>

“በመንግሥትህ ጉዳዮች ላይ ፍላጎት ካላሳየህ፤ በቂሎች አገዛዝ ሥር ለመውደቅ ትገደዳለህ” ታዋቂው ፈላስፋ ፕሌቶ

“በመንግሥትህ ጉዳዮች ላይ ፍላጎት ካላሳየህ፤ በቂሎች አገዛዝ ሥር ለመውደቅ ትገደዳለህ” 
ታዋቂው ፈላስፋ ፕሌቶ
ቬሮኒካ መላኩ
ብአዴን  መስከረም ሳይጠባ ከደጃፍ አድሱን አመት የሚጠብቀው በውስጠ ድርጅታዊ አብዮታዊ መስተንግዶ  እንደሚሆን አረጋገጠ ።
የብአዴን ዓለም ቀኖና የተቀለሰበት ወጋግራ የቆመበት መሬት እየከዳው አንድ በአንድ ሲናድ  ከሚወርደው ናዳ ለማምለጥ ታሪካዊ እርምጃ ወሰደ። ድንቅ ነው።
ብአዴን እስከ ትናንት ድረስ ሲገዛበት የነበረው ሕግ – ” Bereket ሴንትሪክ” ወይም በረከት ስምኦንን የፖለቲካ ጋላክሲ ማዕከል አድርጎ በሚያስቀምጥ የተወላገደ ንድፈ-ሐሳባዊ አረዳድ ነበር፡፡
 ይህንን ንድፈ-ሐሳባዊ ትንተና ደመቀ መኮንንና ገዱ አንዳርጋቸው ከመነቅነቃቸው በፊት በብአዴን ዓለም በረከት ስምኦን እንደ አድባር ዋርካ እየተመለከ ለ27 አመታት ነግሶ ኖሯል፡፡
አብዮትን የፖለቲካ የበኽር ልጅ ነች። አብዮት ልጆቿን ትበላለች የሚለው መፈክር ለብአዴንም ሰርቶ የበህር ልጆቿን በረከትን ስምኦንንና ታደሰ ጥንቅሹን ቀርጥፋ በላች።
አሁን በአሮጌው ትቢያ ላይ አዲሱ ግኝት ይቀለሳል፡፡ ልክ እንደ ፖለቲካዊው ምህዳር ሁላ ብአዴንም በመሬት አንቀጥቅጥ አብዮት ሲታመስ ከርሟል ።
የተሳፈረበት የለውጥ ባቡር እንደ ተርሲስ ባቡር ቀጥ ከማለቱ በፊት ግን ልብን በሀሴት ቀጥ የሚያደርግ እርምጃ ወሰደ።
በስር ነቀል ለውጥ እየታገዘ ያረጀ ያፈጀውን አሠራር ግብዓተ ቀብር ፈጽሞ፣አዲስ ሳይንሳዊ የፖለቲካ አመራርን ለዓይነ ሥጋ ሊያበቃ መንገድ ጀመረ።ብአዴን በለውጥ ሀዲድ ላይ ባቡሩን መንዳት ቀጥሎ ጎታች የሆኑትን አለምነው መኮንን ፣ ከበደ ጫኔ፣ ዝማም እና ጌታቸው አምባዬ የተባሉትን የበረከት ስምኦን ዘረመል አረሞች እንደ ሙጃ ነቃቅሎ እንደሚጥል እንጠብቃለን።
በመጨረሻ ብአዴን ለአማራ ህዝብ ወርድና ቁመና የሚመጥን ድርጅት ለመሆን ዳዴ እያለ ነው። እኛም ከዳዴነት አልፎ ህዝቡን ፊት ፊት እየመራ የሚያሻግር ይሆን ዘንድ ከጎኑ እንቆማለን።
ታዋቂው ፈላስፋ ፕሌቶ “በመንግሥትህ ጉዳዮች ላይ ፍላጎት ካላሳየህ፤ በቂሎች አገዛዝ ሥር ለመውደቅ ትገደዳለህ” (If you do not take an interest in the affairs of your government, then you are doomed to live under the rule of fools) ያለውን ታላቅ አባባል እዚህ ላይ በማስታወስ ብአዴን ተመልሶ ጭቃ ውስጥ መልሶ እንዳይዘፈቅ ከጎኑ መቆም የሁሉም አማራ የውደታ ግደታ ነው።
Filed in: Amharic