>

ባህርዳር ላይ ሲሆን ለምን ያስወግዛል? (ጌታቸው ሺፈራው)

ባህርዳር ላይ ሲሆን ለምን ያስወግዛል?

ጌታቸው ሺፈራው

ከአንድ አመት በፊት ማህበራዊ ሚዲያው ላይ አንድ የትግል ስልት በደንብ እየተዋወቀ ነበር። በትጥቅ እታገላለሁ የሚለውም፣ ሚዲያውም ሳይቀር “ያዘው፣ በለው!” እያለ አሟሙቆታል። ሰላማዊ ትግል ያለውም ጥሩ የማዕቀብ ዘዴ ነው ብሎ ተወያይቶበታል። ገዥዎቹ ጋር የተጣመረው ኦህዴድ አቋም ይዞ ታግሎበታል። አትርፎበታልም።
በወቅቱ በአምቦ፣ ሻሸመኔ፣ ሀረርና ሌሎችም የኦሮሚያ አካባቢዎች ወጣቶች መኪና እያስቆሙ እህል፣ ከሰል፣ ቡና ሌላም ሌላም ሸቀጥ አውርደዋል። ኮንትሮባንዲስት የሚል ስም አንድ ሰሞን ፋሽን ሆኖ ነበር። ያ ወቅት የትህነግ ልክ የተለካበት፣ የተመታበት ወቅት ነበር። ለተቃዋሚው ቀርቶ ለእነ ቲም ለማ ወደ ስልጣን መምጣት የእነዛ ወጣቶች አስተዋፅኦ ቀላል አልነበረም። ኦህዴድ አመኔታ ለማግኘት ይህን ወቅት ተጠቅሞበታል። የአቶ ሀይለማርያም ሾፌር ነው የተባለው ሳይቀር ተይዞ ተፈርዶበታል።
በዚህ ወቅት ከኮንትሮባንድ ባሻገር ወደ ትግራይ ሊጫን ነው የተባለ ሁሉ ታግቷል። ተቃውሞ ያሰማ አልነበረም። ወጣቱ ይህን የሚያደርገው ለዘረፋ አልነበረም። ስለተዘረፈ እንጅ። ወጣቱ ይህን የሚያደርገቅ ፍትህ ስላጣ ነው። በትህነግ ጥላቻ የተነሳ ስለሆነ ነው። በውጭም በሀገር ውስጥም ያለ ፌስቡከኛ “አምቦ አልተቻለም፣ ሻሻመኔ አልተቻለም” እያለ አድንቋል።  በእርግጥ የትግሉ አንድ አካል ነበር። ትህነግ ልኩን ያወቀበት። በእርግጥ ትግል ነውና በዚህ ሂደት ስህተትም ይኖራል። አመዛኙ ግን አድናቆት ነበር!
የዛን ወቅት ትግል ኦህዴድም ተጠቅሞበታል።መጠቀም ብቻ ሳይሆን ሕገወጡን በደንብ ለይቶበታል። ብአዴን ህገወጥም ህጋዊም መለየት አልቻለም።  ብአዴን ዘረፋ አላስቆምለት ያለ ሕዝብ ህጋዊም ህገወጥም ሊያስቆም ይችላል። ይህ ድርጊት ከወራት በፊት ቢሆን ኖሮ አድናቆት በተቸረው ነበር። ቢያንስ አይወገዝም ነበር። ቢያንስ ሕዝብ አይዘለፍበትም ነበር።
ትናንት ባህርዳር ላይ የተደረገው ተመሳሳይ ነው። ተዘርፈናል ያለ ሕዝብ እህል ወደ ትግራይ እንዳይሄድ አስቁሟል። ትክክል ነው ነጋዴዎች ይከስራሉ፣ ሾፌሮች ይንገላታሉ፣ በዚህ መሃል ግርግር ይነሳል። ግን ባህርዳር ላይ ሲሆን ነው ይህ ሁሉ ጩኸት?  ባለፈው የባህርዳር ሰልፍ የወጣው ሰንደቅ አላማ በርካታ የኢትዮጵያ ከተሞች ላይ ወጥቷል። እንዲያውም በእርዝመቱ ከባህርዳር የላቀ። የትህነግ/ህወሓት ልሳንና ፖለቲከኞቹ ግን አሁንም ስለ ባህርዳር ነው የሚያላዝኑት። ስለ ባህርዳር የሚያላዝነው ግን ትህነግ ብቻ አይደለም። ትናንት ሌለ አካባቢ ሲደረግ “በለው!” ሲል የነበር ሁሉ ዛሬ ባህርዳር ላይ ሲሆን ሕዝብን ለመዝለፍ ይሮጣል።
በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ሁሌም መናጆ መፈለጉ ነው። ባለፈው የተሳሳተ ካርታ የግንባታ መሰረት ላይ ሲጣል ይህን ብቻውን መተቸት የፈሩ የእንትና ነው ብለው የማይጠሩትን የሀሳብ ካርታ በማናጆነት ይዘው  ቀረቡ። መሬት ላይ ያለና የሌለ።
 ትናንትናም በአንድ ወቅት እንደ ትልቅ የትግል ስልት ተደርጎ ሲሞገስ የነበረውን የአቅርቦት ክልከላ ባህርዳር ላይ ስለተከሰተ ከሻሸመኔው ድርጊት ጋር አብረው ለማስኬድ የጣሩ ብዙዎች ናቸው። የባህርዳሩን ብቻ አይደለም። የአብዲ ኤሊ መንግስት በፈፀመው ዘግናኝ እርምጃ የተበሳጩ የሀረርጌ ወጣቶች ወደ ሶማሊ ክልል ሊላክ የነበረውን ጫት አውድመውት ብዙ ሰው “ደግ አደረጉ” ብሏል። ትናንት አማራ ክልል ሳንጃ ላይ ይህ ሲሆን እንደነውር የተመለከቱት ብዙዎች ናቸው። ምነው ባህርዳር ዳር ላይ ሲሆን? ምንነው አማራው ላይ ሲሆን?
እነ ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን የመጡበት አንደኛው ስልት የትህነግ አቅም በመገዳደር ነው። ሕዝብ ወደ ትግራይ የሚላኩትን አቅርቦቶች እያስቆመ፣ ሲያወርድ ያኔ “ደግ” ተብሏል። ዛሬ እነ አብይ ስልጣን ላይ ሲሆኑ ለምን ነውር ሆነ? ባህርዳር ላይ ስለሆነ?
በመሰረቱ ህዝብ መሰል እርምጃ የሚወስደው ከመበደል የተነሳ እንጅ ከምንም አይደለም። ለዚህ መበደሉ ፍትህ የሚሰጠው፣ የሚያረጋጋው አካል ሲያገኝ “ተው” የሚለውን ይሰማል። እንዲያውም ሕዝቡ የመበደሉን   ያህል ግብታዊ ሆኗል ለማለት አይቻልም። በራያና ወልቃይት ወገኖቹ ምን እየሆኑ እንዳሉ ያውቃል። ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ምን እየደረሰባቸው እንዳለ ይረዳል።  ፋብሪካ እንዳይኖረው ተከልክሎ ኢንዱስትሪ የት እንዳለ ያውቃል። ጥሬ እቃ ከየት ወደየት እንደሚሄድ ያውቃል። የተዘረፈው፣ የተገረፈው፣ የተዘለፈውን ያውቃል። ይህ ሁሉ በደል ስሜታዊ ያደርጋል።   ይህ ስሜት የሚገራው ያስፈልጋል። ፍትህ የመጀመርያው ነው። አሁንም ማዶ ሆነው እየደነፉ፣ ሕዝብም ፍትህ ሳያገኝ ግብታዊ ቢሆን ምኑ ይገርማል? ሌላ አካባቢ እንደ ትግል የታየው ባህርዳር በአማራው ላይ ሲሆን ለምን ነውር ይሆናል?
እውነቱን ለመናገር ከሌላው በተለየ አማራው ላይ በማንነት መደራጀትም ነውር ተደርጎ እየተወሰደ ነው። አንድ በሌላ አካባቢ ሲደረግ የትግል ስልት የሆነ፣ የነበረም፣ አማራው ላይ ሲሆን ወንጀል የሚደረገው  በማንነት መደራጀቱ ፅንፍ እንዳስያዘው ለመወንጀል ነው።
ማዕቀብ አንዱ የሰላማዊ ትግል ስልት ነው። ይህኛው ሲሆን ገበሬው ገበያ አውጥቶ መሸጥ የለበትም። አሁን ይህ አልተቻለም። የተገዛውን ነው ለማስቆም እየተጣረ ያለው። ይህኛው ጉዳት አለው። ነገር ግን በደል ያንገፈገፈው ሕዝብ ማድረግ የቻለው ይህንን ነው። ይህም ሌላ ቦታ ላይ ሲሆን ትግል ነበር። ጥቅምም ነበረው። አማራው ላይ ሲሆን ግን ያስወግዛል።
“ያኔ ጠቅሞናል፣ አሁን ጊዜው አይደለም። ሌላ ችግር ይከፍታል” ቢባል ባልከፋ። ያኔም አሁንም ትህነግ ለሚፈፅመው አፀፋ ነው። ያኔም አሁንም የተዘረፈና የተገረፈ ሕዝብ የሰጠው ምላሽ ነው። ያኔም አሁንም  ሕዝብ ያስቆመው መኪናን ነው። ያኔም አሁንም ሕዝብ ብሶት አለበት። ለብሶቱ  ፍትህ አላገኘም። ትክክል አይደለም ቢባል እንኳ ኃላፊነቱ ተደራጅቻለሁ የሚል አካል እንጅ  የሕዝብ አይደለም። ትክክል አይደለም ቢባል እንኳ  ትክክል አይደለም የተባለበት በስርዓት መቅረብ ይኖርበት ነበር። ትክክል አይደለም ቢባል እንኳ ፈፅሞ ከጭካኔ ጋር እኩል መውቀጥ ባልተገባ ነበር።  አሁን ግን ትክክል ይሁንም አይሁንም ሕዝብን ማንቃት እያለበት፣ ለሕዝብ ፍትህ መታገል  እያለበት፣  ዘረፋውን ማስቆም እያለበት የሚገባውን ያልሰራው ሕዝብ የራሱን  አማራ ሲወስድ እየዘለፈ ይገኛል። መጀመርያ ኃላፊነቱን ሳይወጣ፣ አሁንም ኃላፊነትም ቅንነትም በጎደለው መንገድ ሕዝብ ይወነጅላል፣ ይኮንናል፣ ያወግዛል! ባህርዳር ላይ ሲሆን! አማራው ላይ ሲሆን!   የፖለቲካችን መገለጫ ይኸው ሆኗል!
Filed in: Amharic