁኔታዎችና ስሜቶች ብቻ የሚነግሡበት፡፡
አንዲት ሀገር ወይም ማኅበረሰብ እንደ ታማኝ በየነ ዓይነት ከባድ አቅም ወይም ተሰጥኦ፣ ለቃል መታመን (commitment) ፣ ጽናት፣ ቁርጠኝነት፣ ትጋት ያለው ከያኔን የምትታደለው በሐምሳና በመቶ ዓመታት አንዴ ብቻ ቢሆን ነው እንጅ እንደልብ የሚገኙ አይደሉም፡፡ በአማካኝ ስናየው ነው እንጅ በሁለትና ሦስት መቶ ዓመታትም አንዴ ላይገኝም ይችላል፡፡ በወያኔ ምክንያት እነኝህ ሁሉ ከያኔያን በመሰደዳቸውና ከተሰደዱትም የሚበዙቱ ከኪነት ውጭ ሆነው የያዙት እምቅ አቅም ባክኖ በመቅረቱ ሀገራችንና ሕዝባችን ምን ያህል እንደተጎዱ የጥበብን አቅም፣ ትሩፋትና ጸጋ የሚያውቅ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ማንም ሊረዳው አይችልም፡፡
በዓለማችን ላይ ለየት ባለ ሁኔታ ኪነትን የተጠበቡባት ከያኔያን እንዳሉ ሰምተናል ዓይተናልም፡፡ ለራስ አደላህ አትበሉኝና ለኔ ግን ታማኝ በየነ ለየት ይልብኛል፡፡ እንዲያው እንደ ምሳሌ ከኮሜዲያኑ (ከወገኞቹ ወይም ከወግ አዋቂዎቹ) ሁለት ሦስቱን ብናነሣ፦ ቻርሊ ቻፕሊንን እንውሰድ “ቻርሊ ከታማኝ ጋር ሲወዳደር ምን ይጎለዋል?” ካላቹህኝ ቻርሊ እንደታማኝ ስሉጥ (activist) ሆኖ ሞያውን በመጠቀም ሕዝቡ ካለበት አሥተዳደራዊና ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) ችግር ለመፍታት ቁርጠኛ ሆኖ አልተንቀሳቀሰም፡፡ እሱ ተዋቂ በነበረበት ዘመን በሀገሩ እንግሊዝና በኖረባት አሜሪካ ሴቶች ሙሉ የመምረጥ መመረጥ መብት አልነበራቸውም፣ ከቤት ወተው የመሥራት ሙሉ መብትም አልነበራቸውም ወዘተረፈ.
“ቢል ኮዝቢ ሾው” የሚባለውን አስቂኝ የቴሌቪዥን (የምርዓየ ኩነት) ትዕይንት ከቤተሰቡ ጋር እየተወነ ያቀርብ የነበረውን ዶ/ር (ሊ/ማ) ሄዝ ክሊፍንም የወሰድን እንደሆን “ከታማኝ ጋር ብናወዳድረው ምን ይጎለዋል?” ካላቹህ ውጤቱ አሁንም ተመሳሳይ ነው፡፡ ዶ/ር (ሊ/ማ) ሄዝ ክሊፍ እንደ ታማኝ በየነ በስሉጥነት (በአክቲቪስትነት) ደረጃ ወገኖቹ ጥቁሮች በአሜሪካ ያለባቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና የዘረኝነት ጥቃት ሰለባነት ችግሮችን ለማስወገድና የሰብአዊ መብታቸውን ለማስከበር አልተንቀሳቀሰም፡፡ ሌላው ከያኔ ደግሞ በገጸ ባሕርዩ ስም ሚስተር (አቶ) ቢን በመባል የሚታወቀው እንግሊዛዊው አትኪንሰንንም ብናይ የተለየ ነገር አናገኝም፡፡ እናም ከዚህ ከዚህ አንጻር አይቸው ነው ታማኝ ይለይብኛል ማለቴ፡፡
ኪነት በታማኝ ውስጥ ተቀምማ፣ ተከሽና፣ ተበጃጅታ፣ ተቆናጅታ፣ ተቆፋጥና፣ ተጠናቃ ነው ያደረችበት፡፡ ዕድለኛ ሆነን ሁኔታዎች ተመቻችተውለት፣ ከላይ እንደጠቀስኳቸው ባዕዳን ከያኔያን አቅሙን ይበልጥ ሊያወጣ የሚችልበት ድጋፍ ተደርጎለት ያለውን አቅም ያህል ልንጠቀምበት አልቻልንም እንጅ፡፡
የታማኝ ሚና በዘርፍ የተገደበ አይደለም፡፡ ልብ ብላቹህ አስተውላቹህ ከሆነ ሀገራችን አሁን ለደረሰችበት ፀረ ወያኔ ሕዝባዊ ትግል ዋነኛ አቀጣጣዩ ታማኝ በየነ ነው፡፡ ታማኝ መጀመሪያ ያደረገው ምን ነበረ? እግዚአብሔር በውስጡ ያስቀመጠበት መክሊቱ አላስተኛ አላስቀምጥ ቢለው፣ እረፍት ቢነሳው ሁለት ሦስት ወንድሞችን አነሣሥቶ ከነሱ ጋር በመሆን የቴሌቪዥ (የምርዓየ ኩነት) መስመር ከፈተና በአንድ ግለሰብ ጥረት ይከማቻል ተብሎ ለማሰብ የማይገመተውን የሀገራችንን የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) እና የኪነጥበብ ጉዳዮች የምስልና የድምፅ ክምችትን ከክምችቱ እያወጣ ያስኮመኩም ያዘ፡፡
በዚሁ መልኩ ጥቂት ከቆየ በኋላ የቴሌቪዥን መስመሩን “ባለቤትነቱን ሕዝብ ይውሰድና ሕዝብ ያሥተዳድረው!” ብሎ ኢሳትን የመሰለ ጣቢያ እንዲገኝ አስቻለ፡፡ የኢሳት መኖርም ለሌሎች ምሳሌ ሆኖ ሌሎች እንደ ኦ.ኤም.ኤንን የመሳሰሉ መስመሮችም እንዲፈጠሩ አስቻለ፡፡ ለሕዝባዊ ትግሉ መቀስቀስ የእነኝህ ጣቢያዎች ሚና ምን ያህል ወሳኝና የማይተካ እንደሆነ ከማንም የተሠወረ አይመስለኝም፡፡ ዋነኛ አቀጣጣዩ ታማኝ በየነ ነው ያልኩትም ለዚህ ነው፡፡
ታማኝ ለሀገሩና ለሕዝቡ እንደስሙ ታማኝ ነው፡፡ “ስምን መልአክ ያወጣዋል!” የሚለው አባባል እንደታማኝ ሠምሮ አላየሁም፡፡
የታማኝ አስተዋጽኦ ወይም በጎ ተጽዕኖ በቀጥታ ከሚሳተፍበት ዘርፍ ሥነኪን (በዘልማድ ኪነጥበብ) ዘርፍ ከተሰማሩት ወገኖች ባሻገርም በሁሉም ዘርፍ በተሠማራ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ጎልቶ የሚታይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በኪነጥበቡ ዘርፍ ግን ወያኔ ታማኝን ቀንደኛ ጠላቱ አድርጎ ስለያዘው ብዙዎቹ እየፈሩ በአደባባይ አይናገሩትም እንጅ ስኬታማ ከሆኑት የኪነጥበብ ሰዎቻችን የታማኝ ኃይልና አቅም ሳያበረታው፣ የብርሃን ነጸብራቁ ሳያበራለት፣ በጎ ተጽዕኖው ሳያነቃቃው፣ አርአያነቱ ሳያተጋው፣ ጀግንነቱ ሳያጀግነው፣ ወኔው ሳይሸንጠው አንድም ከያኔ ለስኬት የበቃ የለም፡፡
በዘመነ ደርግ የፀረ ወያኔና ሸአቢያ የጥፋት ኃይሎች ላይ በተደረገው ትግል እስከ ጄኔራል (ራስ) ደረጃ ያሉ የሠራዊቱ ከፍተኛ መኮንኖች በአሜሪካ የስለላ ተቋም ሲ.አይ.ኤ. ዶላርና የተለያዩ መደለያዎች ተደልለው እምነታቸውን በማጉደል፣ ክህደት በመፈጸም ለሸአቢያና ለወያኔ ስላደሩ የሠራዊቱ እንቅስቃሴ ሽባ ሆኖ ደርግ ድል ሊመታ ቻለና ትግሉም ሳይሳካ ቀረ እንጅ የታማኝ እልህና ቁርጠኝነት የተሞላበት ሚና ጉልህ የነበረበት ኪነጥበቡ ግን የሚጠበቅበትን ሚና በሚገባ ተወጥቶ ነበር፡፡ ታማኝ መሣሪያ ተጫዋች ሲጎድልበት አብዛኛውን የሙዚቃ (የዘፈን) መሣሪያ ስለሚጫወት በጎደለ ገብቶ እየሞላ፣ ድምፃውያን የልቡን አላደርስለት ሲሉ ጣፋጭ ለዛ ባለው ድምፁ እየገባ በመጫወት፣ አነቃቂ ሸናጭ መልእክቶችን፣ መፈክሮችን፣ ምክሮችን በግጥም ከሽኖ በማስተጋባት የኪነጥበቡ ዘርፍ ድርሻውን በሚገባ እንዲወጣ አድርጎት ነበረ፡፡
ይሄ ይሄ ሁሉ ሥራው፣ ታሪኩ፣ በጎ ተጽዕኖውና ጉልህ ሚናው የእግር እሳት የሆነበት ወያኔ እራሱ በካድሬዎቹ (በወስዋሾቹ) በሚያደርገው ፀረ ታማኝ ዘመቻ ታማኝ ሊወድቅ ስላልቻለ ወያኔ ለአማራ ሕዝብ ተቆርቋሪ አስመስሎ በአማራ ሕዝብ ስም ባደራጃቸው ቅጥረኞቹ በኩል ታማኝን ሊቀርብና ሊያሰናክለው ሞክሮ ታማኝ ሊሰማቸውና እንደነሱ ደንቁሮና ታውሮ “አማራ መገንጠል አለበት!” እያለ የወያኔን ፀረ ኢትዮጵያ ተልዕኮ ሊሸከምላቸው ስላልቻለ በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛው ላይ አንዴ “ታማኝ የአማራ ጉዳይ አይገደውም፣ አይሰማውም!” ሱሉት፡፡ ሌላ ጊዜ “ታማኝ አማራ አይደለም!” ሲሉት፡፡ ሌላ ጊዜ ኢሳት በሚያጠፋው ጥፋት ሁሉ እሱን ተጠያቂ ሲያደርጉት፡፡  ሌላ ጊዜ ታማኝ በጥፋት መስመር ያሉ ወገኖችን በፍቅር መመለስ ይቻል እንደሆን ለመሞከር ብሎ ከመስመር አለፍ በማለት ያደረጋቸውን ነገሮች ለምሳሌ ከኦነጎች ጋር ፎቶ (ምሥለ አካል) መነሣት፣ ለነሱ ዕውቅናና ክብር መስጠት የመሳሰሉትን ነገሮች ሆን ብለው አጣመው በመረዳትና የተለያየ ነገር እያሉ ስሙን ለማርከስና ለማጠልሸት፣ ከሕዝቡ ከወገኑ ለመለየት፣ ያለውን ሕዝባዊ ተቀባይነት ለማሳጣት ያደረጓቸው ጥረቶች ሁሉ አልይዝላቹህ አልሳካላቹህ ቢላቸው ለራሳቸው ያድርግላቸውና ሰሞኑን ደግሞ ታማኝን “ሞተ!” ብለው አውርተው አስወርተው አስደንግጠውን ነበረ፡፡
ወሬውን ስሰማ “በፍጹም! ሊሆን አይችልም! ታማኝ የደከመላትን የኢትዮጵያን ነጻነት ሳያይ አይሞትም!” እያልኩ ሐሰተኛውን መርዶ ሐሰት እንደሆነ እራሴን ለማሳመን ስጥርና ከራሴ ጋር ስሟገት አንድ ወዳጀ በነፍስ ደረሰልኝና ወሬው ውሸት እንደሆነ አበሰረኝ፡፡
እውነቴን ነው የምላቹህ ይሄ ወሬ እውነት ሆኖ ቢሆን ኖሮ ከእግዚአብሔር ጋራ መጣላቴ ነበረ፡፡ እውነት ነው እንደ ክርስቲያን ማንኛውንም የእግዚአብሔር ውሳኔ በጸጋ መቀበል ይኖርብኛል፡፡ ይሁንና ግን ይሄ ሐዘን ልክ ሙሴ እስራኤላውያንን ከምድረ ርስት ሳያደርሳቸው በሞዓብ ምድር ላይ በሞት ሲለያቸው ለእስራኤላውያኑ ከተሰማቸው መራራ ሐዘን ይልቅ የከበደና የመረረ ሐዘን ልቤን ሳይሠብርብኝ አይቀር እንደነበረ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ ከዚህ ይሰውረን!
ታማኝ እኮ ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከታቸዋል ከሚባሉት ፖለቲከኞች (እምነተ አሥተዳደራውያን) ፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች፣ የሃይማኖት አባቶች ወዘተረፈ ከምትሏቸው ሁሉ እጅግ በላቀ መልኩ የዜጎች መበደል፣ መገፋት፣ መጨቆን፣ መረገጥ፣ ሰብአዊ መብት መገፈፍ፣ መፈጀት የሚያስጨንቀው፣ የሚያስጮኸው፣ የሚያስለቅሰው፣ የሚያቃትተው እውነተኛ ሰው እኮ ነው፡፡  የሀገርና የወገን ፍቅር የሚያቃጥለው ሰው እኮ ነው፡፡
እስኪ ጥቀሱልኝ የዜጎች ጉዳይ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ወገኖች የታማኝን ያህል አይደለም ኢምንቱን እንኳ ማን ሲንገበገብ፣ ሲጨነቅ፣ ሲጮህ፣ ሲያለቅስ፣ ሲቃትት ዓይታቹህ ታውቃላቹህ? ጭራሽ እንዲያውም የሃይማኖት አባቶች የሚባሉትማ እኔ ምን ዓይነት ጉዶች እንደሆኑ አላውቅም እንኳንና የሀገር፣ የወገን ጉዳይ የሃይማኖታቸው ጉዳይ እንኳ ቢጠበስ የማይሸታቸው ሆነው አርፈውታል፡፡ እስኪ ፈጣሪ ለሁላችንም የታማኝን ቅናት፣ የሀገር ፍቅር ስሜት፣ ተቆርቋሪነት፣ ትጋት፣ ታማኝነት፣ ቁርጠኝነት፣ ጀግንነት ለሁላችንም ያድለን!
ወደ ታማኝ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ሳልፍ ደግሞ እንደሚታወቀው ታማኝ የአንድነት ታጋይ ነው፡፡ ታማኝ አማራ በማንነቱ መደራጀቱን ደግፎ የሚንቀሳቀስ ሰው አይደለም፡፡ አይደግፍም ማለት ግን ይቃወማል ማለት አለመሆኑን ልብ በሉልኝ፡፡ ለምን አይደገፍም? ወይም ለምን አይሳተፍም? ለሚለው ጥያቄ ታማኝ እስካሁን መልስ ሲሰጥ ባላየውም የማይደግፍበት ምክንያቶች የሚመስሉኝ የሚከተሉት ናቸው፦
1ኛ. አማራ በማንነቱ የሚደራጀው እንደሌሎቹ ዘውገኛ ድርጅቶች ጠባብ ብሔርተኛ ለመሆን ሳይሆን የአማራን ህልውና ለማጥፋት ፀረ አማራ ጥቃት ስለታወጀበትና ተፈጻሚም እየተደረገበት ስላለ ይሄንንም እየተፈጸመበት ያለውን አረመኔያዊ ጥቃት ተቃዋሚ ነን የሚሉት አካላት አንዳቸውም ቢሆኑ ሌላው ቀርቶ የዘር ማጥፋት ጥቃቱ በአማራ ላይ እየተፈጸመ መሆኑን እንኳ በማውገዝና በመቃወም አግባብነት ባለው ሁኔታና መድረክ ላይ ለመግለጥ፣ ለማስታወቅ ፈቃደኛ ሆነው ባለመገኘታቸው አማራ “ሕመሜን ሕመሙ ጉዳቴን ጉዳቱ አድርጎ የሚያስብና የሚንቀሳቀስ አካል ከሌለ ከጉዳዩ አንገብጋቢነትና አፋጣኝ መፍትሔ ፈላጊነት አኳያ ይህ አደገኛና ኢሰብአዊ ጥቃት በቂ ግንዛቤና እውቅና እንዲያገኝ፣ ጥቃቱን መቀልበስ የሚቻለው ጉዳዩን እራሴው ይዠ ለህልውናየ በታገልኩ ጊዜ ነው!” ብሎ አምኖ እንዲሁም በሕግም ቢባል በአመክንዮ አንድ ጉዳይ ከጉዳዩ ባለቤት በላይ ሊመለከተው፣ ሊገደው፣ ሊሰማው፣ ሊያስብበት፣ ሊጨነቅበት፣ ሊተጋበት፣ የኔ ሊለው የሚችል ሌላ አካል ስለሌለና “ሊኖር ይችላል!” ብሎ ሌላ አካል መጠበቅ ወይም እንዲኖር መመኘት ቂልነትና ሲበዛ የዋህነት በመሆኑ ቢሆንም አማራ ለራሱ ጉዳይ እራሱን በማንነቱ ማደራጀት ያስፈለገውና ለመደራጀትም የተገደደው ነገር ግን ወያኔ በስውር እጁ በአማራ ሕዝብ ስም እንደሌሎቹ ጠባብ ዘውገኛ ፀረ ኢትዮጵያ ድርጅቶች ሁሉ ፀረ ኢትዮጵያ የአማራ ድርጅቶችን ለአማራ ሕዝብ ተቆርቋሪ አስመስሎ በዳያስፖራው (በግዩራኑ) መሥርቶ የአማራን የህልውና ትግል ስም በማጠልሸቱ፣ ጎዳናውን በማበላሸቱ፣ የህልውና ትግል አስተሳሰብን በመመረዙ፡፡
2ኛ. ታማኝ “አማራ ላይ ለዘመናት ከውጭና ከውስጥ ሲፈጸም የኖረውንና አሁንም እየተፈጸመ ያለውን አማራን የማጥፋትን ጥቃት አማራ ብቻውን ሊወጣው አይችልም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር ሆኖ ካልሆነ በስተቀር!” ብሎ ስለሚያምን፡፡
3ኛ. የጎሳ ፖለቲካ ኢዲሞክራሲያዊና ኢሰብአዊ የሆነ ተፈጥሯዊ ባሕርይ ስላለውና በሠለጠነው ዓለም የማይሠራበት ኋላቀር አስተሳሰብ ከመሆኑ አኳያ ምንም እንኳ አማራ በአማራነቱ የሚደራጀው ሌሎች ጎሳ ተኮር ድርጅቶች እንደሚያራምዱት እንደነሱ የጠባብ ብሔርተኛ ዓላማን አንግቦ ለመታገል ባይሆንም አማራ ብሎ በማንነቱ ተደራጅቷልና ወደፊት እንዲጠፋ ለምንፈልገው የጎሳ ፖለቲካ ዕድሜ መራዘም አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል ብሎ በመፍራቱ፡፡
4ኛ. በአማራ ስም ብሔራዊ ወይም ሀገር አቀፍ አጀንዳ (ርእሰ ጉዳይ) ይዞ መንቀሳቀስ “ኢትዮጵያ የአማራ ብቻ ናት!” የሚል የተሳሳተ ግምት ያሰጣል ብሎ በመሥጋቱ፡፡
5ኛ. ታማኝ አማራ ብሎ ቢታገል በሚያደረገው ትግል ኢትዮጵያን የዘነጋና ሌሎች ኢትዮጵያውያንንም ያገለለ መስሎ የመታየት የመቆጠር ችግር ያጋጥመኛል ብሎ በማሰቡ፡፡
6ኛ. እነ ወያኔና ሌሎቹም ጎሳ ተኮር ድርጅቶች በጎሳ ተኮር ፖለቲካ ተፈጥሯዊ ችግር ምክንያት ዘረኛ ሆነው ዘራቸውን ከሌሎቹ ለይተው፣ ሌሎቹን እየበደሉ፣ እያጠቁ፣ በጥላቻ እየተመለከቱ ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሕዝባችን የሚሏቸውን ጎሳ ጎሳቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተጣጣሩ አድርገውት እንዳየነው ሁሉ አማራም በአማራነቱ ተደራጅቶ ሲታገል እነወያኔ ለየዘራቸው እንዳደረጉት የአማራ ድርጅትም ዘረኛ ሆኖ አማራን ከሌሎቹ ለይቶ ሌሎቹን በመበደልና በመጥላት ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ አማራን ተጠቃሚ ለማድረግ በማሰብ ሥልጣን ለመያዝ የሚታገል የሚመስላቸው የአማራ ትግል ያልገባቸው በርካቶች ስላሉ ታማኝ “በእነዚህ የአማራ ትግል ባልገባቸው ዘንድ ባልሆንኩት ነገር ዘረኛ ተደርጌ እቆጠርና መጥፎ ስም ይወጣልኛል፣ መሰናከያም እሆናለው!” ብሎ በመፍራቱ፡፡
7ኛ. ምንም እንኳ በሀገራችን የመንግሥታት ታሪክ ሥልጣን ይያዝ የነበረው ከንጉሥ በመወለድ በመሆኑ ለምሳሌ ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከጠቢቡ ሰሎሞን ከተወለደው ከቀዳማዊ ምኒልክ እስከ ዐፄ ኃይለሥላሴ በነበረው በሰሎሞናዊው ሥርዎ መንግሥት የነበሩት ነገሥታት ሥልጣን ከአባት ወደ ልጅ በሚወረስበት አምላካዊ ዕዝ ሥርዓት መሆኑ የፈጠረው አጋጣሚ ነገሥታቱ ከአማራ እንዲሆኑ የማድረግ አጋጣሚ የፈጠረ ቢሆንም አማራ ግን እንደ አማራ በአስተሳሰቡ እንኳን አሁን በዚህ በሠለጠነ ዘመን ከጥንት ጀምሮም ጎሳ ተኮር ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ያልሠለጠነና ጠንቀኛ አስተሳሰብ መሆኑን ጠንቅቆ ስለሚያውቅና ስለሚረዳ በዚህም ምክንያት ነገሥታቱ ምንም እንኳ በትውፊት ከአማራ የወጡ እንደሆኑ ቢታወቅም እነሱ ግን አንድም ጊዜ “አማራ ነን!” ሳይሉ፣ መንግሥታቸውም የአማራ መንግሥት መሆኑን ያወጁበት የገለጹበት አንድም አጋጣሚ ሳይኖር ጎሳ ተኮር አስተሳሰብን የዚህን ያህል ያራቁ፣ ያልተቀበሉ፣ የተዋጉ በመሆን ያቆዩልንን የላቀ የአስተሳሰብ ቅርስ አሁን ያለው አማራ ጎሳ ተኮር አስተሳሰብን ቢቀበል ቀደም ሲል የነበረውን ጎሳ ተኮር አስተሳሰብን በመናቅ፣ ባለማስተናገድ ከነበረበት የሞራልና የሠለጠነ የአስተሳሰብ ከፍታ ላለመውረድ ሲያደርገው ከኖረው ትግል መሸነፍ ነው፣ እጅ መስጠት ነው፣ መውደቅ ነው ብሎ በማመኑ፡፡ በእነኝህ 7 ምክንያቶች ይመስለኛል ታማኝ አማራ በማንነቱ መደራጀቱን ደግፎና ተቀብሎ ራሱንም አካቶ መታገል የማይፈልገው፡፡ ይሁንና ግን እነኝህ ሁሉ ችግሮች የየራሳቸው መፍትሔ እንዳላቸው መዘንጋት የለበትም፡፡
ለምሳሌ 7ኛውን ነጥብ በተመለከተ ግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ አማራ ሥልጣን ከሱ ከብሔረሰቡ አባል በሆነው በአንድ ቤተሰብ እጅ በነበረበት ዘመንና ሆን ብለው እሱን ለይተው ህልውናውን ለማጥፋት የሚታትሩ የውጭና የውስጥ የጠላት ኃይሎች ባልነበሩበት ዘመን የአማራ ሕዝብና ሥልጣኑ የነበረው የቀዳማዊ ምኒልክ ቤተሰብ እንዲያ ማሰባቸው ምንም ላይጎዳ ይችላል ትክክልም ነው፡፡ አሁን በዚህ ዘመን ግን አማራ በዚህች ሀገርና በአማራ ሕዝብ ጠላቶች ሥልጣን እንዲያጣ ተደርጎ ሥልጣን እራሳቸውን የአማራ ጠላቶች ባደረጉ ኃይሎች ከመያዙም በላይ አማራ ጨርሶ እንዲጠፋ በትጋት እየተሠራበት ባለበት ሰዓት ግን አማራ ለመጠቃት ምክንያት የሆነበትን ማንነቱን ወይም ህልውናውን ከፈጽሞ ጥፋት ለመታደግ በማንነቱ መደራጀቱ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ የግድ የሚል መሆኑን ለመረዳት ብዙ የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡
አማራ የሚታገለው በዚህች ሀገር ላይ የአማራ መንግሥት መሥርቶ እንደ ወያኔ በሌሎች ብሔረሰቦችና ጎሳዎች አናት ላይ ለመፈናጠጥ ለመፋነን አይደለም፡፡ ይሄ አስተሳሰብ የተረጋጋ፣ ሰላማዊ፣ የሚበለጽግ፣ የሚለማ፣ የሚሠለጥን የመንግሥት ሥርዓት፣ ሀገርና ማኅበረሰብ ለመፍጠርና ለመመሥረት ፈጽሞ ካለማስቻሉም በላይ በ21ኛው መቶ ክ/ዘ ሊታሰብ የሚችል በሳል፣ የሚያዋጣና የሠለጠነ አስተሳሰብ አይደለምና ነው፡፡
አማራ የሚታገለው ለሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች ነው፡፡ አንደኛው እራሱን ከታወጀበት የዘር ማጽዳትና ማጥፋት ጥቃት ወይም ከፈጽሞ ጥፋት በመታደግ ህልውናውን ለማስቀጠል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ያልሠለጠነና ጠንቀኛ አስተሳሰብ በመሆኑ በሠለጠነው የዓለማችን ክፍል የማይሠራበትን የተወገዘውን ጎሳ ተኮር ወይም የዘር ፖለቲካን ከዚህች ሀገር አጥፍቶ የሀገራችንን ፖለቲካ እንደ ምዕራባውያኑ አስተሳሰብ ላይ በመመሥረት ዜጎች እኩል ሆነው በችሎታቸው ብቻ የሚመዘኑበትን ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊ) ሥርዓትን ለመመሥረት ነው፡፡ አለቀ፡፡ አማራ ኃላፊነት እንደሚሰማው ማኅበረሰብነቱና እንደ ባለአደራነቱ ከዚህ የተለየ ዓላማና ግብ የለውም ኖሮትም አያውቅም፡፡ ከዚህ ውጭ በአማራ ስም የሚራገቡ ሐሳቦች ካሉ (በእርግጥም አሉ) እነሱ በአማራ ስም የሚራገቡ የጠላት ድምፆች መሆናቸውን ቅንጣት ልንጠራጠር አይገባም፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን እነኝህን አማራ የተደራጀባቸውን ሁለት የተቀደሱ ዓላማዎችን የሚቃወም ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው ይኖራል ብየ አላስብም፡፡ ይሄንን የተቀደሰ ዓላማ የሚጋሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይሄንን የአማራ ትግል መቀላቀል ይችላሉ፡፡
የአማራን በአማራነቱ ተደራጅቶ መታገሉን የሚቃወሙ አካላት ሊጠነቀቁ የሚገባቸው ጉዳይ ቢኖር አማራ በአማራነቱ ተደራጅቶ መታገሉን ከተቃወሙና ካወገዙ የግድ ደግሞ የሌሎች ጎሳ ተኮር የፖለቲካ አደረጃጀቶችንም መቃወም፣ ማውገዝና ማግለል የግድ የሚኖርባቸው መሆኑን ነው፡፡ የአማራን መደራጀት እየተቃወሙ ግን የሌሎችን ጎሳ ተኮር ቡድኖችን ህልውና የሚፈቅዱና የሚደግፉ፣ የሀገሪቱ ፖለቲካም በእነኝህ ጎሳ ተኮር የፖለቲካ አደረጃጀቶች እጅ እንዲገባ፣ እንዲዘወር፣ እንዲወሰን የሚፈቅዱና አብረውም የሚሠሩ ከሆነ ግን ይሄ የመጨረሻ የፖለቲካ ድንቁርና ከመሆኑም በተጨማሪ አማራን ለማጥፋት ማሴርም መሆኑን ጠንቅቀው ሊያውቁት ይገባል፡፡
በነገራችን ላይ ከላይ የዘረዘርኳቸው 7 ነጥቦች ወይም ችግሮች ታማኝን ብቻ አይደለም እጅግ አሳሳቢ የህልውና አደጋ የተጋረጠበትን አማራ በማንነቱ ተደራጅቶ የሚያደርገውን ትግል እንዳይደግፍና በትግሉም እንዳይሳተፍ ያደረጉት፡፡ ከምሁር እስከ ጨዋ ሌሎች እጅግ በርካታ አማራና ሌሎች ኢትዮጵያውያንንም ነው ከመሳተፍ ያቀቧቸው፡፡ ነገሮች እነሱ እንደሚያስቧቸው ቀላል ሆነው የሀገራችንና የአማራም ችግር እነሱ በሚመኙት መልኩ የሚፈታ የሚቀረፍ ቢሆን ምንኛ ዕድለኞች በሆን ነበር፡፡ ይሁንና ይሄ ምኞት እንኳን ለእውን ለሕልም እንኳ ይርቃል፡፡ እኔ በበኩሌ ይሆናል የሚል ተስፋ የለኝም፡፡ ይሆናል ብየ ተስፋ ማድረጉን ባልጠላሁት ነበር፡፡ ነገር ግን ሀገራችን ኢትዮጵያና አማራ ምን ዓይነት ጠላትና እነኝህ ባዕዳን የሀገራችንና የአማራ ጠላቶችም በኢትዮጵያና በአማራ ላይ ምን ዓይነት ዕኩይ፣ ጽንፈኛና ሰይጣናዊ ፍላጎትና ዓላማ እንዳላቸው አለማወቅ፣ አለመረዳት፣ አለመገንዘብም ይሆንብኛል፡፡ አንድ ነገር ተስፋ አደርጋለሁ እነ ታማኝ ዓይናቸውን ክፍት አድርገው ይከታተሉ እንጅ በሒደት ብዙ የሚገለጹላቸው ዓይን ገላጭ እውነቶች ስለሚኖሩ ታግሰን ብንጠብቃቸው መልካም ይመስለኛል፡፡ እነሱ እውነታውን በሚረዱበት ሰዓት ግን ነገሩ እንዳይረፍድበት ሥጋቴ ነው፡፡
ለጊዜው ግን ጀግናችን ታማኝ ሆይ! ክብር ይገባሀል እናከብርሀለን! ፣ አንተን ክፉ አይንካብን! ፣ የቅድስት ሀገር የእናት ኢትዮጵያ አምላክ ከመልካሙ ቀን ያድርስልን! ፣ በጀግንነትህም ያጽናህ! አሜን!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic