>

በተፈጥሮ የምንታደለውን ዜግነት እና ሐገር ተነጥቆ በስደት መኖር ብዙ ህመም አለው!! (አዜብ ወርቁ)

በተፈጥሮ የምንታደለውን ዜግነት እና ሐገር ተነጥቆ በስደት መኖር ብዙ ህመም አለው!!

አዜብ ወርቁ

ሁለገብ የኪነጥበብ ባለሙያዋ ዓለም ጸሐይ ወዳጆ በሐገሯ ውስጥ በነበራት ቆይታ ለሐገራችን ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ከሐገሯም ከራቀች በኋላ የኢትዮጵያን ታሪክ ባህል እና ኪነጥበብ ለማስተዋወቅ ላደረገችው ትጋት ለማመስገን እንዲሁም ልምዷን እና ሙያዋን የምታካፍልበት ባለሙያዎች እና የጥበብ አድናቂዎችም እውቀት የምናተርፍበት መድረኮች እየተመቻቹ ነው፡፡

ይሄ መድረክ ሲዘጋጅ በቅድሚያ ዓለምጻሐይን ለማያውቃት ሆኖም ግን የምን ግዜም ምርጥ ከሆኑት የፈጠራ ስራዎቿ ጋር አብረን የኖርን የጥላሁን ገሰሰን “ኢትዮጵያ”ን በየመድረኩ ያቀነቀነን፣ “ሰላም” የተሰኘው መሓሙድ አህመድ የተጫወተውን ተወዳጅ ዘፈን የምንወድ ስለ ዓለም ሰላም የሚነሱ ሃሳቦች እና የሚፈጸሙ የሰላም ስምምነቶች በ ‹‹ሰላም›› ሙዚቃ ሲታጀብ ሐሳባችንን የሚያጎለብትልን ፣ ለሰላም ስንጨባበጥ ስሜትን ከውስጥ ፈንቅሎ እጅ ለእጅ የሚያያይዘን፣ በደስታ የሚያስነባን፣ የሚያስተቃቅፈን ዘመን ተሻጋሪ የሆነው ድንቅ ግጥም እና ሌሎችም በርካታ ስራዎች ፈጣሪ ዓለምጸሐይ ወዳጆ መሆኗን ለማናውቅ በስራዎቿ ማስተዋወቅ እና ማስታወስ ተገቢ በመሆኑ ነው፡፡

ዓለም ጸሐይ ባለፈው ጽሑፌ ዘርዘር አድርጌ የጠቀስኳቸውን በርካታ ስራዎች ከመስራቷም በተጨማሪ ከ27 ዓመታት በኋላ ወደ ናፈቀቻት ሐገሯ ስትመለስም ባዶ እጇን አይደለም፡፡

ግጥሞችን፣ ወጎችን፣ ለዘመናት በኢትዮጵያ ላይ ሆኖ ለማየት የጓጓችበት የለፋችበትን አሁን እውን ለማድረግ የተነሳችበትን ታላቅ ሐሳብ፣ ከዜማ ሊዋሃዱ በድምጻዊያን ሊቀነቀኑ የተሰናዱ በርካታ የዘፈን ግጥሞችንም ይዛ ነው፡፡ ዓለም ፀሐይ ለ27 ዓመታት በአካል ከተለየቻቸው ቤተሰብ እና ወዳጆቿ ጋር ልትገናኝ ነው፡፡

በተፈጥሮ የምንታደለውን ዜግነት እና ሐገር ተነጥቆ በስደት መኖር ብዙ ህመም አለው፡፡ ይሄን የዜግነት በረከት ማነው የሚነጥቀው? ማነውስ የሚመልሰው? የሚፈጠረው ህመምስ እንዴት ያለ ነው? የሚለውን ለመግለጽ ከወራት በፊት በደራው ጨዋታ ፕሮግራም ላይ ዓለም አቀፍ ታዋቂነት ያተረፈችው የደበቡ አፍሪካዊቷን ሚሪያም ማኬባን ታሪክ እንደምሳሌነት በመጥቀስ በሷ የስደት ህይወት ታሪክ ውስጥ ከሐገር ተሰደው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያኖችን ህመም ለማሳየት በማሰብ ሚሪያም ማኬባ ለአንድ መጽሔት የሰጠችውን ቃለመጠይቅ ተርጉመን በደራው ጨዋታ ፕሮግራም ላይ አቅርበነው ከነበረው እና ሚሪያም ማኬባ ስለስደት ከተናገረቸው ጥቂቱን እናካፍላችሁ፡፡

ሚሪያም ማኬባ ፡-፡  “ሐገር በችግር ውስጥ በነበረችበት ጊዜ በስደት ውጪ ሐገር ኖሮ ሁኔታዎች ሲስተካከሉ ወደ ሐገር ተመልሶ ሰዎች ላይ ይፈጸም የነበረውን ማየት እና መስማት ያማል፡፡ አቅመቢስነት እና አንዳንዴም የጥፋተኝነት ስሜት ነበር የሚሰማኝ፡፡ ሀገሬ ለመግባት እንዳልችል መታገዴ በጣም ከባድ ህመም ነው፡፡ ሆኖም ግን ሐገሬ ከወገኖቼ ጋር ችግሩን ተካፍዬ፣ አብሬያቸው ሆኜ አንድ ነገር እንኳን አለማድረጌ ድንጋይ እንኳን አለመወርወሬ ከሐገሬ ውጭ ተቀምጬ ሁሉም ሆኖ ሁሉም ተቀየሮ ማየት ከባድ ህመም አለው፡፡ አንዳንዴ ከሐገር ቤት ለቤተክርስቲያን ዝማሬ ፣ ለአገልግሎት ወይም ለሌሎች ጉዳይ ወገኖቼ ወዳለሁበት ሐገር ይመጣሉ የመጡበትን ጉዳይ ጨርሰው ወደ ሐገርቤት ሲመለሱ አየር ማረፊያ ድረስ ሄጄ እሸኛቸዋለሁ፡፡ እጆቼን እያውለበለብኩ ከተሰናበትኳቸው በኋላ መኪናዬ ውስጥ ገብቼ አለቅሳለሁ… አልቅሼ አልቅሼ ሲደክመኝ እራሴን ለማጽናናት አንድ ቀን እኔም ወደሐገሬ እመለሳለሁ ብዬ አስባለሁ መልሶ ግን ሃሳቤ በጥቁር ጭጋግ ሽፍን ይልብኝና ምንድነው የማወራው ምናልባትም መቼም መቼም ሐገሬን አላያት ይሆናል ብዬ ተስፋ እቆርጣለሁ፡፡ለእኔ እጅግ ከባድ የነበረው አሁንም ድረስ ሳስበው የሚያመኝ እናቴ ስትሞት በቀብሯ ላይ ተገኝቼ አፈር አለማልበሴ ነው፡፡ እናቴን አልቀበርኳትም፡ ››

ዓለምጸሐይ ወዳጆም ወላጅ እናቷን ፣ ወላጅ አባቷን፣ የትዳር አጋሯን እና የልጆቿን አባት ቆማ ለመቅበር አልታደለችም፡፡

እርሟን ልታወጣ ፣ ከ27 ዓመታት በኋላ ከወገን ከቤተሰቦቿ ጋር በዓይነስጋ ልትተያይ፣ ልምዷን እና እውቀቷን በአካል ተገኝታ ልታካፍል ለሐገሯ ያሰበችውን ያለመችውን ልትፈጽም ማክሰኞ ነሐሴ 22/2010 ዓ.ም ከጠዋቱ በአንድ ሰዓት ወደ እናት ሐገሯ ልትመጣ ነው፡፡

በሰላም ለሐገርሽ ያብቃሽ

Filed in: Amharic