>

". የዜግነት ግዴታን ለመወጣት እና ግላዊ አበርክቶን ለማኖር ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል!" ም.ጠ.ሚ/ር  ደመቀ መኮንን - በታማኝ በየነ አቀባበል

“. . . የዜግነት ግዴታን ለመወጣት እና ግላዊ አበርክቶን ለማኖር ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል!”
ም.ጠ.ሚ/ር  ደመቀ መኮንን
 “ሃገሬ በምትፈልገኝ ቦታ ሁሉ በተግባር ለመገኘት ዝግጁ ነኝ!”
አርቲስት ታማኝ በየነ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከረጅም ዓመታት የውጭ ሃገር ቆይታ በኋላ ወደ እናት ሃገሩ የተመለሰውን አርቲስት ታማኝ በየነን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
አርቲስት ታማኝ ከረጅም ዓመታት የውጭ ሃገር ቆይታ በኋላ ሲመለስ . . . “ወደ ምትወዳት እናት ሃገርህ እንኳን ደህና መጣህ” ብለውታል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ፡፡
በሃገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ውሃ-ልኩን ጠብቆ ለህዝብና ለሃገር የሚተርፍ ቁም-ነገር እንደዜጋ ለማበርከት መልካም መንፈስ እና ቀና ድጋፍ መኖሩን አቶ ደመቀ አውስተዋል፡፡
ከዚህ በኋላ ስለ እናት ሃገር እና ህዝቦቿ በርቀት በመብከንከን ሳይሆን፤ የዜግነት ግዴታን ለመወጣት እና ግላዊ አበርክቶን ለማኖር ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
አርቲስት ታማኝ በበኩሉ መንግስት ያደረገለትን ደማቅ አቀባበል እጅግ እንዳስደሰተው በመግለጽ፤ በሃገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ቀጣይነቱ እንዲረጋገጥ እና ፍሬ እንዲያፈራ የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግሯል፡፡
“ሃገሬ በምትፈልገኝ ቦታ ሁሉ በተግባር ለመገኘት ዝግጁ ነኝ!” በማለት አርቲስት ታማኝ  ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ በውይይቱ ላይ አረጋግጧል፡፡
ምንጭ:- ም/ጠ/ሚ ደመቀ መኮንን ገጽ
Filed in: Amharic