>
5:13 pm - Saturday April 18, 8308

አረቦቹ ድንገት "ፍቅራችሁ ሊገለን ነው" ብለው ተጠመጠሙብን እኮ ነገሩ እንዴት? (ሰይድ የሱፍ አሊ)

አረቦቹ ድንገት “ፍቅራችሁ ሊገለን ነው” ብለው ተጠመጠሙብን እኮ ነገሩ እንዴት?
ሰይድ የሱፍ አሊ
የአሰብ ወደብ ኪራይ ለዩናይተድ አረብ ኢምሬት
 የተባበሩት አረብ ኢምሬት የኤርትራውን አሰብ ወደብ ለ30 አመት የወታደራዊ ቤዝነት መከራየቷን Beirut based Arabic TV channel, Al-mayadeen  በመዘገቡ ምስራቅ አፍሪካ ላይ ምን እየሆነ ነው በሚል አገራቱን ስጋትና ጥርጣሬ ላይ እንደጣለ ይታወቃል፡፡
ኤርትራም አልሸጥኩም  ብላ ለማስተባበል ሞክራ ነበር፡፡ ኢምሬት ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትራችን ዶ/ አብይ  ጋር እፍፍ ያለ ፍቅር ይዛለች፡፡ከኤርትራም ጋር እንድንታረቅ ከፍተኛውን ሚና ተጫውታ ኢሱ..ኢሱ አስብላናለች፡፡ቀጥለውም ለታመመው ኢኮኖሚያችን  ምንም ሳንሰጣቸው 3 ቢሊዮን ዶላር ሰጡንና ልባችንን ቀጥ ሊያደርጉት ደረሱ፡፡ መድሃኒት መግዣ እስከማጣት የደረሰች ሀገራችን ትንሽ ተንፈስ እንድትል አደረጓት፡፡ ግን እንዲህ በብላሽ ዶላር ማስታቀፍ ምን የሚሉት ነው? እያልን አረቦቹን ስንጠራጠር በመንግስት ቴሌቭዥን አህመድ ሸዴ ብቅ ብለው የሪልስቴትና የሆቴሎች ግንባታ ምናምን ኢንቨስት ማድረግ ስለሚፈልጉ ወዘተ አሉን፡፡እሺ ይሁን ብለን እንዲሁ እየተጠራጠርን ዝም አልን፡፡ዛሬ ደግሞ ሪም የተባሉትን የኤምሬት ባለስልጣን ጠቅላያችን አገኟቸው የሚል ዜና ሰማን፡፡ከዜናው ጋር የቀረበልን ደግሞ ዩናይትድ አረብ ኢምሬት ከአሰብ እስከ አዲስ አበባ የነዳጅ መስመር ግንባታ ለማድረግ ማሰቧን አበሰሩን፡፡ ጥሩ ነው፡፡
በኛም በኩል የአሰብ ወደብን ኢትዮጳያ ለመጠቀም በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራ ነው፡፡እዚህም ላይ ኢምሬት ግፊት ይኖራታል፡፡ በአሰብ ወደብ መጠቀም በተለይ ለሰሜኑ የአገራችን ክፍል ቅርብ ከመሆኑም በላይ የጅቡቲን የዘወትር የወደብ ኪራይ ጫና የሚያስተነፍስ በመሆኑ ሸጋ ቢሆንም መጠቀም ስንጀምር ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያለባት አገራችን ከፍተኛ  ኪራይ ለዩናይትድ አረብ ኢምሬት ትከፍላለች፡፡ምክነያቱም ወደቡ ቢያንስ ለሚቀጥሉት 25 ዓመታት የኢምሬት ነው፡፡እንግዲህ በሚዘረጉት የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦም ነዳጅ ያቀርቡልናል፡፡እንገዛለን፡፡ኤምሬት የወረወረችልንን ቢሎዮን ዶላር በአጭር ወራት በእጥፍ ትወስዳለች ማለት ነው፡፡ከዚያም የኤርትራው  የወደብ ኪራይ ውል እስኪጠናቀቅ ኢትዮጵያ የማትነጥፍ የኢኮኖሚ ምንጭ ሆና ትቀጥላለች ማለት ነው፡፡በዚያውም ማቆሚያው መቼ እንደሆነ ግራ ያጋባቸውን የገቡበት የየመን ሁቲ አማጽያን ጋር የሚያደርጉትን ጦርነት መቆጣጠሪያና የቀይ ባህርን ቀጠና ደህንነትን ነዳጅ የጫኑ መርከቦቻቸው ጉዞ እንዳይስተጓጎል ይቆጣጠሩበታል፡፡የወደቡ ኪራይም በየመን ለሚያደርጉት ጦርነት የተወሰነውን ወጭ ይሸከምላቸዋል፡፡ አሰብ ወደብ ያለምንም ጥቅም ሳር ከሚበቅልበት ኢትዮጵያም ኢምሬትም ቢጠቀሙበት አይከፋም፡፡እናም አረቦቹ ድንገት ፍቅራችሁ ሊገለን ነው ብለው ሲጠመጠሙብን ነገሮችን እንዲህ አድርገን እየገጣጠምን ለመረዳት እንሞክራለን፡፡
Filed in: Amharic