>

‹‹ኩሸት›› እና ‹‹እውነት›› በልሂቃኗ ኢትዮጵያ!  — የዶ/ር አብይ፣ የዶ/ር ነጋሶና የአቶ መለስ ቆሎዎች!!

‹‹ኩሸት›› እና ‹‹እውነት›› — በልሂቃኗ ኢትዮጵያ!
 አስፋ ሀይሉ
 — የዶ/ር አብይ፣ የዶ/ር ነጋሶና የአቶ መለስ ቆሎዎች!!
‹‹ኩሸት›› የሚባለው በስነፅሑፍ ‹‹ከእውነታው እጅግ የተራራቀ ግነት›› ማለት ነው፡፡ ግን ‹‹ኩሸት›› ከ‹‹ውሸት›› ይለያል፡፡ ለምሳሌ ‹‹የፍየሏ ቀንድ ከመርዘሙ የተነሣ ጣራውን ሊነካ ምንም አልቀረውም›› ብሎ መጻፍ — ወይም ‹‹በጀርባዋ ተዘናፍሎ ቁልቁል የተዘገራው ፀጉሯ ቁልቁል የሚወርደውን የአባይን ጅረት ያስንቃል›› ብሎ መጻፍ — ሁለቱም ‹‹ኩሸት›› ይባላሉ፡፡ ስዕሉን በተደራሲ ምናብ ለመከሰት ሲባል – (ለ ‹ቪቪድ ድራማቲክ ኢፌክት› ተብሎ) እጅግ የተጋነኑ ንፅፅሮች ናቸው፡፡ ግን ፈጽሞ ውሸት አይደሉም፡፡ የፍየሏ ቀንድ መርዘሙም፣ የልጂቱ ፀጉር መዘናፈሉም — ሁለቱም እውነተኛ መነሻዎች ናቸው፡፡ ውሸት አንላቸውም፡፡ ግነቶቹ ግን ኩሸት ናቸው፡፡
እና ባለፈው አንድ ይህን የ‹‹ኩሸት—እውነት›› ነገር እንዳስታውስ ያደረገኝን አንድ ቅንብር ፎቶ አጋጥሞኝ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ማህበራዊ ድረገጾችን ያጥለቀለቀው አስገራሚ ፎቶ — ትሁቱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን — ዶ/ር አብይ አህመድ — አስመራ ላይ — በፕሬዚደንት ኢሣያስ ቤት ይመስለኛል — በክብር እንግድነት ከተቀመጠበት ሥፍራ ተነስቶ — ለእንግዶች የቡና ቁርስ ሲያዘግን የሚታይበት ልብ የሚነካ የጨዋ ተግባሩን ለዓለም የሚያሳይ ፎቶ ግራፍ ነበር፡፡ ያን ፎቶ ተከትሎ ግን — ማኅበራዊ ሚዲያውን ያጥለቀለቀ ሌላ ቅንብር ፎቶግራፍ መጣረ፡፡
ብዙዎቻችን እንደምናስታውሰው — ያ ቅንብር ፎቶ — በሁለት ዓይነት ‹‹ቨርዥኖች›› ነበር የተለቀቀው፡፡ አንደኛው ቅንብር ላይ — በአንድ በኩል ዶ/ር አብይ አህመድ — የቡና ቁርስ የሞላባትን ስፌት ይዘው — ለሰዉ አጎንብሰው ሲያዘግኑ ይታያል፡፡ በቅንብሩ ላይ ግን አንድ ሌላም ቆሎ የሚያዘግን ሰው ከጎኑ ተጨምሮበታል፡፡ በዚህኛው ፎቶ — የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (ለገሠ ዜናዊ) — በተመሣሣይ የአብይ ስፌት እንግዳውን ጎንበስ ብለው ሲያዘግኑ ይታያል፡፡ አቶ መለስ — የሚያዘግኑት ግን የቡና ቁርስ ሳይሆን — የጥይት ክምር ነው፡፡ ገረመኝ በጣም!!!
ቆየና ደግሞ — የቆሎ ማዘገኑ ሁለተኛው ቨርዥን ፎቶግራፍ — በማህበራዊ ድረገጾች ተለቀቀ፡፡ በዚህ በሁለተኛው ቅንብር ፎቶግራፍ — ዶ/ር አብይ ጭራሹኑ የሉበትም፡፡ ቤቱና እንግዶቹ እና የሚያዘግኑበት ስፌት ግን አለ፡፡ የእርሳቸውን ኦሪጂናል የቡና ቁርስ ስፌት ይዘው ሰዉን ጎንበስ ብለው ሲያዘግኑ የሚታዩት ዶ/ር አብይ አይደሉም፡፡ ሌላ ሰው ነው፡፡ የቀድሞው ፕሬዚደንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ናቸው፡፡ እንዴ?!! ብዬ ሣልጨርስ — ከጎናቸው የሚያዘግነውን ሌላ ሰው ደግሞ አየሁት፡፡ አቶ መለስ ናቸው፡፡ እንዴ?!! አሁንም፡፡
ይህኛው ቨርዥን — በተመሣሣይ የዶ/ር አብይ ፎቶ የተቀናበረ ነው፡፡ ዶ/ር ነጋሶም፣ አቶ መለስም — ሁለቱም — በዶ/ር አብይ ስፌት ነው — የቡና ቁርስ ለእንግዳ እያዘገኑ የሚታዩት — በቨርዥን-2ቱ ፎቶ፡፡ በፎቶው ግን — ዶ/ር ነጋሶ የዶ/ር አብይን የቅድሙን እውነተኛውን ቆሎ ሲያዘግኑ — አቶ መለስ ዜናዊ ግን — በተመሣሣይ ስፌት ለእንግዳ የሚያዘግኑት — ያንኑ የቅድሙን የጥይት ቆሎ ክምር ነው፡፡ አሁን የባሰ መጣ አልኩ!!!!
እንዴ??!! በተለይ ይሄኛው ሁለተኛው ቨርዥን — የምሩን — ግነት ሊባል ከሚችል ደረጃ እጅጉን ወደ ውሸትነት ደረጃ አሻቀበ የሚል ሃሳብ መጣብኝ — ‹‹ኩሸት›› ሳይሆን — በቃ ‹‹ውሸት››!! እንዴ!!?? አንዳንዴ እኮ — ልናጋንን እንችላለን — ተገቢም ነው — የስነፅሑፍ ለዛና ድምቀትም ነው፡፡ ሴንሴሽናሊቲም አለው፡፡ ሰዋዊነት፣ ስሜታዊነት፣ አሁንነት የሚባለው ነፍስ አለው፡፡
ነገር ግን — ለምሳሌ — በኢትዮ-ኤርትራው ጦርነት ወቅት — አቶ መለስ ዜናዊ እና ዶ/ር ካሡ ኢላላ ብቻቸውን እኮ ነበር — ጦርነቱ ሊካሔድ አይገባውም ብለው — ሽንጣቸውን ገትረው ሲከራከሩ የነበሩት፡፡ አይደለም እንዴ?? እንዲያውም የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን የህይወት ታሪክ ‹‹ዳንዲ – የነጋሶ የህይወት መንገድ›› ብሎ — ዳንኤል ተፈራ ጄ. ባሳተመላቸው መጽሐፍ ውስጥ ራሱ — ይህን ነገር ዶ/ር ነጋሶ ራሳቸው ግልጽ አድርገው አልፈውታል፡፡
በወቅቱ — ‹‹ሌሎቻችን›› — ‹‹ሻዕቢያ ጦሯን ከባድሜ ካላስወጣች — ኃይል ተጠቅመን በኃይል የመጣውን በመመለስ ሉዐላዊነታችንን ማስከበር አለብን!›› የሚል አቋም እንደያዙ ፤ መለስ ዜናዊ ግን ያን ሃሳብ አጥብቀው እንደተቃወሙ — በመጨረሻም የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴው በጉዳዩ ላይ ባለመስማማት — ወደ ድምፅ አሠጣጥ ሲኬድ — የአቶ መለስ ሀሳብ ‹‹17 ለ 2›› በሆነ ድምፅ በዶ/ር ካሡ ኢላላ ብቻ ተደግፎ በዝረራ እንደተሸነፈ — ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ደግሞ ከ17ቱ አንዱ እንደሆኑ — እውነታውን ግልጽልጽ አድርገው አስነብበውናል፡፡ ለዚህም ዶ/ሩ ክብር ይገባቸዋል፡፡
በእርግጥ ኢህአዴግ ለወሰነው የጦርነት ውሳኔ እና በዚያ ጦርነት ላለቁት ኢትዮጵያውያን ኃላፊነቱን የሚወስድ እንደመሆኑ መጠን፤ በተመሣሣይ ግን — የሚያስተዳድራት ሀገር ‹‹ተወርራለች›› ብሎ ያመነ ማንም ሀገር-ወዳድ አካል እንደሚያደርገው — በሀገር ላይ የተቃጣብንን ወረራ እንከላከላለን ብሎ መወሰንም — መብትም ነው — ሀገራዊ ግዴታም ሊሆን ይችላል — እና በዚያ ለምን አቋምህ ያ ሆነ ወይም አልሆነ ብለን ለመውቀስም ሆነ ለማድነቅ — ብዙ ነገሮችን መፈተሽ እና ለታሪክ ፍርድ መተው እንደሚገባን ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን አሁን ያስገረመኝ — ይሄ መለስ ለአስመራዎች በእንቅብ ጥይት ሲያዘግኑ — ዶ/ር ነጋሶ ደግሞ ለአስመራዎች በእንቅብ ዳቦና ቆሎ ሲያዘግኑ — የሚያሳየውን ፎቶ ሳይ ነው — እጅግ የገረመኝ፡፡
ምክንያቱም — እውነታው —  ከዚያ የመለስ-ነጋሶ ቅንብር ፎቶ — ፍፁም ተቃራኒ ስለሆነ ነዋ፡፡ ስለዚህ ያ ፎቶ ለእኔ — ከ‹‹ኩሸት››ም አልፎ — በቃ — እልም ያለ ዓይኑን ያፈጠጠ ‹‹ውሸት›› ስለሆነ፡፡ አቶ መለስ በሥልጣነ-ዘመናቸው ብዙ አግባብ ያልሆነ ውሳኔ አሳልፈው፣ ሌላ ቀርቶ በርካታ ‹‹ወንጀል›› ሠርተው ሊገኙ ይችሉ ይሆናል፡፡ ከሠሩት በትክክል በሠሩት አግባብ ያልሆነ ነገር ስማቸው ቢነሣ — ሙት መውቀስ ካልሆነ በቀር — ‹‹ኩነኔ›› እሚያስገባን አይመስለኝም፡፡
ነገር ግን — እውነታውን አገላብጦ — አቶ መለስ — በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝቦች መካከል ዳግም ወደ ጦርነት መገባት የለበትም በማለታቸው — እንዲያውም ‹‹ዘር ከልጓም ይስባል›› በሚል — ‹‹ኤርትራዊ ደምህ ነው እንዲህ የሚያስለፈልፍህ›› ተብለው — ሁለት ሰባት እንዲያሳልፉ ወደፀበል ሊላኩም እንደነበረ፣ ከሥልጣናቸው ገሸሽ እስከመደረግ በደረሰ ስለመገለላቸው፣ እና በግድ የድርጅቱን ማዕከላዊ ኮሚቴ የድምፅ ውሳኔ — ‹‹እየተናነቀህም ቢሆን አስፈጽማት!›› ተብለው ወደ ጦርነት ተገደው እንደገቡ — በግልጽ የሚታወቅ እውነታ እያለ — ያ ጦርነት መካሄድ አለበት ያለውን ሰው — የሰላም ቆሎ እያዘገኑ — ያ ጦርነት መካሄድ የለበትም ያለውን — እና በግዱ ያስፈጸመውን ሰው ግን — የመሣሪያ ጥይት እያዘገኑ — እውነታውን — በፍፁም ውሸት አገላብጦ — ለሕዝብ ማቅረብ ግን — ታሪክን በስህተት ጎዳና እንዲሄድ እያወቁ አይንን አፍጦ ከመጠምዘዝ አይተናነስም፡፡
በአንድ በኩል — ዛሬ ላይ ያለን እና የተረፍን ትውልዶች — ብዙዎች — ማንም ያለሥራው በጭፍን ሊወቀስ፣ ባልዋለበት ሊኮነን አይገባውም፣ ማንም ሰው ሊመዘን እና ሊኮነን የሚገባው በሠራት ሥራው፣ እና በነበረበት የታሪክ ሂደት ተመዝኖ ነው እያልን — ለእውነትና ለሀቅ ስንሟሟት — እንታያለን፡፡ በጎ ሥራቸው እንደኃጢያት ተቆጥሮ ያለሥራቸው ስም ሲሰጣቸው የኖሩ — በርካታ ታላቅን ሥራ ሠርተው ያለፉ ታላላቅ ሠዎችንም — የሠሩትን ሁሉ እያየን፣ እየሰማን — በሚዛናዊ ልኬት በህዝብ ዓይን ተመልክተን የራሳችንን እንድናጤን — ወደ እውነት እንድንቀርብ — በእውነት ብዙዎች ምንም ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ — በታሪካችን ሚና የነበራቸው ዜጎቻችን — ተገቢውን ቦታ እንዲያገኙ እየታተሩ የሚገኙም በርካታ ሀገር ወዳዶች እንዳሉም ግልጽ ነው፡፡
ነገር ግን — በሌላ በኩል — ለሚዛናዊነት እና ለእውነት እና ለሀቅ ተቃራኒ በሆነ አቅጣጫ — ‹‹ውሸት››ን ከ‹‹እውነት›› እንዳንለይ ሆነን — ያንዱን ላንዱ ማድረግ ግን ተገቢ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ ያለአግባብ ሠው አስገድለዋል፣ ያለህግ ዜጋን ጭፍጭፈዋል፣ ያለሀቅ ዘርፈዋል፣ ያለፈሪሀ-እግዜር ገርፈዋል፣ ረግጠዋል፣ ጨቁነዋል — የሚባሉ ሰዎች — በትክክል በሠሩት ሥራ ይወቀሱ፡፡ ይፀፀቱ፡፡ ይኮነኑ፡፡ አሊያም ድርጊቶቹ በትውልድ እንዳይደገሙ – እውነቱ እየተነገረ — ሁሉም ትምህርት ይውሰድባቸው፡፡
ግን — ግን — ግን — ሰውን ያደረገውን ‹‹እውነት›› ወደ ጎን ብሎ — ተቃራኒውን ያላደረገውን የ‹‹ውሸት›› ካባ አላብሶ — ‹‹እውነታ››ውን አገላብጦ ማቅረብ ግን — ሁላችንን በ‹‹ሸፍጥ›› መንገድ ላይ አሣፍሮ — ከመጣንበትም የ‹‹ኩሸት›› እና ‹‹ውሸት›› የተምታታ ጎዳናም አስውጥቶ — ከዚያ በባሰ ፍጥጥ ባለ የ‹‹ውሸት›› ጎዳና ሁላችንም እየተበሻሸቅን እንድንጓዝ የሚያደርግ — በውሸት ዓለም ተለያይተን — እውነት በሌለበት ጎዳና — በውሸት መዓት እየተበሻሸቅን እውነቱ-ከሐሰቱ ተድበስብሶ ያንኑ እየደገምን እንዳንቀጥል — ሁላችንም ወደዚያ ዓይነቱ የስህተት ጎዳና እንዳይገፋን — ትልቅ ስጋት አለኝ፡፡
እውነት ውሸትን መሞገቻ ብቸኛ መሣሪያ ነች፡፡ የሀቀኞች መሞገቻ እውነት ብቻ ነች፡፡ እና እውነትን እንያዝ፡፡ የሚያንገበግበን፣ የሚያናድደን ብዙ ቢሆንም — እውነት እንድትጨፈለቅ አናድርግ፡፡ እውነት የመጨረሻዋ ውሸትን የመዋጊያ መሣሪያችን ነችና፡፡ እናማ… ‹ሚን ላማለት አካባቢ ኖ›?? አካባቢውማ — በቃ — ‹ከሐሰተኛ ነቢያት እንጠንቀቅ!› ነው፡፡ ከእኔም ከራሴም ዓይነቱ ጭምር፡፡ አበቃሁ፡፡
አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ እምዬ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡ ሑሩ ወመሐሩ፡፡ አሜን፡፡
ፎቶግራፉ ‹‹መለስ_ዜናዊ_FDRE_Defense_Force››
Filed in: Amharic