>

በመፈክር የምታስተኛው ፤ በመፈክር የምትቀሰቅሰው፤ ግብስብስ (mob) - በዕውቀቱ ስዩም

በመፈክር የምታስተኛው ፤ በመፈክር የምትቀሰቅሰው፤ ግብስብስ (mob)
በህዝብ እና በግብስብስ (mob) መካከል ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ይገልጣሉ፤ ያልታተመው መዝገበቃላቴ በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት እንደሚከተለው ያስቀምጠዋል፤
ህዝብ (The people)
እንደየብጤው የሚሰባሰብ
ርስበርስ የሚናበብ
የጋራ መከራ ያሳለፈ፤
ለጋራ አላማ የተሰለፈ፤
ኑሮው በስራት፤
ህሊናን ወይም እግዜርን በመፍራት፤
የደመነፍሱን ዝንባሌ የገራ፤
በህግ በደንብ የሚመራ፤
የሚመካከር የሚወያይ፤
ካንድ እድሜ በላይ አርቆ የሚያይ፤
ስተቱን የማይደግም፤
በራሱ የማይለግም፤
በጊዜው የሚፈላ በጊዜው የሚሰክን፤
ክፋትን እንደ ፈንጅ የሚያመክን፤
አመል ችሎ የሚዳበል፤
ጉራማይሌ ልዩነትን እንደ እንግዳ የሚቀበል፤
ግብስብስ (mob)
ከዚም ከዚያም የተጠራቀመ ያልባሌ ሰው ስብስብ፤
ተከማችቶ የሚጎርፍ ተርጋግቶ የማያስብ፤
-የተቆጣ-
ስራና የህይወት አላማ ያጣ፤
ያለ ስራት የሚተራመስ፤
መስመር ጥሶ የሚርመሰመስ፤
ወድያው ተክቦ ወድያው የሚደረመስ፤
እምነቱ ሀሜት፤
መርሁ ስሜት፤
ሆድ የባሰው፤
በመፈክር የምታስተኛው ፤በመፈክር የምትቀሰቅሰው፤
አፍ የተሰጠው ጆሮ የሌለው፤
ማመዛዘን ያላደለው፤
ከጭንቅላቱ አንድ ሁለት ቡለን የጎደለው፤
ደንብ የማያከብር፤
ደካማ ላይ የሚጨክን ብርቱ ሲያይ የሚደነብር፤
ልቅ!
የራሱን መብት የሚጠይቅ የሌላውን መብት የሚጨፈልቅ!
አንደበቱ ከመተንኮስ –
ተግባሩ ጎጆ ከመለኮስ -የማያልፍ-
ሻማ ብለህ ስትለኩሰው ሰደድ ሆኖ የሚከሰት-
ባጥንት ክምር የሚረካ ባመድ ቁልል የሚደሰት;
Filed in: Amharic