>

ፍቅር እንዲያሸንፍ ከራስ መውጣት ያስፈልጋል (ዶ/ር ዘላለም እሸቴ)

ፍቅር እንዲያሸንፍ ከራስ መውጣት ያስፈልጋል

ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

አዲስ የኦሮምያ ካርታ ማውጣት የጊዜው መልስ ነውን?

ፍቅር እንዲያሸንፍ ክርስቶስ ሰማይን ትቶ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ።  ያለዋጋ ፍቅር ሊያሸንፍ አይችልም። ስለዚህ ፍቅር በምድራችን እንዲያሸንፍ፤ ሁላችንም ከቡድንተኝነት አስተሳሰብ ወጥተን፤ ለጋራ ኢትዮጵያዊነት ልዕልና መኖር እንድንችል መያያዝ መቻል አለብን።

ስንኖር ኢትዮጵያዊ፤ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን የተባለው ትልቅ አባባል ነው።  ስንኖር ኢትዮጵያዊ ነን ከማለታችን በፊት ግን ለግላዊ ቡድንተኝነት መሞት ያስፈልገናል።  ኢትዮጵያዊነትን ለመኖር ከፈለግን፤ ከተከፋፈልንበት አጥር ወጥተን መያያዝ መቻል የግድ ይላል።  ያለበለዚያ ኢትዮጵያዊነትን በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ ብቻ የምናወራው ነገር እንጂ፤ የምንኖረው የሕይወት ዘይቤ ሊሆን አይችልም።

ዶ/ር አብይ ያለ ጊዜያቸው የተከሰቱ መሪ ሳይሆኑ አይቀሩም ብዬ እፈራለሁ።  ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ዛሬ ላይ ተገኝተው ለኢትዮጵያዊነት መሞገት ብቻ ሳይሆን፤ ነገን አሻግረው አይተው አንድ አፍሪካን ሲሰብኩ፤ በሌላ በኩል ብዙ መሪዎች ትላንትና ላይ ተቸክለውና በጎሣ አጥራቸው ተገድበው፥ ከንግግር ያለፈና በተግባር ላይ የተመሰረተ መደመርና መሻገር ላይ ሲልቁ አይታዩም።

መሪዎችን ሁሉ ጨምሮ ሕዝበ ኢትዮጵያ ሰማያዊ ጥበብ ከመቸውም ጊዜ የበለጠ ያስፈልገናል።  የምስራችን ብስራት ሰማን እንጂ በምስራች ውስጥ ለመገለጥ ብዙ ፈተና በፊታችን ተደቅኗል። በለመድነው አካሄድ መሄድ መሰናከል ካልሆነ በቀር ለድል አያበቃንም።

በእውነት ከራሳችን ወጥተን፤ በፍቅር ለጋራ ኢትዮጵያዊነት እሴት መኖርን ዋና ነገር ለማድረግ እንንቃ። ዶ/ር አብይ እንዳሉ ስንደመር ከ “እኔና” ከ “አንተ” ወጥተን፤ ወደ “እኛ” እንሻገራለን። ለራሳችን ስንሞት የምንጎዳ ይመስላል፤ ግን በ “እኛ” ውስጥ የምናገኘው በረከት ከ “እኔነት” ከምናገኘው እጅግ በብዙ ይበልጣል።  ይህ የፍቅር ህግ ነው። ያኔ የፍቅር አሸናፊነት ዕውን ሆኖ በምድራችን ይታያል። ኢትዮጵያም በፈጣሪ ስር ያለች አንድ ቤተሰብ እንደሆነች ዕሙን ይሆናል።

 

ጊዜው የሚጠይቀው ስለ ጎሣችን ካርታ ለመሳል የምሽቀዳደምበት ሳይሆን፤ ዲሞክራሲ እንዲወለድ ሁሉም የኢትዮጵያ ነፃ አውጭ መሆን ነው።  ይህንን ባለማስተዋል ዕድሉ ካመለጠን፤ ይቅርታ የሌለው ሃጢያት እንደ መስራት ይቆጠራል።

ለሁላችንም ቅን ልቦና ይስጠን!

የፀሐፊው አድራሻ፥  myEthiopia.com

Filed in: Amharic