>

ሁሉን በካድሬ አስወረራችሁ - ምናለ የእምነት ተቋማትን እንኳን ብትተውልን?!? (መስከረም አበራ)

ሁሉን በካድሬ አስወረራችሁ – ምናለ የእምነት ተቋማትን እንኳን ብትተውልን?!?
መስከረም አበራ
ዘረኝነት ባመጣው ጣጣ መከራ የምናየው እኛ ሃገር ቤት ያለነው ሰዎች ነን፡፡ እኛ የዘረኝትን ጣጣ ነገር ዓለሙ ካለፈ በኋላ “you tube” አይደለም የምናየው፡፡ የሰው ልጅ በዘሩ ምክንያት በድንጋይ ተወግሮ ተገድሎ እንደ ጧፍ በእሳት በነደደበት ሃገር እየኖርን  በተዓምር የተረፍንነን፣ በዘረኝት ጦስ ስምንት መቶ ሽህ ህዝብ በፈሰሰበት ሜዳ ላይ ልባችን እያነከሰ የምናልፍ የምናገድም ነን፣ ከሃገሬ ውጡ ባይ ሞት በበራችን ሆ ብሎ የሚያልፍ ሰዎች ነን!   ሰዎች ለስብዕና ታግለው ባቀኑት ሃገር ቁጭ ብሎ ሰው መሆን ባይቻል እንኳን ዝም ማለት ወይ አስቦ ማውራት ከባድ አይመስለኝም፡፡ አለማዊውን ፖለቲካ አፍ ያመጣውን እያወሩ ከማመስ አልፎ በመንፈሳዊ ተቋማት ውስጥ ገብቶ “በእንትን ቅጥር ያላችሁ ሰዎች በእንትን ቋንቋ ቀድሱ፤በእንትን መንደር የምትኖሩ ሰዎች በእንትን ቋቀዋ አዛን አድርጉ” ማለት ወጥ መርገጥ ነው፡፡
ለመሆኑ መንፈሳዊው መንደር ዓለማዊው ክበብ እንደሚያይ እንደማያይ፣ አለም እንደምትገመግም እንደማይገመግም በሰውነቱ ላይ ዶክትሬት የጫነ ሰው ሊጠፋው ይገባ ነበር??? ለማንኛውም አለማዊው የሃገራችን  የጎሳ ፌደራሊዝም ዘጠኝ ክለሎች ሲኖሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በጣም በርካታ  የሃገረ ስብከት ክፍሎች አሏት፡፡ለምሳሌ ጌዲኦ፣ሲዳማ እና ቡርጅ በአንድ ሃገረስብከት ውስጥ ሲሆኑ ከንባታ ሃድያ እና ጉራጌ በሌላ ሃገረስብከት ውስጥ ያድራሉ፡፡ አንድ ተደርጎ በተከለለው ሰፊው ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሃገረ ስብከቶችም እንደ ኦቦ ለማ መገርሳ ባሉ አንድ ጳጳስ አይመራም! ብዙ ጳጳሳት ናቸው የሚያስተዳድሩት፡፡ የእስልምናውም የራሱ የሆነ አደረጃጀት አለው!
በአለማዊው ፖለቲካ ዘሩ ብቻ በቂ የሆነ ካድሬ በትውልድ ቦታው ከሆነ የትም ቦታ በሚሰፋው  ወንበር ላይ ይቆናጠጥ ይሆናል፡፡ በመንፈሳዊው አለም ግን ሌላ መለኪያ ነው፡፡ቋንቋ ለመንፈሳዊ ተቋማት እንደ ጎሳ ፖለቲካው መንደር ዋነኛ ነገር አይደለምና አገልጋዮች የሃይማኖት መሪዎች ከየትም ተወልደው የትም ሄደው ፈጣሪያቸውን ያገለግላሉ፣ምዕመናኑን ያስተምራሉ፡፡ በኦሮሚያ ያሉ መንፈሳዊ ተቋማት በኦሮምኛ ስራቸውን ይከውኑ በሚለው የኦሮሞ መኳንንት ትዕዛዝ መሰረት እነዚህ የሃይማኖት አባቶች ተባረው እንደ ፖለቲካው በካድሬ ፓስተር፣ካህናት እና ሼኮች ይተኩ ነው ነገሩ! መንፈሳዊ እውቀት በኦሮምኛ ቋንቋ እውቀት ይተካል? ወይስ ኦሮሚያ ክልል ያሉ የሃይማኖት ተቋማትም ኦሮሞ ፓስተር፣ኦሮሞ ሼክ፣ኦሮሞ ቄስ ይሰይሙ እና “ከዘር ከቋንቋ ተዋጅታችኋል” ያላቸውን አምላክ ትዕዛዝ አትላንቲክ ማዶ ተሰይሞ በሚያዘው ሰውየ ትዕዛዝ ይተኩ? በፕሮቴስታንት እምነት  “በመንፈስ በመሞላቴ ሰማያዊ ቋንቋ በሆነው ልሳን እፀልያለሁ” የሚለውን አማኝ የህግ ዶክተሩ ምን ሊያደርጉት ነው? ፍርድቤት ሊገትሩት? ምናለ የእምነት ተቋማትን እንኳን ብትተውልን……… !
Filed in: Amharic