>
5:13 pm - Thursday April 19, 7685

‘’ዛሬ የምንሠራው ሥራ የዛሬን ሕይወት እያንጸባረቀ ለነገው ትውልድ ፈር መቅደድ አለበት!!!” (የተከበሩ የአለም ሎሬት ሜትር አፈወርቅ ተክሌ)

‘’ዛሬ የምንሠራው ሥራ የዛሬን ሕይወት እያንጸባረቀ ለነገው ትውልድ ፈር መቅደድ አለበት!!!”
( እጅግ የተከበሩ የአለም ሎሬት ሜትር አፈወርቅ ተክሌ)
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በሰሜን ሸዋ በምትገኘው አንኮበር ላይ ጥቅምት 13 ቀን 1925 ዓ/ም ከአባታቸው አቶ ተክሌ ማሞ እና ከእናታቸው ከወይዘሮ ፈለቀች የማታወርቅ ተወለዱ።
ገና በአሥራ አምስት ዓመታቸው በ1940 ዓ/ም ለከፍተኛ ትምህርት ተመርጠው የምሕንድስና ትምህርት ለመከታተል ወደ እንግሊዝ አገር ተላኩ፡፡
እርሳቸውንና አብረዋቸው ለትምህርት የተላኩትን ተማሪዎች ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሚከተለውን በማለት ነበር ወድፕ እንግሊዝ ያሰናበቷቸው። “ተግታችሁ አጥኑ፣ ተማሩ ጠንክራችሁ መሥራት እና ሀገራችሁ ኢትዮጵያን የምትገነቡበትን ዕውቀት ይዛችሁ ተመለሱ። ስትመለሱ አዕምሯችሁ ዝግጁ የሆነ እውቀታችሁም ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚችል ጥበብን ሸምቶ እንዲመለስ ነው እንጂ አውሮፓ ውስጥ እንዴት ያሉ ረዣዥም ፎቅ ቤቶች እንዳሉ ወይም መንገዶቻቸው የቱን ያህል ስፋት እንዳላቸው እንድትነግሩን አይደለም።”
የጠላት የግፍ ወረራ እና እልቂት ያስከተለውን የሰው፣ የንብረት እና የባህል ጥፋት ገና በህጻንነት ዕድሜያቸው የተመለከቱት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ከነጻነት በኋላ ሃገራቸውን እንደገና እንዴት መገንባት እንደሚቻል ሲያወጡ እና ሲያወርዱ ከቆዩ በኋላ ዋናው እና ቀዳሚው ጉዳይ እውቀት መሸመት መሆኑን ተረዱት ፡፡
ግንዛቤያቸውን በማሳደግም በማዕድን ምሕንድስና ዘርፍ ላይ እውቀት በመጨበጥ ሃገራቸውን መጥቀም እንዳለባቸው ቢወስኑም ወላጆቻቸውና ዘመድ አዝማዶቻቸው ግን የኪነ ጥበብ ስጦታቸውን በቤታቸውና በከተማው ዙሪያ በሚስሏቸው ስዕሎች በመመልከታቸው በዚሁ ሙያ እንዲሰማሩ ይጎተጉቷቸው ነበር።
በትምህርት አቀባበላቸው በሒሣብ፣በኬሚስትሪ እና በታሪክ ትምህርቶች ጥሩ ውጤት በማምጣት ከመምህሮቻቸው ተደጋጋሚ አድናቆት ቢያገኙም የተፈጥሮ ስጦታቸው ኪነ ጥበብ እንደሆነ መምህሮቻቸው ለመገንዘብ ግን ብዙ ጊዜም አልወሰደባቸውም።
በመምህራቸው አበረታችነት በዚህ ስጦታቸው ላይ የበለጠ ለማተኮር ወስነው በለንደን ማእከላዊ የኪነ ጥበብ ትምሕርት ቤት የገቡት አፈወርቅ ከዚህ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤት በማጠናቀቅ ለከፍተኛ ጥናት በስመ ጥሩው የለንደን ዩኒቨርሲቲ የስሌድ ኪነ ጥበብ ማዕከል የመጀመሪያው አፍሪካዊ ተማሪ ሆነዋል ፡፡
በዚህ ትምህርት ቤት ቆይታቸውም በቀለም ቅብ፣ በቅርጻ ቅርጽ እና በኪነ ህንጻ ጥናቶች ላይ በመስራት ተመርቀዋል።
’ኪነ ጥበብ የሰው ልጅን መንፈስ ለማዳበር፣ ሀገራችንን ለማሳደግ፣ ለማሳወቅ እና ለሕይወታዊ ኑሮ ተስፋ ለመፍጠር የላቀ ሚና ይጫወታል’’ የሚሉት ባለታሪካችን ለጥቀውም ‘’ዛሬ የምንሠራው ሥራ የዛሬን ሕይወት እያንጸባረቀ ለነገው ትውልድ ፈር መቅደድ አለበት፡፡” በሚል ስሜት ኪን ማንኛውንም የሰው ኑሮ ረገድ የሚነካ እንደሆነ ያስረግጣሉ።
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሱ በተለያዩ ግዛቶች በመዘዋወር በአንዳንድ ቦታም እስከ ሦስት ወራት በመቀመጥ የኢትዮጵያን ታሪክ እና የብሔረሰቦቿን ባህልና ወግ ሲያጠኑ ቆይተዋል።
በ1946 ዓ/ም በሀያ ሁለት ዓመታቸው የተለያዩ የስነ ጥበብ ሥራቸውን የሚያሳይ የመጀመሪያውን ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አቅርበዋል።
ከትርዒቱ ባገኙት ገቢ በድጋሚ ወደ አውሮፓ በመሄድ ለሁለት ዓመት በጣሊያን፣ በፈረንሳይ፣ በስፔን፣ በፖርቱጋል፣ በእንግሊዝና ግሪክ ጥልቅ የኪነ ጥበብ ጥናት አከናውነዋል።
በጦርነትና በሌሎች ምክኒያቶች ተዘርፈው በነዚህ ሃገራት የሚገኙትን የኢትዮጵያ ጥንታዊ የሃይማኖትና የታሪክ የብራና መጻሕፍትን በጥልቅ አጥንተውና የመስታወት ላይ ስዕል ( የሞዛይክ አሠራር ጥበብን ) ቀስመው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ወደ ሃገራቸው እንደተመለሱ ንጉሠ ነገሥቱ አዲስ አበባ በሚገኘው የመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ግድግዳ፣ ጣሪያና መስኮቶችን በሃይማኖታዊ ምስሎች በቀለምና በመስታወት ስዕሎች እንዲያስውቡት ባዘዟቸው መሰረት አሁን የሚታዩት ፡-የዳግም ምጽአት ፍርድ፣ የድንግል ማሪያም ንግስና ፣ ኪዳነ ምሕረት፣ እና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን የዘውድ ስርዓት የሚያሳዩ ሥራዎችን ሰርተዋል ፡፡
ከዚህም ሌላ አሁን በሐረር ከተማ ቆሞ የሚታየውን የልዑል ራስ መኮንን ሀውልት የቀረጹት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ናቸው ፡፡
ከታዋቂ ሥራዎቻቸው በከፊል
• በአዲስ አበባ በቀድሞው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት አዳራሽ መግቢያ የሚታየው በመቶ ሃምሳ ካሬ ሜትር ላይ የተሳለው ትልቅ የመስታወት ስዕል
• አዲስ አበባ በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የውስጥ ስዕሎች፣ ሞዛይኮች
• አዲስ አበባ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚገኘውን የመጀመሪያውን የ’ዳግም ምጽዓት ፍርድ ስዕል
• በሐረር የልዑል ራስ መኮንን ሐውልት
• በአዲግራት የ’ዳግም ምጽዓት ፍርድ ስዕል
• በለንደን ‘ታወር ኦፍ ለንደን’ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎት ቤት ከብር እና ከእንጨት የተሠራ የመንበር መስቀል
• በሩሲያ፣ አሜሪካ እና በሴኔጋል ኤግዚቢሽን ላይ የቀረበው ‘የመስቀል አበባ’ ስዕል
• “እናት ኢትዮጵያ’
• የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ምስል እና
• ‘ደመራ’ ተጠቃሾች ናቸው ፡፡
የስዕል እና ሌላ የኪን ሥራዎቻቸው ወዲያው በ’ቴምብሮች’፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የኪነ ጥበብ ትርዒት ላይ እጅግ በጣም እየታወቁና እየገነኑ መጡ።
ከዚህ ሁሉ ስራቸው በተጨማሪ ግን ጨረቃ ላይ ስማቸው የተፃፈላቸው ብቸኛው ጥቁር መሆናቸውና የሃገራችን #ኢትዮጵያን ሠንደቅም ️ አብረው ስላሰቀሉልን ልባችን በኩራት ይሞቃል።
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ማክሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2004 ዓ/ም በተወለዱ በ79 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለዩ። ቀብራቸውም በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈፅሟል። https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=2351013938257248&id=100000459948280
በስነ ጥበብ ዘርፍ ላከናወኑት ሥራ እጅግ እናመሠግናለን 
ምንጭ:-  እምዬ ሚኒሊክ  
Filed in: Amharic