>

ኦሮምኛ የስራ ቋንቋ መሆኑ ለሰፊዋ ኢትዮጵያ ዳይናሚዝም ጠቃሚ እንጂ ሸክም አይደለም! (ዮናታን ተስፋዬ)

ኦሮምኛ የስራ ቋንቋ መሆኑ ለሰፊዋ ኢትዮጵያ ዳይናሚዝም ጠቃሚ እንጂ ሸክም አይደለም!
ዮናታን ተስፋዬ
ኦሮምኛ የስራቋንቋ ይሁን ሲባል አማርኛ ይቅር ማለት አይደለም። አማርኛ በታሪክ አጋጣሚ የሀገሪቷ የስራ ቋንቋ ሆኖ ሲሰራበት መቆየቱ በብዙ የሀገሪቷ አካባቢዎች ከአፍ መፍቻ ቀጥሎ መግባቢያ ቋንቋ ኆኗል። ኦሮምኛም በይፋ የሀገሪቷ የስራ ቋንቋ ባይሆንም በተለያየ የታሪክ አጋጣሚ በተለይም በአጎራባች ክልሎች ጨምሮ በሌሎች ክልሎች የሚነገር ቋንቋ ነው። ከዚህ ረገድ በተለያየ መልኩም ቢሆን ሁለቱም ቋንቋዎች ሰፊ ተናጋሪ ስላላቸው የፌደራል የስራ ቋንቋ መሆን ይችላሉ።
እንግሊዘኛን በተመለከተ የፌደራሉ የስራ ቋንቋ ባይሆንም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ሲባል መማር የማይቀር ጉዳይ ነው። በሯን ዘግታ ለዘመናት የኖረችው ቻይና እንኳን መንደሪን ብቻውን እንደማያዋጣ በመረዳት ዜጎቿ እንግሊዘኛ ማስተማር ከጀመረች ቆየች።
ሌሎች የሀገራችን ቋንቋዎች በተመለከተ እንደየ አካባቢው ሁኔታ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ጭምር እንዲማሩ ማድረግ ይቻላል። ለምሳሌ እስከዛሬ በነበረው አሰራር በትግራይ ክልል ከትግራይ ባልተናነሰ ሁኔታ አማርኛ ትምህርት ይሰጣል ከዚህ የተነሳም በፌደራሉ መንግስት ቢሮክራሲ ውስጥ በርካታ የትግራይ ክልል ተወላጆች ያለምንም ችግር ገብተዋል። ከሆነ ዓመት በኋለ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ያለውን የኢኮኖሚ ኦፖርቹኒቲ ኤክስፕሎይት ለማድረግ በኢንፎርማል አካሄድ ኦሮምኛን እየተማሩ በከፍተኛ ሁኔታ በክልሉ ከፍተኛ የመንግስት መዋቅር አንስቶ እስከ ትንንሽ ሱቆች ከሚዲያ አንስቶ እስከ ቀበሌ ካድሬነት ገብተው ሲሰሩ ቆይተዋል። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች በማጤን ይመስለኛል የአማራ ክልል ያሉ ዩኒቨርስቲዎች ኦሮምኛን ለማስተማር ሀሳቡን እያጤኑ ያሉት።
በአጠቃላይ ከላይ ባነሳሁትም ምሳሌዎች ይሁን በሌላ ምክንያቶች ሀገሪቷ ካላት ሰፊ ግዛት፤ ከህብረ ብሔራዊነቷ እና ከቋንቋዎቹ ባህሪያት በመነሳት ከአማርኛ ቀጥሎ ኦሮምኛ እና እንግሊዘኛ የሀገሪቱ የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ እጠይቃለሁ። በትምህርት ፖሊሲው ፍኖተ ካርታም ሶስት ቋንቋ ተብለው የተጠቀሱት እነዚሁ ቋንቋዎች እንዲሆኑ ጥሪ አቀርባለሁ!
ኢትዮጵያ ለሁሉም ሁሉም ለኢትዮጵያ!
Filed in: Amharic