>

ዐቃቤ ሕግ "ይፈታሉ" ያላቸውን የፖለቲካ እስረኞች ሊያስፈርድባቸው ነው! (በጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው)

ዐቃቤ ሕግ “ይፈታሉ” ያላቸውን የፖለቲካ እስረኞች ሊያስፈርድባቸው ነው!
በጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፖርላማው በወሰነው መሰረት በሽብር የተከሰሱትን ክስ እንደሚያቋርጥ መግለጫ መስጠቱ ይታወቃል። የተፈረደባቸው ደግሞ በምህረት አዋጁ መሰረት ይፈታሉ ተብሎ ነበር። ሁሉም ግን አልተፈቱም። ከ80 በላይ በአርበኞች ግንቦት 7 የተከሰሱ፣ እንዲሁም በኦነግ የተከሰሱ፣ በአጠቃላይ ከመቶ በላይ በአርበኞች ግንቦት 7 እና ኦነግ የተከሰሱ በእስር ላይ ይገኛሉ።
በአሁኑ ወቅት በርካታ ተከሳሾች ፍርድ ቤት እየተመላለሱ ነው። በእስር ላይ ይገኛሉ። እነ ገብሬ ንጉሴ ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር። በእነ ገብሬ ንጉሴ ክስ መዝገብ 14 ሰዎች ተከስሰው ነበር። 9ኙ “በክሱ ላይ የተጠቀሰውን ፈፅመናል” ብለው ስላመኑ እስከ 16 አመት ተፈረደባቸዋል። የተፈረደባቸው ከወር በፊት ሲፈቱ ገብሬ ንጉሴ፣ ጌትነት ዘሌ፣ ሻንቆ ብርሃኑ፣ ተሻገር መስፍን እና ሰጠኝ ጎባለ አሁንም በእስር ላይ ናቸው።
ያልተፈቱት “የአርበኞች ግንቦት 7 አባል ነን፣ ነገር ግን በክሱ ላይ ተፈፀመ የተባለውን አልሰራንም” ብለው በመከራከራቸው መከላከያ ምስክር እንዲያመጡ ተቀጥሮባቸው ቂሊንጦ ቆይተዋል።
የተፈረደባቸው ሲፈቱ በአንድ መዝገብ ተከሰው ያልተፈረደባቸው ግን “የሰው ህይወት አጥፍታችኋል አትፈቱም” ተብለዋል። ዛሬ!
በተደረገው ጦርነት የሰው ህይወት መጥፋቱን አምነው “አድርገነዋል” ያሉት ተፈርዶባቸው ተፈትተዋል። በአንድ ክስ መዝገብ ተከሰው “አላደረግነውም” ያሉት ግን በእስር ላይ ይገኛሉ። ለነሃሴ 15/2010 ለውሳኔ ተቀጥረዋል።
በተመሳሳይ በማዕከላዊ ብዙ ስቃይ የተፈፀመበት አስቻለው ደሴም ለነሃሴ 15 ቀጠሮ ተሰጥቶበታል።
ዐቃቤ ሕግ ክሳቸው ተነስቶ እንዲሁም በምህረት አዋጁ ይፈታሉ ቢልም ይህን መግለጫ የሰጠው ዐቃቤ ሕግ “አትፈቱም” እያለ ቀጠሮ እያሰጠባቸው ይገኛል! ጌታነህ አቡሃይ የምህረት አዋጁ አይመለከትህም ተብሎ ለጥቅምት 8/2011 ቀጠሮ ተሰጥቶበታል።
(ፎቶው የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት የነበሩትና ከኤርትራ የመጡት የሰጠኝ ጎባለ፣ ገብሬ ንጉሴ እና ሻንቆ ብርሃኑ ነው)
Filed in: Amharic