>

ሺህ በርጫ ከኋላው ሺህ በርጫ ከፊቱ .. (ዘውድአለም ታደሠ)

ሺህ በርጫ ከኋላው ሺህ በርጫ ከፊቱ ..
ዘውድአለም ታደሠ
ሰላም ሰላም ክቡራትና ክቡራን! ፒስ ነው ወይ? ሰሞኑን ጮማ ጮማ ወሬ ስላለ የቱን አውርቼ የቱን እንደምይዝ አይናዋጅ ሆኖብኛል ። የምር እንዲህ በወሬ ቡፌ ተጨናንቄ አላውቅም። ለማንኛውም የለት ወሬያችንን ለሚሰጠን ሰባተኛው ንጉሳችንና ለጓዶቹ ዝቅ ብዬ እጅ እነሳለሁ 🙂 እነአብይ ባይኖሩ ይሄኔ ወሪያችን ሁሉ እንደዲሲ ግበረሃይል “ሼም ኦን ዩ” ይሆን ነበር።
እኔ ምለው አዲሱ ከንቲባ አዲስ አበቤው መታወቂያ ላይ ብሔር እንዳይፃፍ ሊያደርጉ ነው የተባለው እውነት ነው ወይ? ከሆነ የኛ ቤተሰብ ውሳኔውን እንደማይቀበል ከወዲሁ ላረጋግጥላቸው እወዳለሁ። ቆይ እሳቸው እኛ አዲስ ብሔር ልንመሰርት ስንል ነው እንዴ እንዲህ አይነት ውሳኔ እኛን ሳያማክሩ ሚወስኑት? ይሄማ በማንነታችን ላይ የተቃጣ ተግባር ነው። እንዴ ምን ነካዎት ኦቦ ታከለ? በርስዎ ላይ ሰንት ተስፋ አድርገን እንዴት እንዲህ ብሔር አልባ ያደርጉናል? እኛኮ እቺን ወደርስዎ ቢሮ የመራናት ካርታ ከፀደቀችልን ብለን ባንዲራ አሰርተን፣ ህገመንግስት አርቅቀን ክልል በመሆን በቤተሰባችን ውስጥ በሰፊው የሚነገረውን የ አግግጵ ቋንቋ የፌደራሉ የስራ ቋንቋ አስደርገን ለመኖር እያሟሟቅን ነው። ቆይ በጀት እንዳንጋራዎት ነው እንዴ ብሔረሰብ የመመስረት መብታችንን ሚጋፉት? አረ ኦቦ ታከለ የምር አይነፋም!! ባይሆን እኛ ክልል ከሆንን በኋላ ውሳኔዎትን ሊያስተላልፉ ይችላሉ እስከዚያው ግን አግግጵ ለተባለው ብሔራችን እውቅና እንዲሰጠን አበክረን እንጠይቃለን። ከዚህ በመቀጠል ግን ስለአግግጵ ብሔረሰብ አመጣጥ በአጭሩ አስረዳለሁ …
የመጀመሪያው የአግግጵ ብሔረሰብ መስራች የሆነው ቅም አያቴ ከማዳጋስካር ሚስቱንና አረንጓዴ ፈረሱን ይዞ ወደአዲሳባ ቄራ አካባቢ ከሶስት መቶ አመት በፊት ፈለሰ … ቅም አያቴ ቀን በእርሻ ስራ ማታ በአልጋ ሴራ ሲተጋ ቆይቶ አስራሰባት ልጆችና መቶ ሰላሳ የልጅ ልጆችን አይቶ ባጭሩ ራሱን በመቶ አርባ ሰባት አባዝቶ በመቶ ሃያ አመቱ ተቀጨ። ምፅ (ደግ አይበረክትም ይላሉ የአግግጵ አበው)
በዚህ ሁኔታ የኛ ብሔረሰብ ባህልና ቋንቋውን እንዲሁም ጤናውን ጠብቆ ሲኖር ሲኖር ሲኖር አፄ ሚኒሊክ የተለያዩ ብሔረሰብ አባላትን አምጥተው በዙሪያችን አሰፈሩ። የምኒሊክ ሰፋሪዎችም ቀስ በቀስ መሬታችንን ወሰዱት። አያቶቻችን ግን ታጋሾች ነበሩና ዝም አሉ። ቀስ እያሉ እኚህ የምኒሊክ ሰፋሪዎች ቋንቋና ባህላችንንም ዋጡት (ይሄን ስፅፍ ራሱ እንባዬ በሁለት ቆንጮቼ እየተንዠቀዠቀ ነው)
ደርግ መጥቶ ደግሞ “አቢዮቷንኳ እንዲህ ሰፊ መሬት የላትም” ብሎ ሁለት ክፍል ቤት አስቀርቶልን መሬታችንን ነጥቆ ለደርግ ሰፋሪዎች ሰጣቸው።
እና ክቡር ከንቲባዬ …ኢህአዴግም ደርግን በቴስታ ብለ ስልጣኑን ሲይዝ ቦርድ ለወጣ አንድ ወታደሩ የቀረችንን አንዲት ክፍል ቤት ሰጠብን። ክቡር ከንቲባዬ… በዚሁ ከቀጠልን የኛ ብሔረሰብ እንደዳይኖሰር ከምድረ ገፅ የመጥፋት አደጋ ተጋርጦብናል የሚል ስጋት አድሮብናል።
አሁን ዙሪያችን በምኒሊክ በደርግ ና በኢህአዴግ ሰፋሪዎች ተከብቦ እየኖርን ነው።
ከንግዲህ ግን ክቡር ከንቲባዬ .. በእርስዎና በመንግስትዎ ተስፋ አድርገን ታሪካዊቷ የአግግጵ ብሔራችን እውቅና እንዲሰጡልንና ታሪካዊ መሬታችንን ከነዚህ የሶስት መንግስት ሰፋሪዎች ነጥቀው እንዲሰጡን ተስፋ አድርገናል። ለጥያቄያችን ይህን ፅሁፍ ባነበቡ በሶስት ሰአት ውስጥ መልስ ካልሰጡ ግን የኛ ብሔረሰብ ለዘመናት ባካበተው የውጊያ ጥበብ ተጠቅሞ የራሱን እድል በራሱ እንደሚወስን ላስጠነቅቆ እወዳለሁ። ስላዳመጡኝ በአግግጵ ቋንቋ “ጮምጶጥያኢጊጊንቆፅ ህስጦን” በማለት አመሰግናለሁ።
እና እንዴት ናችሁ ጓዶች? የሐገራችን ነገርኮ ከላይ እንደገለፅኩት ሆነ!
እሺ አሁን ወደዋናው ነጥብ እንግባና (እኔ ደግሞ እንደልደቱ አያሌው ነጥብ ምናምን ማለት እወዳለሁ) እና ወደዋናው ነጥብ ስንመጣ አብዲ ኢሌ የሚሉት ነጥብ መጨረሻው ምን ሆነ? የሚለውን ነጥብ ነጥብ በነጥብ የሚያስቀምጥልን ሰው ጠፋ ማለት ነው?
እስካሁን እዚህ ፌስቡክ ላይ ስዩም ተሾመ ብቻ ነው “ምንጮቼ ነገሩኝ፣ ምንጮቼ ላኩልኝ፣ ምንጮቼ ሹክ አሉኝ” እያለ አንዴ ታስሯል፣ አንዴ ተፈቷል፣ አንዴ ፈርጥጧል ፣ እያለ በነፍሳችን ሚጫወተው። (ስዩሜኮ እያየነው ተንቀሳቃሽ አርባምንጭ ሆነ ጓዶች  🙂 )
አረ በፈጠራችሁ የአብዲ ኢሌ መጨረሻ ምን ሆነ? ቆይ እኛ የሱን መጨረሻ ለመስማት እስራኤል ዳንሳ ጋር መሄድ አለብን እንዴ? ለነገሩ እስራኤልን ስለአብዲ ኢሌ ብንጠይቀው “ጌታን ተቀብሎ ነቢይ ይሆናል” ነው ሚለን። ያ ጥበቡ ወርቅዬም እግዜር ስለሚሞቱ ሰዎች ብቻ ነው ሚነግረው። ችግር ሆነኮ!
እኔ እስካሁን ስለአብዲ ኢሌ ከሰማኋቸው መረጃዎች አሳማኝ ሆኖ ያገኘሁት «አብዲ ከፌደራል መንግስቱ ጋር እየተደራደረ ነው» የሚለው ነው።
አብዲ ለመታሰር ተስማምቶ ነገር ግን እስር ቤት ውስጥ በየቀኑ ሶስት ዙርባ ጫትና ሺሻ ከሱማሊያ በጀት ላይ ተቀንሶ እንዲቀርብለት ጠይቋል። ሃይለኛ የስልጣን ሱስ ስላለበትም ከበርጫው በተጨማሪ የማረሚያ ቤቱ የእስረኞች ሊቀመንበር፣ የምግብ አቅርቦት ጠቅላይ ሃላፊና የፅዳትና ግርፋት ዋና ኢታማዦር ሹም እንዲሆን ጠይቋል ይባላል። ዶክተር አብይም ጥያቄውን ተመልክተው ጌታ ጫትና ሺሻን ስለማይወድ ወይ እንደታምራት ላይኔ ጌታን እንዲቀበል አሊያም ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት አስቸኳይ እርምጃ ወስዶ ኢትዮጵያ እንዲያደርገው አዘዙ። አብዲ ኢሌም ውሳኔውን ሰምቶ እንደአፄ ቴዎድሮስ እንዲህ አለ …
እጅህን ስጥ አለኝ አብይ
እጅ ተይዞ ሊወሰድ
ነዳጁን አወድማለሁ በሳት ሰደድ
አያውቅም ክንዴ እንደሚያነድ?
ብሎ ጥይቱን በጀግንነት ጠጣ! ችግሩ ጥይቱን የውሃ ብርጭቆ ውስጥ አርጎ ስለጠጣው ሊሞት አልቻለም። 🙂 የአብዲ ኢሌን ሁኔታ ያየች አንዲት ሱማሌም
“ሺህ በርጫ ከኋላ ሺህ በርጫ ከፊቱ
ይህን ሳታይ ሞተች ያቺ ክፉ አማቱ” ብላ ገጠመች።
ኤኒ ሃው አብዲ ባሁኑ ሰአት ለዚህ ያበቃው ጌታቸው አሰፋን እየረገመ ቤተመንግስት ውስጥ ፈርሾ እየቃመ ነው። አብዲ ሲመረቅን እጁን ይሰጥ ይሆን? እሱን ወደፊት አብረን የምናየው ይሆናል!
Filed in: Amharic