>

የአማራና የኦሮሞ ፖለቲከኞች ያቆሙትን  የጥላቻ ግንብ  የናዱት የዘውዴ ጉደታ አረፉ!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

የአማራና የኦሮሞ ፖለቲከኞች ያቆሙትን  የጥላቻ ግንብ  የናዱት የዘውዴ ጉደታ አረፉ!!!
አቻምየለህ ታምሩ
ልብ የሚሰብረው  ቀዳማዊው የድልድይ አርክቴክት ህልፈተ ህይወት!!!
በዛሬው እለት ኢትዮጵያ ሲደክምላት የነበረ ውድ ልጇን አጣች! የትውልድ ድልድዩ  ዘውዴ ጉደታ ከዚህ አለም በሞት  መለየቱን  ስሰማ  በተሰበረ ልብ ነው!  ወዳጄ ዘውዴ ጉደታ የአማራና የኦሮሞ ፖለቲከኞችን በማቀራረብ  በፖለቲካ ለተፈጠሩ ችግሮቻችን መፍትሔ  ይፈለግ ዘንድ ከልቡ  ሲወጣ ሲወርድ፤ ለገንዘቡና ለጊዜው ሳይሳሳ  ድልድይ  በመስራት ሲደክሙ  ከማውቃቸው  ሰዎች መካከል አንዱና ቀዳሚው  ነው።
ዘውዴ የአማራና የኦሮሞ ፖለቲከኞች መካከል የቆመውን  የጥላቻ ግንብ  መንገድ ፈልጎና  ተቀራርቦ በመነጋገር ማፍረስ  የጋራ  ድልድይ መስራት ይቻላል በሚለው እሳቤ ግንባር ቀደም ተሰላፊና ራሱንም የተግባር ሰው አድርጎ  ይሰራ የነበር ውድ ሰው ነበር።
ዘውዴ ከፖለቲከኛነት በላይ ሰው ነው።  ለጠሩት ሁሉ የሚደርስ፣ እጅግ ቀና፣ ትሑት፣ ሰው አክባሪና በመነጋገር የሚያምን  ታላቅ ሰው  ነበር። ብዙ ጊዜ ተሟግተናል፤ ተከራክረናል፤ በሀሳብም ተለያይተናል!  ስለተሟገትንና በሀሳብ ስለተለያየን ግን አንድም ቀን  ወንድምነቱን፣ ክብሩን፣ ቀናነቱን፣ የዘወትር ቤተሰባዊ ሰላምታውን  ቀንሶ አያውቅም ነበር።  ዘውዴ «ምናለ ሰው ሁሉ እንደ አቶ ዘውዴ ጉደታ በሆነ» የሚያሰኝ  ሰው ነበር!
በሰው ላይ ሞትን የሚያህል እዳ  ተጭኖ  ዘውዴ ጉደታም  ያሰበውን  ሁሉ ለመፈጸም ባለመቻሉና  የለፋላትን አገሩን  እግሩ ሳይረግጥ  ማለፉ እጅግ ያሳዝናል። ትልቁ  ሰው ባላሰበውና እጅጉን በሚያስፈልግበት ሰዓት በሰው አገር  አለፈ!  ሞቱ ልቤን እጅጉን  ሰብሮታል!  ዘውዴ ሆይ! እግንዲህ ምን ይባላል፤
እግዚአብሔር ነፍስህን   በገነት ያኑራት። ለወዳጆችህና ለቤተሰብህ  በሙሉ ጽናትንና ብርታትን ፈጣሪ እንዲሰጣቸው ከልብ እመኛለሁ!
Filed in: Amharic