>
5:13 pm - Friday April 18, 9152

ህወሀቶች ድንኳን ጥለው ለቅሶ ተቀምጠዋል!!! (መሳይ መኮንን)

ህወሀቶች ድንኳን ጥለው ለቅሶ ተቀምጠዋል!!!
መሳይ መኮንን
”ኢትዮጵያ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን አቅጣጫ ስታ አደገኛ ጉዞ ላይ ናት። መፍትሄው ወደ ቦታችን መመለስ ነው።” ወ/ሮ ፈትለወርቅ የኢህአዴግ ጽ/ቤት ሀላፊ። ህወሀት በጥፍሯ ቆማ እየፎከረች ነው። የፓርላማ የኢህአዴግ ተጠሪ አቶ አስመላሽ ወልደስላሴም ”ህዝበኝነት” እያለ ዶ/ር አብይን ከዝቅ አድርጎ ሲያብጠለጥል ሰማሁት። የመለስን ሞት ስድስተኛ ዓመት እያሰቡ ያሉት ህወሀቶች ድንኳን ጥለው ለቅሶ ተቀምጠዋል። ቤተመንግስቱን ማጣታቸው በሚገባ አሟቸዋል። ዳግም ለመቆናጠጥና ኢትዮጵያ ወደ 27ዓመቱ የመቃብር ጨለማ ዘመን ለመመለስ ፍላጎታቸውን ከመቀሌ ሆነው አሳይተዋል። ከሰፈሩ ያለፈ ራዕይ ሳይኖረው የትግራይ ህዝብን ከሌላው የኢትዮጵያ ወገኑ ጋር በሰላም እንዳይኖር መርዝ ተክሎ የሄደውን መንደርተኛ መሪያቸውን እያሰቡ እዬዬውን አቅልጠውታል።
እውነት ለመናገር አቶ መለስን ”ታላቁ” እየተባለ ዛሬ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲነገርላቸው ስሰማ አጥወልውሎኛል። የለውጥ ሂደቱ በውስጤ የፈጠረውን ተስፋ የሚያጨልም ባይሆንም ዘንድሮም የመለስ ስም በዚህ መልኩ ሲጠራ መስማት መንፈሴን ይረብሸዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ጨዋነትና ፈሪሃ እግዚያብሄር የሰጠው ትዕግስት እድሉን ሰጣቸው እንጂ ህወሀቶች እንደሀጢያታቸው ቢሆን ከለውጡ በኋላ ቤታቸው ከርቸሌ መሆን ነበርበት። ይሉኝንታና ሀፍረት ያልፈጠረባቸው፡ ሰው የመሆን ጸጋና በረከት ያልታደሉ  ዓይና አውጣ፡ የትኛው ቃል እንደሚገልጻቸው አላውቅም። ሀገሪቱን ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ከተው የኖሩበት ዘመን የሚያንገበግበን ኢትዮጵያውያን ፊት ቀርበው ዛሬም ስፎክሩና ሲሸልሉ ማየት በብርቱ የሚያም ነው።
ህወሀት አቅም ባይኖረውም ለውጡን እንደሚቀለብሰው በአደባባይ እየነገረን ነው። ሞንጆሪኖ ከመቀሌ በትክክል ያስተላለፈችው መልዕክት ወደ ቦታችን መመለስ አለብን ነው። ወደ ዚያ የመቃብር ዘመን፡ ከጨለማው ከድቅድቁ አስፈሪ የጭቆናና የውርደት ዘመን ካልተመለስን እንተላለቃለን እያለች ነው። የአስመላሽ ቀረርቶም ኢትዮጵያን ህወሀት ካልገዛት ሰማይ ምድሩ ይናወጣል አይነት መልዕክት የተሸከመ ነው። ህወሀት ተስፋ አልቆረጠችም። ትንፋሿ እየተቆራረጠ፡ የሞት ሳል እየሳለች ”ዘራፉን” አልተወችውም።
የህወሀት የዳግም ቤተመንግስት ምኞት ከንቱ ነው። በእርግጥ ምኞት አይከለከልም። በመለስ ሙት ዓመት ሰበብ ሰሞኑን የጀመሩት ፉከራና ሽለላም ሰሞንኛ ድንፋታ ሆኖ ያልፋል።
Filed in: Amharic