>

እናሸጋግራችኋለን (ከይኄይስ እውነቱ)

እናሸጋግራችኋለን

ከይኄይስ እውነቱ

ሥልጣን ላይ ያለው ‹‹የጎሣ ፓርቲዎች ግንባር›› እንዴት ነው የሚያሸጋግረን?

የጠ/ሚኒስትሩ ዋና ትኩረት በወያኔ ግንባር ድርጅት ዕቅድ መሠረት ከሁለት ዓመት በኋላ የሚደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ እንደሆነ÷ ምርጫውንም ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ ነፃና ሚዛናዊ ምርጫ ማድረግ በገለልተኛ ተቋማት ቢታገዝም እንኳን በራሱ ግብ አይደለም፤ የዴሞክራሲ አንድ መገለጫ እንጂ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሥፈኑ ዋስትና  አይደለም፡፡ ሌላው ነፃና ሚዛናዊ ምርጫ እንዲኖር የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን በሚመለከት ጠ/ሚሩ በይፋ ለሕዝብ ያሳወቁት ጥቅልም ሆነ ዝርዝር ጉዳዮች የሉም፡፡ አንዳንድ ማሻሻያዎች (reforms) ለምሳሌ ‹‹የይስሙላ ሕገ መንግሥቱን›› እና ሌሎች አፋኝ ሕጎችን በሚመለከት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የኔ አቋም ይህ የይስሙላ ሰነድ ሙሉ ለሙሉ መለወጥ አለበት ቢሆንም፣ ለመሆኑ የአሁኑ ማሻሻያ የማስመሰያው ‹ሕገ መንግሥት› ስለሚሻሻልበት የሚደነግገውን አንቀጽ 105ን ይጨምራል ወይ? በምርጫው አሸናፊ የሚሆነው ፓርቲ ሀገር-አቀፍም ይሁን የጎሣ የይስሙላውን ‹ሕገ መንግሥት› ሙሉ ለሙሉ ለመለወጥ ወይም ለማሻሻል የሚያስችለው ቊልፍ ድንጋጌ ይህ የተጠቀሰው ድንጋጌ በመሆኑ ማሻሻያው ውስጥ መካተቱ ወሳኝ ነው፡፡

በእስካሁኑ ሂደት በማሻሻያው መርሐ ግብር ጠ/ሚሩ ወይም የሚመሩት ግንባር ከመረጧቸው ግለሰቦች ውጭ ከአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ከሚገኙ ምሁራን እንዲሁም ተቃዋሚ የፖለቲካ ማኅበራትና የማኅበረሰብ ድርጅቶች የተወከሉ ግለሰቦች መኖራቸውን አልሰማንም፡፡ አቶ ለማንና ጠ/ሚሩን ማመን/መቀበል እርሳቸው የሚመሩትን ‹ግንባር› መቀበል ማለት አይደለም፡፡ ግንባሩ በብቃትም÷በቅንነትም ሆነ በሞራል ልዕልና ረገድ በጭራሽ የሚታመን የኋላ ታሪክ (track record) የለውም፡፡ ባንዳንዶች ዘንድ ጊዜውን ለመምሰል የሚደረግ ማስመል እንጂ ከላይ የሚፈስ ሃሳብ እስከነ ቆሻሻው ሲጋቱ የከረሙ ሰዎች ባንድ ጀምበር ይለወጣሉ ብሎ መጠበቅ ተላላነት ነው፡፡ ባጠቃላይ ነፃና ሚዛናዊ ምርጫ ለማካሄድና ለዚህ የሚሆነው መደላድል መሠረት ሊያደርግ የሚገባው ግለሰቦችን በማመን ወይም ባለማመን ሳይሆን ኹሉም የሚያምንባቸው ተቋማት ደረጃ በደረጃ ሲገነቡ ብቻ ነው፡፡ ግንባሩ እንደ ድርጅት ብቃት የለውም፡፡ ስለሆነም ከግንባሩ ውጭ ያሉ ሌሎች ኢትዮጵያኖችን ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡ ‹እናሻግራችኋለን› ሲባል የተረዳኹት አሳታፊነትን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ጠ/ሚሩ በዙሪያቸው ያሰባሰቡት ለውጡን የተቀበሉ ኃይሎችን ነው የሚል እምነት ካላቸው (ከወያኔ ትግሬ በስተቀር) እነዚህ ወገኖች ለምርጫው ተአማኒነትና ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እንዲሁም በተቋማት ግንባታው ሂደት ከግንባሩ ውጭ ለውጡን የሚደግፉ ኃይሎች መሳተፋቸውን በደስታ ሊቀበሉት ይገባል፡፡

በሌላ በኩል የምርጫ ፉክክሩ በጎሣ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ከሆነ ውጤቱ የተሻለ እምነት፣ የተሻለ አስተሳሰብ፣ የተሻለ ርዕይ በማቅረብ የሚደረግ ጤናማ ውድድር ሳይሆን፣ አንድ ጎሣ በሌላ ጎሣ ላይ የድል አድራጊነት ወይም የበላይነት የሚያሳይበት ለመሆኑ ከወዲሁ ከጥርጣሬ በላይ ለመናገር ይቻላል፡፡ የጎሣ ፖለቲካው ቀጣይነት ካለው (የጎሣ ፓርቲዎች የዚህ ፖለቲካ ውጤት ናቸውና) እንዴት አድርገን ነው ወደ ዴሞክራሲያው ሥርዓት ሽግግር እንደምናደርግ ልንናገር የምንችለው? የዴሞክራሲን ሚና በሚያዳክመውና በሚሸረሽረው የጎሣ ፖለቲካ ወደ ዴሞክራሲ መንገድ መሄድ በራሱ እንቆቅልሽ ነው የሚሆንብን፡፡  ምናልባትም አናሳ ጎሣን ከሚወክል ‹የጎሣፖለቲካ ድርጅት› የጭካኔና አፈና አገዛዝ የበላይነት (dominant minority tyranny)፤ ከፍተኛ ቊጥር ያለውን ጎሣ ወደሚወክል ‹የፖለቲካ ድርጅት› የጭካኔና አፈና አገዛዝ (tyranny of the majority) መሸጋገር እንዳይሆን ጠንከር ያለ ሥጋት አለኝ፡፡ እንደሚታወቀው ዴሞክራሲ (መንግሥተ ሕዝብ) የብዙኃን አስተዳደር ብቻ ሳይሆን የግለሰቦችና የአናሳ ቡድኖች መብቶችም የሚጠበቅበት የአስተዳደር ዘይቤ ነው፡፡ ይህንን ሥጋት መሠረት የሌለው አድርጎ መቊጠር ብልህነት አይመስለኝም፡፡ የብዙኃን የጭቆናና አፈና አገዛዝ (tyranny of the majority) እንኳን ከዘረኝነት ጋር ተያይዞ ከዚያም ውጭ በቀላሉ የማይታይ ሥጋት መሆኑን ከአገሮች ተሞክሮ በመነሳት በመስኩ ጥናት ያደረጉ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያም አብዛኛው በጎሣ የተደራጁ የፖለቲካ ቡድኖች (እንወክለዋለን የሚሉት ጎሣ/ነገድ ከፍተኛ ቊጥር ቢኖረውም እንኳ) የአገር አንድነት÷ የብሔራዊ ማንነት (ኢትዮጵያዊነት) ጉዳይ ሲነሳ ከብዙኃኑ ላለመለየት መስለው የመታየት እንጂ ጎጠኛ አጀንዳቸውን ባንቀልባ አዝለው የሚዞሩ ናቸው፡፡ ሎንዶን ላይ ኢትዮጵያ ትበታተን ሲሉ ያናፉትን ኦነጎችንና ተረፈ-ኦነጎችን የኢትዮጵያ ሕዝብ መቼም አይረሳቸውም፡፡ አሁንም ‹ጊዜው የእኛ ነው› በሚል ወደአገር ውስጥ የገቡትንም ሆነ ውጭ ሆነው ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉት ኹሉ ከአፍራሽ ዓላማቸው ጋር እንዳደፈጡ በሚገባ እናውቃለን፡፡ እስቲ ጠ/ሚሩ የሚመሩት ግንባር ከጎሣ ገለልተኛ በሆነ መልኩ አንድ ወጥ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ መሥርተው ለሌሎችም አብነት በመሆን ያሳዩን፡፡ ይህንን በማድረግ ለዜግነት ፖለቲካ ተግባራዊ መሠረት ማኖር ይችላሉ፡፡

አንዳንድ ምሁራን እና አስተያየት ሰጭዎች አሁን ምድር ላይ ባለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ መልክዐ ምድር መለያየትን መሠረት ያደረገው ‹የጎሣ ፌዴራል ሥርዓት› እና ጎሣን መሠረት ያደረጉ የፖለቲካ ቡድኖችን ማስቀረት አይቻልም የሚል ጽኑዕ እምነት እንዳላቸው፤ ይህንንም ለማስቀረት የሚደረግ ሙከራ የበለጠ ኹከትንና አለመረጋጋትን እንደሚፈጥር ይናገራሉ፡፡ በመሠረቱ ይህም አመለካከት መሠረት የሌለው አይደለም፡፡ የጥቂት ዘረኞች የወያኔ አገዛዝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም ዓይነት የአብሮነት ታሪክ÷ ምንም ዓይነት ዝምድና÷ ምንም ዓይነት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር እንደሌለው ቆጥሮ፣ ‹‹ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›› የሚባል  የማይጨበጥ ግዑዝ ጣዖት ጥርቅም አድርጎ በመለያየት/በመከፋፈል ላይ ላለፉት 27 ዓመታት አጥብቆ ሠርቷል፡፡ የፌዴራል ሥርዓት ዋና ትርጕሙ አብሮነት ሆኖ ሳለ፣ ኢትዮጵያን ‹አትድረሱብኝ› በሚልና ጎሣን መሠረት ባደረገ የ‹ክልል› አጥር ሸንሽኖ የአገራችንንም ሆነ የሕዝቧን አንድነት በእጅጉ አናግቷል፡፡ ቊጥሩ ቀላል የማይባል ሕዝብ ወያኔ የከለለትን ‹አጥር› የኢትዮጵያ ክፍል መሆኑ ቀርቶ በዛ የሠፈረው ጎሣ ብቸኛ ‹‹አገር›› እና ለሀብቱም ብቸኛ ባለቤት ሆኖ (በይስሙላ ‹የክልል ሕገ መንግሥት ጭምር አፅድቆ) ሌሎች ኢትዮጵያውያን ዜጎችን መግደል÷ማሰር÷ መዝረፍና ማፈናቀል የዕለት ተዕለት ተግባሩ ከማድረግ አልፎ የአገር ህልውናን እየተፈታተነ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ቢያንስ የዘራፊዎች መሣሪያ ሆኗል፡፤

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አንድ ጸሐፊ ከሥጋት በዘለለ እንደገለጹት በጎሣ ያልተደራጁ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች (አንዱን በስም ጠቅሰው፤ ምናልባትም ከተጠቀሰው ውጭ ጠንካራ የሚባል አለመኖሩንም የሚጠቁም ይመስላል) በምርጫው የሚኖራቸው ሚና ከአጃቢነት እንደማያልፍና በጎሣ የተደራጁት ድርጅቶች እንወክለዋለን ከሚሉት የጎሣ አባላት ድምፅ ከመሸራረፍ ያለፈ ፋይዳ እንደማይኖራቸው ገልጸው ይልቁንም ትኩረታቸውን የዴሞክራቲክ ተቋማት ግንባታ ላይ እንዲያደርጉ ይመክራሉ፡፡ የጎን መጎነታተልን የምጸየፍ ሰው ብሆንም የፖለቲካ ድርጅቶች የየራሳቸው ድክመት እንደሚኖራቸው ብገነዘብም፣ ይህ ዓይነቱ አስተያየት የግል ስሜት/ጥላቻ በጣም ያየለበት ይመስለኛል፡፡

አንድ የተገፋ ጎሣ/ነገድ ተደራጅቶ ራሱን ከግፈኞች ጥቃት የመከላከል/ህልውናውን የማስከበር መብቱን መናገር እና ጎሣውን መሠረት አድርጎ የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ መደራጀት የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በኔ የግል አመለካከት በዚህ በ21ኛው ክ/ዘመን ጎሣን መሠረት አድርጎ በፖለቲካ ከመደራጀት የላቀ ድንቁርና አለ ብዬ አላምንም፡፡ በሕግ እስካልተከለከለ ድረስ መብት ሊሆን ይችላል፡፡ የተፈቀደ ኹሉ ግን አይጠቅምም፡፡ ይህን የሚያደርግ ቡድንም ሆነ የሚደግፍ ግለሰብ ጎሠኞችን/መንደርተኞችን ለማውገዝ ምን ዓይነት የሞራል ብቃት አለው? እውነቱን እንነጋገር ከተባለ አንድ ግለሰብ የአንድ ጎሣ/ነገድ አባል መሆኑ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የዚያ ጎሣ/ነገድ ተወካይ ወይም ጥቅም አስከባሪ ያደርገዋል የሚለው ድምዳሜ እጅግ የተሳሳተ ይመስለኛል፡፡ ሥልጣንና ሥልጣንን ተገን አድርገው ለራሳቸውና በዙሪያቸው ለሚኮለኮሉ ዘመዶቻቸውና ሎሌዎቻቸው ጥቅም ለማስገኘት ካልሆነ አንድን ጎሣ/ነገድ እንወክላለን የሚሉ በርካታ ‹የፖለቲካ ድርጅቶች› ለምን ዓላማ ተቋቋሙ?

ከፍ ብሎ የተገለጸው ሥጋት ቢኖርም ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም እንደሚባለው የአገራችንና የሕዝባችንን ዕጣ ፈንታ እገሌ ይቀየማል፣ እገሌ ያኮርፋል፣ እገሌ ፈቃዱ ካልተፈጸመ ለዕልቂት ወደኋላ አይልም፣ አገር ይበትናል በሚል ሥጋትና አስተሳሰብ ዘላቂውን ለጊዜያዊው ልንሠዋ አይገባም፡፡ መዳረሻችን ነፃነት፣ እኩልነት፣ ማኅበራዊ ፍትሕና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት በዜግነት ላይ የሚመሠረት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከሆነ፣ መሠረቱን በያንዳንዱ ሂደት በዓለት ላይ እናዋቅረው፡፡ ታሪክ ተደጋጋሚ ዕድል አይሰጠንም፡፡ ወያኔ ትግሬ የፈጠረው ዕውነታ የፈለገውም ይሁን በመርህ ላይ የተመሠረተ አቋም ካለን እስከመጨረሻው መዝለቅ፣ (በተለይም ፖለቲከኞች ላልሆንን፣ የመሆንም ፍላጎት ለሌለን፣ ሥልጣንን ለምንጸየፍ) ለመርሁም ታማኝ ሆኖ መገኘት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ለሥልጣን እንደሚፎካከሩት የፖለቲካ ቡድኖች በየጊዜው የሚለዋወጥ አቋም ሊኖረን አይገባም፡፡

እኔ ዕትብቴ በኢትዮጵያ ምድር የተቀበረ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነኝ÷ከፍ ሲልም በአርዓያ ሥላሴና አምሳል የተፈጠርኩ የሰው ልጅ ከመሆኔ ውጭ ራሴን ከየትኛውም ጎሣ ጋር አያይዤ አላውቅም፤ በዚህ መልኩ ማየትም አልፈልግም፡፡ መታወቂያቸው ኢትዮጵያዊነት ብቻ የሆነ አእላፋት ዜጎች አሉ፡፡ በዜግነት ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ምድር ቦታ እስኪያገኝ አቅሜ የፈቀደውን ኹሉ አደርጋለኹ፡፡ ‹ደመናው› እስኪገፍ እንጂ የብዙኃኑ ኢትዮጵያዊ ፍላጎትም ይመስለኛል፡፡ የወያኔ ማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› ይህን አይፈቅድም፡፡ የዶ/ር ዐቢይ የማሻሻያ መርሐ ግብር ይህንን የሚጨምር ከሆነ ወደፊት የምናየው ነው፡፡ የአቶ ለማና ዶ/ር ዐቢይ ጅምር የለውጥ እንቅስቃሴ ኢትዮጵያዊነትና አገራዊ አንድነት እንዲንሠራራ በጎ አስተዋጽኦ ማድረጉ እንዳለ ሆኖ፣ የጎሣ ፓርቲዎች በፖለቲካው መድረክ መሠልጠናቸው አይካድም፡፡ ባንድ በኩል ጎሣን መሠረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ቡድኖች ወጣቱን በስሜት ለመንዳት የሚያደርጉት አፍራሽ ቅስቀሳ፣ በሌላ ወገን ወያኔ ለ27 ዓመታት የጎሣ ፖለቲካ ሥር እንዲሰድ ያደረገው ተጽእኖ ቀላል ባይሆንም አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎሣና ከነገድ የዘለለውን ኢትዮጵያዊ ዜግነት ቅድሚያ እንደሚሰጠውና በልቡ ጽላት ጽፎት እንዳኖረውም ደጋግሞ አረጋግጧል፡፡ ስለሆነም ከየትኛውም ጎሣ/ነገድ ያልወገነ ሀገረ አቀፍ  የፖለቲካ ማኅበር እንዲጠነክር ማበረታታት እንጂ ጊዜው ጎሣ ጎሣ የሚባልበት ነውና ለሥልጣን መወዳደራችሁ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል የሚለው አስተያየት በአመለካካትም ደረጃ ትክክል ካለመሆኑ በተጨማሪ ዜግነትን መሠረት በማድረግ ብቻ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄድ ምርጫ ውስጥ ድምፅ በመስጠት ለመሳተፍ የሚፈልጉ ዜጎችን በአገራቸው ጉዳይ የመሳተፍ መብታቸውን የሚያጣብብ ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ጠ/ሚሩ ወይም የሚመሩት ‹ግንባር› ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የማሸጋገሪያው መንገድ መጪው ምርጫ ብቻ እንደሆነ ለድርድር የማይቀርብ ሃሳብ ይዘዋል፡፡ በውኑ ይህ የግንባሩ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ነው ወይ? ከዚህ ውጭ አማራጭ ባለመኖሩ ነው ምሁራን ዝምታን የመረጡት ወይስ አሁንም የአገራችን ያለመረጋጋት ሥጋት ሌሎች አማራጮችን የማስተናገድ አቅም የለውም ከሚል እሳቤ?

በመጨረሻም እግረ መንገድ ለማንሳት በምፈልገው ጉዳይ አስተያየቴን እቋጫለሁ፡፡ በብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ ሆን ብሎ ለማደናገር ይሁን ወይም በብዥታ የተፈጠረ አመለካከት አስተውላለሁ፡፡ ወደድንም ጠላንም አንድ አገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትወከልበት  አንድ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ ይህ ሰንደቅ ዓለማ እንደ ሁኔታው በስምምነት ዓርማ ሊኖረው ወይም ላይኖረው ይችላል፡፡ አገሪቱ የምትከተለው ቅርፀ መንግሥት አሐዳዊም ይሁን ፌዴራላዊ የሚኖራት አንድ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ነው፡፡ በርግጥ በፌዴራል ሥርዓት አባል ግዛቶቹ የየራሳቸው መለያ ሰንደቅ ዓላማ ይኖራቸዋል፡፡ እነዚህ የግዛት ሰንደቅ ዓላማዎች ግን በየትኛውም ሁኔታ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማውን ተክተው አይውለበለቡም፡፡ የሚሰቀሉትም ከብሔራዊው ሰንደቅ ዓላማ ጎን ሆኖ በሕግ በሚወሰነው መጠን ዝቅ ብለው ነው፡፡ ይህም የአገሪቱ ሕዝብ በሙሉ የጋራ ሉዐላዊነትና ክብር መገለጫ ለሆነው ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በስምምነት የሚሰጥ ቀደምትነት ነው፡፡ ባንፃሩም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚያራምዱት ፍልስምና ወይም መርሐግብር አኳያ መለያ ዓርማ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በየትኛውም ሁኔታ የራሱ ሰንደቅ ዓላማ ሊኖረው አይችልም፡፡ ይዞም ከተገኘ ሕገ ወጥ ነው፡፡ ስለሆነም ወጣቶች እባካችሁ አገራችሁን የምትወዱ ከሆነ፣ ለሁላችንም ዕኩል እንድትሆን የምትፈልጉ ከሆነ፣ ከትርምስና ኹከት ወጥታ የነፃነት አየር በመተንፈስ ለግልና የጋራ ብልጽግና የምንሠራባት የጋራ ቤታችን እንድትሆን ከምር የምትመኙ ከሆነ፤ በስሜት መነዳቱን አቁመን በስክነትና በምክንያታዊነት÷በንግግርና በመደማመጥ ÷ ከእኛ በዕውቀትም በልምድም የተሻለ ሃሳብ ያላቸውን ምክር በመስማት አገራችንን እንድንታደግ አደራ እላችኋለሁ፡፡

Filed in: Amharic