>
5:13 pm - Thursday April 19, 9646

የታምራት መንገድ (አርአያ ተስፋማርያም)

የታምራት መንገድ
አርአያ ተስፋማርያም
ታምራት ከመታሰራቸው በፊት ሙስና እየፈፀሙ እንደሆነ ያጋላጡት ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝና ግሩም ተ/ሃይማኖት ታስረው በውሻ እየተነከሱ ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል። ይህንንም ዘግናኝ ድርጊት “ከደሙ ንፁህ” እንደማይሉ ነው
አቶ ታምራት ላይኔ ጉራጌ – ኢትዮጵያዊ ናቸው። ኢህአዴግ ተምቤን በሚገኝ ዋሻ ኮማንድ ፖስት ነበረው። ታጋዮችን በመምራት በዋሻው ወታደራዊ ትእዛዝ ይሰጡ የነበሩት ታምራት፣ ስዬና ተወልደ ነበሩ። ስልጣንም – በድርጅቱ ተሰሚነትም ነበራቸው። አቶ ታምራት ሙስና ፈፅመዋል! ከመንግስት ቡና ኮርፖሬሽን ጅቡቲ ድረስ የተወሰደ ቡና Red sea ለሚባል ካምፓኒ 5.5 ሚሊዮን ዶላር ተሸጠ።  በልጃቸው ብሌን ጌታቸው ስም 9.9 ሚሊዮን ዶላር በስዊዘርላንድ ሲቀመጥ፣ ይህ የገንዘብ ቁጥር ከፍ ያለው በአቶ ታምራት ስምና ፊርማ “ለኢትዮጵያ እዳ መክፈያ” በሚል ከሼክ አላሙዲ 16 ሚሊዮን ዶላር ወስደው ስለነበር ነው። አላሙዲ ለምስክርነት ሰቀርቡ በችሎት የተገኙ ጋዜጠኞች እንዲወጡ ተደርጓል።
 አላሙዲ በማስረጃ የተደገፈ ደብዳቤ ያቀረቡና ታምራት ገንዘብ ወስደው እንዳስቀሩባቸው የመሰከሩ ሲሆን የአላሙዲ ጠበቃ አቶ ተሾመ ገ/ማርያም ነበሩ። ስዊዘርላንድ የተቀመጠውን ገንዘብ ለማስመለስ በፍትህ ሚኒስትር ተወክሎ ጉዳዩን ይከታተል የነበረውAlemayehuZemedkun ነው። ከ3 አመት በፊት በታምራትና ሻእዲያ ስም የተቀመጠ 200 ሚሊዮን ብር ለፍትህ ሚ/ር ገቢ ተደርጓል። ይህ ገንዘብ ከስማይ የተሽመጠጠ ነው?..አሜሪካ የከፈቱት ጋዝ ስቴሽንና የሸመቱት መኖርያ ገንዘቡ ከየት የመጣ ነው?.. ታምራት ከመታሰራቸው በፊት ሙስና እየፈፀሙ እንደሆነ ያጋላጡት ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝና ግሩም ተ/ሃይማኖት ታስረው በውሻ እየተነከሱ ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል።
ይህንንም ዘግናኝ ድርጊት “ከደሙ ንፁህ” እንደማይሉ ነው። ብዙ ድርጊታቸውን በህይወት በሌሉ ባለስልጣናት ላይ ሲደፈድፉ ታዝበናል። ለሁለተኛ ግዜ ከስዬ ጋር ሲከሰሱ በፍ/ቤት ይናገሯቸው የነበሩትን ተከታትለናል። ታምራት ችሎት ሲቀርቡ ፅሁፎች ያቀብሉኝ ነበር። በምኒልክና አስኳል ጋዜጦች ላይ ስማቸው ሳይገለፅ “ከቀድሞ የኢህአዴግ ባለስልጣን” በሚል ይታተም ነበር። ፅሁፋቸው ጥልቅና ብስለት ነበረው።
ፍ/ቤትም እያለቀሱ በማረሚያ ቤቱ ሃላፊ በጥፊ መመታታቸውን ሲናገሩ (ከዚህ ቀደም የታምራት ጥፊ በሚል ፅፌዋለሁ) እንዲሁም ያስፈራሯቸው የነበሩት 4 ባለስልጣናትና አንድ ጄኔራል እንደሆኑ ሲገልፁ..አሁን የሚናገሩትን የመለስ፣ የክንፈና የመስፍን ግርማ (አቃቤ ህግ) አንድም ቀን ተናግረው አያውቁም። ታምራት በችሎት ሲያለቅሱ እንዲህ ሲሉ ተናዘዋል፤ “ምስራቅ ወርጄ ሽርጣም ሱማሌ ይልህ የነበረው ነፍጠኛ አማራ ልኩን አሳየው..ብዬ የአማራ ተወላጆችን ማስገደሌ ትልቅ ፀፀት ይሰማኛል! እናንተ ጋዜጠኞች ይህን የፀፀት ይቅርታ ቃሌን ለህዝብ አድርሱልኝ” ሲሉ እዛው ችሎት ነበርን። በጋዜጦች ላይም ፃፍን። 
ይህ ቃልና አጠቃላይ የችሎት ክርክሩ በድምፅ ሪከርድ ሆኖ ለታሪክ ተሰንዷል። ይቅርታ መልካም ነገር ነው! ታምራት ይቅርታ መጠየቃቸው የሚደገፍ ቢሆንም ነገር ግን ሁሉን በመሸምጠጥ መሆን የለበትም! ታምራትም ሆኑ ኢህአዴግ በሺህ የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች እንዲገድሉ አድርገዋል። ኦነግም ይህን ፈፅሟል። መሪዎቹ ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል! በኦሮሚያ እስር ቤቶች በማስፋፋት በክልሉ ተወላጆች ላይ ግፍ ተፈፅሟል። በትግሉ ዘመን ህወሀት “ፊውዳል ናችሁ” በሚል ቢሺህ የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ግድያ መፈፀሙን በ1997 አረጋዊ በርሄ ተናግረዋል። ያለፈን ቁስል እንዲሽር ተበዳዮችና የሟች ቤተሰቦች ይቅርታ ሊጠየቁና ካሳ ለሚገባቸው ይህ ተፈፃሚ እንዲሆን መደረግ አለበት! ተጨማሪ የምትሉትን ሀሳብ ስጡበት…
Filed in: Amharic