>

ካድሬነት ልጓም ያስፈልገዋል! (ጌታቸው ሽፈራው)

ካድሬነት ልጓም ያስፈልገዋል!
ጌታቸው ሽፈራው
ካድሬ የፖለቲከ ድርጅት አባል ነው። አባል ብቻ ግን አይደለም። ስለ ድርጅቱ መልካም  መልካሙን ሲሰብክ የሚውል አባል ነው። ካድሬነት አዝማሪነት ነው። የድርጅቱን ደካማ ጎን እያለፈ መልካም መልካሙን ብቸ ማውራት ነው።
ድርጅቶች የሚጎለምሱት በውስጠ ድርጅት ትግል፣ ከውጭም በሚሰጣቸው አስተያየትና  የሚገጥማቸው ትግል ነው።
ካድሬዎች ግን ብዙ ጊዜ ይህን አይጠቀሙበትም። ለሀገር ተብሎ የተመሰረተን ድርጅት ካድሬ ሆነው ድርጅቱን ከሀገር ያስቀድሙታል። ለማን እንደተመሰረተ ረስተውት ሕዝብና ሀገርን ረስተው፣ ድርጅቱ በሕዝብና በሀገር ላይ የተሳሳተውን ወደጎን ብለው ድርጅቱ ላይ ይለጠፋሉ።
የኢትዮጵያን ፖለቲካ አዘቅት ውስጥ የከተተው ጭፍን የድርጅት ፍቅር ነው። የኢህአፓ አባል ኢህአፓን አስቀደመ፣ የመኢሶን አባል መኢሶንን አስቀደመ፣ የኢሰፓ ካድሬ በኢሰፓ አመለከ።  ሀገር ተረስታ መዝሙሩ፣ ሙገሳው ስለ ድርጅት ሆነ።
ሕዝብና ሀገር በላይ ድርጅት ቀደመ። የድርጅት ፍቅር ያናወዘው ወንድሙን ረሳው፣ ገበሬውን ረሳው፣ ተማሪውን ረሳው፣ ሰራተኛውን ረሳው፣ ስለ ድርጅቱ ገንቢ አስተያየት የሰጠውን ወንድሙን ጠላት አደረገው። የድርጅት ፍቅር አናውዞታልና።
ለሀገር ብየ መሰረትኩት ያለውን ድርጅት ጣኦት አድርጎታልና። ስለ ኢሰፓ አሉታዊ የሚመስል አስተያየት የሰጠ ተረሸነ። የኢሰፓ ካድሬዎች ድርጅቱን ከሀገር በላይ አድርገውታልና ምንም አይነት አስተያየት መቀበል አይፈልጉም። ተሰብስበው ከሀገር በላይ ስለ ድርጅት መዘመር ለምደዋል።
ይህ በእኛ ዘመንም እየተደገመ ነው! 
የድርጅት ፍቅር ጭፍን ነው፣ የካድሬ ምክንያታዊ ለማግኘት ይከብዳል። ፕሮፖጋንዳ ትልቅ የፖለቲካ ተግባር በመሰለበት ሀገር ደግሞ ካድሬነት ትልቅ ስራ ሆኗል። በገዥውም በተቃዋሚውም በኩል ካድሬነት እውነታን መካድ ላይ፣ ድርጅትን መከላከል፣ ሕዝብንና መርህን ለድርጅት ሲባል መርገጥ ላይ እያተኮረ ነው። በተግባር ተመሳሳይ እየሆነ ነው።
ድርጅት ገንዘብ አለው። ሲበዛ ተኳሽ፣ ሲያንስ ተሳዳቢና ስም አጥፊ አያጣም። ሚዲያን መጠቀም ይችላል። በተቃራኒው ድርጅት የሚነግድባቸው ድምፅ አልባዎች ይኖራሉ።
መተቸት ያልለመደ፣ የውስጠ ፖለቲካ ትግልን ያላዳበረ ድርጅት ቆሜለታለሁ በሚለው ሕዝብ ላይ የሚፈፅመውን ስህተት የሚነግረውን አሪዮስ ያደርገዋል። ዲሞክራሲ ባልዳበረበት ሀገር ትልቁ ፈተና ከገዥዎች የሚመጣው ብቻ አይደለም።  ተቃዋሚ ነኝ ከሚልም ሆነ ተቃዋሚ ከሚባለው የሚመጣውም ቀላል አይደለም። ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ይከበር እያለ በእሱ ላይ ሀሳብ እንዲነሳ አይፈቅድም። ለሕዝብ መቆምን እየሰበከ ሕዝብን ሲረግጥ መነቀፍን አይፈልግም። ገዥዎቹ ላይ እጠላዋለሁ ያለውን ሲፈፅም በግልፅ ቀርቶ በሹክሹክታ እንድትነግረው አይፈልግም። ብትነግረውም በሕዝብ ላይ ያስተባብላል፣ ጭቃ ይቀባሃል እንጅ አያርምም። አይጠቀምበትም!
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ይህ ክፉ የካድሬነት ባህል ከመቸውም ጊዜ በላይ እንደመልካምነት እየታየ ነው።  ድርጅታዊ ፍቅር ለሐገር ፍቅር መነሻ እስኪመስል ድረስ በካድሬነቱ ደረቱን የሚነፋው በዝቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ካድሬነት ድብልቅልቁ ወጥቷል።
ካድሬነት በጠያቂነት ላይ ውህደት ፈጥሯል። የገዥዎችና የተቃዋሚ ካድሬነት አጀንዳ አገናኝቷቸዋል። እስረኛ ይፈታ ሲባል፣ ስለ ተፈናቃዮች ሲጮህ የገዥውም የተቃዋሚውም ካድሬዎች በአንድነት “ዝም በል” በማለት የሕዝብን ጥያቄ  መደፍጠጥ ላይ እየተባበሩ ነው።
በድርጅት ፍቅር ያበዱት የመኢሶን እና የኢሰፓ ካድሬዎች ስልጣን፣ ለስልጣን ምንጭ የሚሆን ተስፋ በሌሎች ላይ አንድ እንዳደረጋቸው፣ በሌሎች ላይ አብረው እንደመቱት ሁሉ፣ የደርግ የሆነን የራሳቸው አደርገው እያወደሱ ጠያቂን አብረው የደመሰሱበትን ያህል ዛሬም የካድሬ ሕብረት እየታየ ነው።
ለገዥዎችም ለተቃዋሚውም ሰልፍና ስብሰባ የሚጠራ፣ የሚያጨበጭበው ሁሉ ድርጅት በሕዝብ ጥቅምና ክብር ላይ ሲመጣ “ዝም በል” ከማለት አልፎ የስድብና የስም ማጥፋት ዘመቻ ይጀምራል!
በሀገራችን ታሪክ የድርጅት ፍቅር የተመዘገበና ያለም ነው። ይህ ግን ቆይቶ ውጤቱ መና ሆኗል። ለድርጅትም ሆነ ለሀገር የሚጠቅመው ክፍተቱን፣ ሕፀፁን እስከ ጥጉ መናገሩ ነው። አዲስ ሆነ የቆየ ድርጅት በሕዝብ ላይ ሀይል አለው፣ የመሸወድ ብሎም የመነገድ ክፉ ባህሪ ያዳብራል። ይህ ድርጅታዊ ባህሪ የሚቀረፈው በመጠየቅ ነው። መጠየቅ ያለመደ፣ በድርጅት ፍቅር የናወዙ አባላት ያሉት ድርጅት ለዚህ ግብረ መልሱ የከፋ ሊሆን ይችላል።
መሳርያም፣ ተሳዳቢም ይዞ ይመጣል። ለገበሬው፣ ለእስረኞች፣ አቅምና ድምፅ ለሌላቸው ሲባል፣ ቢጠቀምበት ለድርጅቱም ለሀገርም ስለሚጠቅም ከመጠየቅ ወደኋላ አለማለት ነው የሚጠቅመው!
በጭፍንነቱ እሱ ብቻ አይጠፋም። ድርጅት ይዞነው ወደገደል የሚገባው። ሀገርና ሕዝብ ይዞ ነው ወደገደል የሚሄደው። ጎትቶ ገደል ውስጥ ሳይከትት ልጓም መሆን የግድ ይላል። ኃላፊነትም ነው። ምን አልባት አንድ ቀን አይኑ ሲገለጥ ይታየው ይሆናል። ባይመለስ እንኳ ሌላ አካል ይዞ ገደል መግባት የለበትም። በድርጅት ፍቅር ናውዞ፣ ስለ ድርጅት ሲዘምርና ሲያዜም ሕዝብን እንዲረግጥ ሊፈቀድለት አይገባም!
 ለድርጅትና ካድሬዎች ልጓም ማበጀት ነው! ፊት ለፊት መነገር አለበት!
ድርጅቶች ይፈርሳሉ፣ ይሳሳታሉ፣ ግለሰቦች ያልፏሉ። ሀገርና ሕዝብ ቋሚ ነው!
Filed in: Amharic