>
5:14 pm - Thursday April 20, 9167

ለማ መገርሳ  እና ፖል ካጋሜ በጨረፍታ (ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ)

ለማ መገርሳ  እና ፖል ካጋሜ በጨረፍታ

ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ

ከኮተቤ ሜትሮፖሊን ዩኒቨርስቲ

ሩዋንዳ በምሰራቅ አፍሪካ የምትገኝ ትንሽ አገር ስትሆን በ1994 እንደ አ.አ ከደረሰበት የሁቱና ቱትስ  እልቂት አገግማ ዛሬ ሰላማዊ አገር ሆናለች፡፡ የሩዋንዳ የዘር ፍጅት የሰው ልጅ አረሚያዊ ማነቱን ያሳየበት አንዱ የታሪክ ክስተት ነበር፡፡ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች  ሁቱና ቱትስ በዘውግ ተቧድነው አንድ ሚሊዮን ገደማ የሚደርሱ ዜጎቻቸውን ያጡበት ክስተት ዋናው ምክንያት የዘርን ጥላቻ በሚሰብኩ የፖለቲካ ሊህቃን ምክንያት ነው፡፡

በሩዋንዳ በ1994 ከተፈጸመው የዘር ፍጅት በፊት የሩዋዳ ዜጎች በቋንቋ አንድ ቢሆኑም በብሔር ተከፋፍለው  በዘውግ መታወቂያ ደብተር ላይ ቱትሲ፣ ሁቱ እና ትዋ በሚል የዘር መታወቂያ ካርዶች ልዩነታቸው ገዝፎ ነበር፡፡ ጭካኔ በተሞላበት የዘር ፍጅት መታወቂያቸው ላይ የተጻፈው የብሔር ማንነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ ከዘር ፍጅቱ በኋላ የፖል ካጋሜ ስልጣን መያዝ ተከትሎ የብሔርና እና የኃይማኖት ማነትን የሚገልጽ ስያሜ በመታወቂያቸው ላይ እንደዳይሰፍር ተደረገ፡፡ ዛሬ በሩዋዳ ውስጥ ቱቲስ እና ሁቱ የሚል መከፋፈል እንደነውር የሚቆጠር ሆኗል፡፡ ዜጎች በችሎታቸው ብቻ የሚለኩበት ስርዓት በመፈጠሩ ፖል ካጋሜ ሀገሪቱን እያዘመናት ይገኛል፡፡

ከሩዋንዳ የዘር ፍጅት ትምህርት የቀሰሙት እንደ ታንዛንያ ያሉ ሀገራት በዜጎቻቸው መታወቂያ ላይ ምንም ዓይነት የኃይማኖትና የብሔረ ማንነትና የሚገልጽ ቃላት እንደይኖሩ በማድረግ ከ120 በላይ ያሉ ብሔሮች በሰላም ለማስተዳደር ችለዋል፡፡

የህወኃት ወራሹ ስርዓት በ1983 ስልጣን ከጋዛ በኋላ የብሔር ጥላቻን የሚፈጥሩ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ፣ በብሔር ስም ህዝቡን በመከፋፈል በርካታ የጎሳ ግጭት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል፡፡ ዘረኞች መሰረተ-ቢስ በሆነ ጥላቻና በራስ ወዳድ ማነታቸው ምክንያት ህዝቡን በዘር እያቧደኑ በሚፈጠረው ግጭት የስልጣን እድሚያቸውን ለማራዘም ብዙ ጥረዋል፡፡ ይህም ይሳካላቸው ዘንድ በመታወቂያቸው ላይ የብሔር እና የኃይማኖት ማንነታቸንን በግዴታ ጭነውብን ለ27 ዓመታት ለጎሪጥ ስንተያይ፣ ስንጋጭ፣ ስንጋደል፣ ስንሰደድ ቆይተናል፡፡

ፖል ካጋሜ በሩዋንዳ ላይ ከተፈጠረው እልቂት ተምሮ ከዘር ፍጅቱ በፊት የነበረውን የብሔር ማንነት አጥፍቶ አንድነት የሰፈነባት ሩዋንዳን ሲመሰረት ብልሁ፣ ወጣቱ መሪ ለማ መገርሳ ደግሞ ያንዣበበውን የብሔር ግጭት ተረድቶ የዘር ፍጅቱን በማስቀረት አገሪቱን ከዶ/ር አብይ አህመድ ጋር ሊታደጓት እየታተሩ ነው፡፡

አሁን ለሚታየው የለውጥ ሂደት ጠንሳሽ እና ፊታውራሪ የሆነው የቁርጥ ቀን ኢትዮጵያዊ  ለማ መገርሳ በአገሪቱ ያንዣበበውን አደጋ በመረዳት በሚወስዳቸው እርምጃዎች ሀገሪቱን እየታደጋት ይገኛል፡፡ ለማ መገርሳ  ከወሰዳቸው በርካታ እርምጃዎች አንዱ የብሔር ማንነትን በዜጎች መታወቂያ ላይ ፍቆ በኢትዮጵያ ዜግነት መተካቱ ነው፡፡የቆራጥ መሪያችንን የለማ መገርሳን አርያን በመከተከል ለሌሎችም የክልል ርእሰ-መስተዳደር ከዜጎቻቸውን መታወቂያ ላይ ከብሔር ማንነት ይልቅ ኢትዮጵያዊነት በማስፈር በአንድነታችን ጉዞ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የህወኃት ወራሹ ስርዓት ባለሟልና ተቆርቋሪ ነን የሚሉ የሰርኣቱ አጋፋሪዎች ከጎሳ ድርጅት ይልቅ በአስተሳሰብ ልዩነትን ያማከለ የፖለቲካ ድርጅት መሰረት ላይ ማንነታቸውን እንዲገነቡ እና የጎሳ ፖለቲካ እና የብሔር ቡድነኝነት ከአንድነት ይልቅ መለያየትን፣ ከመተማመነን ይልቅ መጠራጠርን ከሰላም ይልቅ ግጭትን፣ ከፍቅረ ይልቅ ጸብን የሚያራግብ እንደሆነ ከበቂው የታሪክ መዛግብት ትምህርት ቢቀስሙ መልካም ነው ፡፡      

 

Filed in: Amharic