>
5:14 pm - Sunday April 20, 7119

ሊንከን እና መለስ፤ የምርጥ መሪ እና የመጥፎ መሪ ወግ!  (ስዩም ተሾመ)

ሊንከን እና መለስ፤ የምርጥ መሪ እና የመጥፎ መሪ ወግ! 
ስዩም ተሾመ
በአራት ኪሎ ቤተ መንግስት ዙሪያ ያለው የቀድሞ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ምስል ላይ “የክፍለ ዘመኑ ምርጥ መሪ” ተብሎ ተፅፎበታል፡፡ በእርግጥ አቶ መለስ ዜናዊ ይህቺን ሀገር ለ21 አመት መርቷል፡፡ በመሪነት ዘመኑ በራሱ ትክክልና ይበጃል ያለውን ነገር ሰርቶ አልፏል፡፡ ነገር ግን፣ ገና በ6ኛ የሙት አመቱ እነዚህ ምስሎች ከቤተ መንግስቱ ዙሪያ እየተነቀሉ ነው፡፡ በመለስ ዜናዊ ስምና ራዕይ የተሰየሙ ተቋማት ወደ ቀድሞ መጠሪያቸው እየተቀየሩ ነው፡፡ በአንፃሩ የአብርሃም ሊንከን ክብርና ዝና ከ150 አመታት በኋላም በአሜሪካኖች ልብ ውስጥ ደምቆ ያበራል፡፡
ባለፈው አመት የሊንከን ሜሞሪያልን የመጎብኘት እድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ በግራ በኩል ባለው የፕረዘዳንቱ ሃውልት ከላይ በኩል የተፃፈው ፅሁፍ እንዲህ ይላል፡- “IN THIS TEMPLE AS IN THE HEARTS OF THE PEOPLE FOR WHOM HE SAVED THE UNION THE MEMORY OF ABRAHAM LINCON IS ENSHRINED FOREVER” በቀኝ በኩል ባለው የአብረሃም ሊንከን ምስል ላይ ደግሞ እንዲህ ይላል፡- “The man who gave meaning, honor, and purpose of a nation speaks to us still.”
አዎ… የሀገርን ትርጉም፥ ክብርና ፋይዳ የሰጠው ፕረዜዳንት ዛሬም ድረስ ለአሜሪካኖች እየተናገረ ነው። አብርሃም ሊንከን ለአሜሪካ ትርጉም፥ ክብርና ፋይዳ የሰጣት አስከፊውን የአሜሪካ የእርስ-በእርስ ጦርነት በማሸነፍ የሀገሪቱን አንድነት በማስከበሩ ነው። በዚህ ምክንያት አብርሃም ሊንከን ከሞተ 150 አመታት በኋላም ለሀገሪቱ ሕዝብ ይናገራል፤ ዛሬም ድረስ አሜሪካኖች ጆሮና ልባቸውን ከፍተው ያዳምጡታል።
“የክፍለ ዘመኑ ምርጥ መሪ” የተባለለት መለስ ዜናዊ ግን ከሞተ 6 አመት በኋላ ክብርና ዝናው ተገፈፈ፡፡ ምክንያቱም መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያን ትርጉም፥ ክብርና ፋይዳ ያሳጣት፣ ለአስከፊ የእርስ-በእርስ ጦርነት ያመቻቻት፣ ከአንድነትና አብሮነት ይልቅ ሀገሪቱን ለመለያየትና ለመበታተን ጥረት ያደረገ መሪ ነው፡፡ በዚህ በጥቁሮች ሀገር የአፓርታይድ ስርዓትን የዘረጋ፣ በነፃነት ምድር ባርነትን ያቀነቀነ፣ ሥራና ሃሳቡ ሁሉ በክፋትና አሻጥር የተሞላ፣ በክፉ ምግባሩ የሚታወስ “የክፍለ ዘመኑ መጥፎ መሪ” ተብሎ በታሪክ ይታወሳል፡፡
Filed in: Amharic