>
5:13 pm - Sunday April 20, 5175

“በተሠየሙበት ሰማዕቱ መርቆሬዎስ በዓል ቀን መመለሳቸው፣ትልቅ የታሪክ መጋጠም ነው፤” (ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ)

“ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ በአንድ ዕለት የተቀባንበት ነባር የመነሻ ታሪክ አለን!!!”
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ
* “በተሠየሙበት ሰማዕቱ መርቆሬዎስ በዓል ቀን መመለሳቸው፣ትልቅ የታሪክ መጋጠም ነው፤”
 
* በሢመተ ጵጵስና፣ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጋራ በአንድ ቀን የተቀቡ አባቶች ናቸው፤
 
• በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥራ አብረው አገልግለዋል፤
 
• ዛሬም፣በዕርቀ ሰላሙ ስምምነት መሠረት፣ በእኩል የአባትነት ክብር በየድርሻቸው ያገለግላሉ፤
 
• “በቅዱስ ሲኖዶስ አመራር፣ የሰላምና የአንድነት አስተዳደሩን የምናስቀጥልበት ወቅት ነው፤”
 
• “በዝግታ እየተመካከርንና ሥራውን እያሻሻልን በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሕዝቡን እንመራለን፤” 
†††
ሀራ ተዋህዶ
4ኛው የቤተ ክርስቲያናችን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ እና 6ኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ በማዕርገ ጵጵስና የአንድ ዘመን ተሿሚዎች ናቸው፡፡ በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ፣ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም. ከተሾሙት 13 ኤጲስ ቆጶሳት መካከል ለማዕርገ ፕትርክና የበቁት የዛሬዎቹ ኹለቱ አባቶች ይገኙበታል፡፡ የፊቱ አባ ዘሊባኖስ ፈንታ ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ ተብለው በኦጋዴን አውራጃ፣ የፊቱ አባ ተክለ ማርያም ዐሥራት ብፁዕ አቡነ ማትያስ ተብለው በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ኤጲስ ቆጶስነት የተሾሙት በአንድ ቀን ነበር፡፡
በአቀባበል መርሐ ግብሩ ይህንኑ ያወሱት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ቅዱስነትዎና እኔ በእግዚአብሔር ተጠርተን በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ እድ በአንድ ዕለት ተቀብተን በኤጲስ ቆጶስነት መሠየማችን የማይዘነጋ ነባሩ ታሪካችን ነው፤” ብለዋል፡፡
በሢመተ ጵጵስና ብቻ ሳይኾን በክህነቱም በአንድ መቅደስ አገልግለዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ትላንት ረቡዕ፣ ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በቤተ ክርስቲያን ደረጃ ይፋዊ አቀባበል ያደረጉበት የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ የቀደሱበትና ያወደሱበት፣ በልዩ ልዩ ተግባራት ተመድበው የሠሩበትና ዘመናዊ ትምህርት የተከታተሉበት ነው፡
በዕርቀ ሰላሙ የጋራ ስምምነት መሠረት፣ ቤተ ክርስቲያናችን፣የኹለቱንም ቅዱሳን ፓትርያርኮች ስም በጸሎቷ እየጠራች፣ በእኩል የአባትነት ክብር አስቀምጣ በየድርሻቸው እንዲያገለግሏትና እንዲመሯት አድርጋለች፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በጸሎትና ቡራኬ በማድረግ ሲመሯት፣ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ደግሞ የአስተዳደር ሥራውን በመሥራት ይመሯታል፡፡
“ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ፣ በጤናና በሕይወት ጠብቆ ለዚህ ሕይወት አድርሶ ወደ ቅድስት ሀገርዎ ኢትዮጵያ ለመግባት እንኳን አበቃዎ፤” በማለት ተቀብለዋቸዋል – ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፡፡ አያይዘውም፣ “ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበት ጊዜ አለው፤ ተብሎ እንደተጻፈው፣ ቅዱስነታቸውና እኔ ዕድሜ ከጤና አምላካችን ሰጥቶን ይህን ቀን ለማየት ስላበቃን ለእግዚአብሔር ልዩ ምስጋናን ዘወትር እያቀረብን ወንድማማችነታችንና መንፈሳዊ አባትነታችንን አጽንተን ከመኖር የበለጠ ሌላ ምን እንከፍለዋለን፤” ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡
የካህናትና የምእመናን እንባ የታበሰበት ሲኖዶሳዊና አስተዳደራዊ አንድነቱ፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር ለማሻሻል፤ በካህናት፣ በምእመናንና በወጣቶች መካከል የሠለጠነ አሠራር ለመትከል፣ ስለ ሀገራችንና ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ኹለንተናዊ ልማትና ዕድገት የምንደክም የሥራ ተካፋዮች እንደሚያደርገን ቅዱስነታቸው ተናግረዋል፡፡ “ኅሡ ሰላማ ለሀገር፣ ለሀገራችሁ ሰላምን እሹ፤” የሚለውን ለመፈጸም፣ “ናሁ አዳም ወናሁ ሠናይ ሶበ ይሄልዉ አኃው ኅቡረ፤ ወንድሞች በኅብረት ቢኖሩ እነኾ መልካም ነው፤ እነኾም ያማረ ነው፤” ለሚለው ዘይቤ ተገዥ ኾነው የቤተ ክርስቲያንን የሰላምና የአንድነት አስተዳደር በቅዱስ ሲኖዶስ እየመሩ ሐዋርያዊ ተልእኳቸውን እንደሚፈጸሙም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ 4ኛ ፓትርያርክ ኾነው የተሾሙት፣ ነሐሴ 29 ቀን 1980 ዓ.ም. ሲኾን፣ በፖሊቲካዊ ግፊትና ጫና መንበራቸውን ለቀው ከሀገር ከመውጣታቸው በፊት እስከ ነሐሴ 28 ቀን 1983 ዓ.ም. ድረስ ለቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ አመራር ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ከ26 ዓመታት ስደት በኋላ፣ ትላንት ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ በስሙ በተሠየሙበት በሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ክብረ በዓል ወደ ቅድስት ሀገራቸው ኢትዮጵያ መመለሳቸውን፣ “ትልቅ የታሪክ ግጥምጥሞሽ ያደርገዋል፤” በማለት የአቀባበል መርሐ ግብሩን የመሩት የጠቅላይ ጽ/ቤት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ሓላፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጩ አድንቀዋል፡፡
ቅዱስነታቸው አቡነ መርቆሬዎስ፣ በኤጲስ ቆጶስነት በተሾሙበት ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም. እንዲሁም ሢመተ ፕትርክናቸው በተፈጸመበት ነሐሴ 29 ቀን 1980 ዓ.ም.ከወጡት የቤተ ክርስቲያናችን ኅትመቶች ያሰባስብነውን የሕይወት ታሪክና ሥራዎቻቸውን እንደሚከተለው መጥነን አቅርበናል፡፡
‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡
ልደት
በፊት ስማቸው አባ ዘሊባኖስ ፈንታ የሚባሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በጎንደር ክፍለ ሀገር በደብረ ታቦር አውራጃ በአለታ ወረዳ አረጊት ኪዳነ ምሕረት በተባለችው ገዳም ሰበካ፣ ልዩ ስሙ ማር ምድር በ1930 ዓ.ም.፣ ከብላታ ፈንታ ተሰማና ከወ/ሮ ለምለም ገሰሰ ተወለዱ፡፡
መንፈሳዊ ትምህርት፤
ዕድሜያቸው ለትምህርት በደረሰ ጊዜ፣ በተወለዱበት ገዳም መሪጌታ ላቀው ከሚባሉ መምህር፣ ንባብና ዳዊት ተማሩ፡፡ ከዚያም በኋላ አጭታን ኪዳነ ምሕረት በምትባለው ደብር ምዕራፍና ጾመ ድጓ ተምረዋል፡፡
ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወደ ጎጃም ክፍለ ሀገር ሔደው ጎንጅ ቴዎድሮስ በተባለው ገዳም ለኹለት ዓመት ከመሪጌታ ወርቁ፣ ወደ ዋሸራ በመዛወር በቅኔ ዝነኛ ከነበሩት ከመሪጌታ ማዕበል ፈንቴ ለኹለት ዓመት በጠቅላላ በአራት ዓመት የቅኔ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ ከዚያም በኋላ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ተመልሰው፣ በደብረ ታቦር አውራጃ እስቴ ወረዳ አጋጥ ደብረ ጽዮን፥ የምዕራፍ፣ ጾመ ድጓና ድጓ ትምህርታቸውን ከመሪጌታ ሙጩ አጠናቀዋል፡፡
ወደ አቋቋም ቤት በመግባት፣ መነጒዘር በሚባለው ደብር፣ ከመሪጌታ ሚናስ ለኹለት ዓመት የአቋቋም ትምህርት ተምረዋል፡፡ ከዚያም ቁት አቡነ አረጋዊ ደብር፣ ከመሪጌታ ውብ አገኝ ለአንድ ዓመት ዝማሬ መዋሥዕት ተምረዋል፡፡ ወደ ደብረ ታቦር አውራጃ ተመልሰው፣ ከጥንቱ መምህራቸው ከመሪጌታ ሙጩ ላቀ ዘንድ የድጓ ትምህርታቸውን በመቀጠል ጽፈውና አመልክተው ከጨረሱ በኋላ፣ በነፋስ መውጫ አውራጃ በታች ጋይንት ወረዳ በምትገኘው በስመ ጥሩዋ በቤተ ልሔም አራት ዓመት ቆይተው ድጓ አስመስክረው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡
የድጓ ትምህርታቸውን ካስመሰከሩ በኋላ ወደተወለዱበት ገዳም ሔደው፣ በአረጊት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ለሰባት ዓመታት ያህል ድጓ አስተምረዋል፡፡
ሥርዐተ ምንኵስናና መንፈሳዊ አገልግሎት፤
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ፣ ሥርዐተ ምንኵስናን ከመምህርነት ጋራ አጣምሮ ለመያዝ ያላቸው ፍላጎት ከፍ ያለ ስለኾነ በጣና ገዳም ዳጋ እስጢፋኖስ በመግባት ማዕርገ ምንኵስናን ከመምህር ኃይለ ማርያም(በኋላ የባሕር ዳር ቅዱስ ጊዮርጊስ መልአከ ገነት) በ1961 ዓ.ም. ከተቀበሉ በኋላ፣ በዚሁ ዓመት ማዕርገ ቅስናን፣ ከጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ተቀብለዋል፡፡
የገዳምን ሥነ ሥርዐት ይበልጥ ማጥናት ስለፈለጉ፣ በባሕር ዳር አውራጃ ልዩ ስሙ ጋሾላ በተባለ ገዳም ገብተው የገዳሙን ሥነ ሥርዐት እያጠኑና ለገዳማውያን እየታዘዙ ለኹለት ዓመት ገዳሙን ረድተዋል፡፡ በገዳሙ በነበሩበት ጊዜ፣ በጸሎተ ማኅበር፣ የልማት ሥራ በመሥራትና አቅመ ደካሞችን በመርዳት ገዳሙን አገልግለዋል፡፡
ከዚያ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ በቅዳሴና በማሕሌት እያገለገሉ ትርጓሜ ሐዲሳትንና አቡሻኽርን ተምረዋል፡፡ ዘመናዊ ትምህርታቸውንም በቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት እስከ ኹለተኛ ደረጃ ተከታትለዋል፡፡ በተጨማሪም ለመምህራን፣ የተደረገውን የስብከት ዘዴ ኮርስ ለኹለት ዓመታት ተምረው የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡
 
በቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነት፤
የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ኾነው በመሾም በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የነበረውን ችግር ተገንዝበው ለአገልጋዮች መኖሪያ ቤት አሠርተውላቸዋል፡፡ የእሑድ(የሰንበት) ት/ቤት ወጣቶችም የመሰብሰቢያ አዳራሽ ስላልነበራቸው አንድ አዳራሽ ከነሙሉ ድርጅቱ አሠርተው በመስጠት ችግራቸውን አቃለውላቸዋል፡፡ ተጀምሮ የነበረው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እንዲጠናቀቅና በአካባቢው የነበሩ ምእመናንም በሰበካ ጉባኤ እንዲደራጁ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡
ሢመተ ጵጰስና፤
ባላቸው በቂ የቤተ ክርስቲያን ዕውቀትና ባሳዩትም የመንፈሳዊ አገልግሎትና የሥራ ወዳድነት፣ ቤተ ክርስቲያናችን፣ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም. ባደረገችው የ13 ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ፣ በካህናትና በምእመናን በከፍተኛ ድምፅ ተመርጠው የኦጋዴን አውራጃ ኤጲስ ቆጶስ ኾነው ተሾመዋል፡፡
በዚህ አውራጃ፣ በጠላት ፈርሶ የነበረውን ቤተ ክርስቲያን በማሠራትና በማሳደስ፤ በጦርነት ምክንያት የተሸበረውንና የተደናገጠውን ሕዝብ በማጽናናት ስለ ኢትዮጵያ አገሩ ፍቅር በማስተማርና በማስረዳት ሐዋርያዊ ተልእኳቸውን ፈጽመዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በ1971 ዓ.ም. ወደ ጎንደር ሀገረ ስብከት ተዛውረዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በጎንደር ሀገረ ስብከት የፈጸሙአቸው ሥራዎች፡-
በወቅቱ በነበረው አለመረጋጋት፣ በጭልጋና በደባርቅ አውራጃዎች እየተዘዋወሩ ሕዝቡን በማስተማር ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በየጊዜው በሚያሳዩት መልካም የሥራ ውጤት፣ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሊቀ ጵጵስና ማዕርግ ተቀብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ራሷን እንድትችል ለማድረግ ቀዳሚ ተግባር የሚኾነው ምእመናንን በሰበካ ጉባኤ ማደራጀትና ማጠናከር ስለኾነ፣ በሀገረ ስብከት በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሰበካ ጉባኤን በማቋቋምና በማጠናከር፣ የሰንበት ት/ቤቶችንም በማስፋፋት ቅርሳቅርሶች በክብካቤ እንዲያዙ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ መጽሔቶችና ጋዜጦች ለሕዝበ ክርስቲያን እንዲደርሱ፣ የቤተ ክርስቲያን መመሪያና ደንብ ቃለ ዐዋዲ በተግባር እንዲተረጎም አድርገዋል፡፡
በጎንደር ክፍለ ሀገር የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታደሱና በርከት ያሉ አዲስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነፁ አድርገዋል፡፡ በተለይም በደብረ ታቦር አውራጃ በእስቴ ወረዳ፡-
1. የአረጊት ኪዳነ ምሕረትን ቤተ ክርስቲያን በግል ገንዘባቸው ቆርቆሮ እንድትለብስ አድርገዋል፡፡
2. በዚሁ ወረዳ ውስጥ የምትገኘውን ደብረ ምሕረት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን፣ ከግል ገንዘባቸው ብር 9ሺሕ በማውጣት ቆርቆሮ እንድትለብስ አድርገዋል፡፡
3. መንፈሳዊ አዳሪ ት/ቤቶች እንዲከፈቱ፣ የካህናት ማሠልጠኛ እንዲቋቋምና ካህናት በተግባረ እድ የሚሠለጥኑበት ት/ቤት እንዲከፈት አድርገዋል፡፡
4. ምንም መተዳደሪያ ያልነበራቸው የአብነት መምህራንና ሊቃውንት፣ ለክህነት ከሚከፈለው ገንዘብ ደመወዝ እንዲቆረጥላቸው በማመቻቸት ሳይሰለቹና ሳይቸገሩ ሞያቸውን ለትውልድ እንዲያስተላልፉና የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞችም በትምህርት አቅማቸውን እንዲያሻሽሉበት አድርገዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ለአንድ የዜማ መምህር፣ ለአንድ የቅዳሴ መምህር፣ ለአንድ ዕቃ ቤት ጠባቂ በድምሩ ለሦስት ሰዎች ከራሳቸው ደመወዝ በመክፈል ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ አድርገዋል፡፡ በብፁዕነታቸው ሊቀ ጵጵስና፣ 43 አብያተ ክርስቲያናት ተተክለዋል፤185 አብያተ ክርስቲያናት ተሠርተዋል፡፡
የልማት ሥራዎች፤
ሀ/ በጋይንት አውራጃ በታች ጋይንት ወረዳ በምትገኘው በታላቋ ደብር ቤተ ልሔም ከአንድ በጎ አድራጊ ርዳታ በመጠየቅ በናፍጣ የሚሠራ አንድ የሞተር ወፍጮ አቋቁመው ለካህናቱና ድጓ ለሚያደርሱ ተማሪዎች ደመወዛቸውን እንዲችሉ ጥረዋል፡፡
ለ/ በደብረ ታቦር አውራጃ በእስቴ ወረዳ ሊጋባ ቅዱስ ሚካኤል በተባለው ቤተ ክርስቲያን አካባቢ አንድ የሞተር ወፍጮ በጎ አድራጊዎችን በመጠየቅ እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ አገልጋይ ካህናትም የወር ደመወዝተኛ እንዲኾኑ አድርገዋል፡፡
ሐ/ ጥንታውያን መጻሕፍት ለትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ ባደረጉት ጥረት፡- ጠቢበ ጠቢባን፣ ሙሉ ሲኖዶስ፣ የቅዳሴ አንድምታ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰናቸውን ውሳኔዎች በሙሉ በብራና እንዲጻፉ አድርገዋል፡፡ በጭልጋ፣ በሊቦ፣ በደብረ ታቦር፣ በጋይንት አውራጃዎችና በእስቴ ወረዳ የችግኝ ጣቢያዎች አቋቁመው በየዓመቱ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ችግኞች በየአብያተ ክርስቲያናቱ ሰበካና ለሕዝባውያን ድርጅቶች እንዲከፋፈሉ በማድረጋቸው የተራቆቱ መሬቶች በዛፎች እንዲዋቡ ጥረዋል፡፡
መ/ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በማስፈቀድ በማኅደረ ማርያም የሐዲሳት፣ የድጓና የቅዳሴ ት/ቤት አሠርተው ለመምህራኑ ከ50 እስከ 200 ብር ደመወዝ እንዲከፈላቸው፣ ለደቀ መዛሙርቱ ድጎማ እንዲሰጣቸው አድርገዋል፡፡
ሠ/ ጥንታዊውንና ታሪካዊውን የጣና ቂርቆስ ገዳም በብር 8ሺሕ835 እንዲታደስ አድርገዋል፡፡ በጣና ለሬማ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ብር 4ሺሕ ረድተዋል፡፡ የደረሞ ቅዱስ ሚካኤልን ቤተ ክርስቲያን ብር 21ሺሕ 114 በማውጣት አሳድሰዋል፡፡ እንዲሁም ጥንታዊውን የግርቢ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በብር 8ሺሕ860 ብር እንዲታደስ አድርገዋል፡፡ በአዘዞ በሰሚ ቅዱስ ሚካኤል ወደ ካህናቱ ማሠልጠኛ የሚወስደው መንገድ በምግብ ለሥራ መርሐ ግብር እንዲሠራ አድርገዋል፡፡
በጎንደር መንበረ መንግሥት ጥበበ እድና የአዳሪ ቤቱ ዙሪያ ርዳታ በመጠየቅ ከ9ሺሕ በላይ በማወጣት እንዲሠራ አድርገዋል፡፡ በጎንደር ጉባኤ ቤትና የዶክተር አየለ ዓለሙ የመቃብር ቤት የአራቱ ጉባኤያት ሥዕል እንዲሠራበት አድርገዋል፡፡ በሊቦ አውራጃ በቆላ እብናት ለአምራቾች የኅብረት ሥራ ማኅበር ብር 15 ሺሕ ረድተዋል፡፡ በጎንደር ከተማ በአዘዞ አባ ሳሙኤል በመጠለያ ለሚረዱ ከልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ መምሪያ ጋራ በመተባበር የኤልክትሪክ ምጣድ ርዳታ አድርገዋል፡፡ በዳባት ወረዳ የሚገኘውን የደፍቂ ቅዱስ ሚካኤልን በብር 5ሺሕ፣ ቆማ ፋሲለደስን በብር 5ሺሕ አሳድሰዋል፡፡ ለአምስትያ ገዳም ብር 4ሺሕ፣ ለጣርክ ማርያም ብር 7ሺሕ ረድተዋል፡፡
ዐደባባይ ኢየሱስም በብር 40ሺሕ እንዲታደስ አድርገዋል፤ የድምፅ ማጉያም አስገብተውለታል፡፡ በጎንደር ዙሪያ አውራጃ ለቸንከር ተክለ ሃይማኖት ርዳታ በመጠየቅ ብር 764ሺሕ አበርክተዋል፡፡ በዚያው በጎንደር ዙሪያ ከማክሰኝት እስከ አርባያ ለመንገድ ሥራ ብር 30ሺሕ ርዳታ እንዲገኝ አድርገዋል፡፡ ከእብናት እስከ ጎሐላ ለመንገድ ሥራ የብር 6ሺሕ ርዳታ እንዲገኝ አድርገዋል፡፡
በስሜን አውራጃ ለሚገኙ ጥንታውያን ገዳማት፤ ለቤተ ሚናስ ዋልድባ ከብር 10ሺሕ በላይ፤ ለጣዕመ ክርስቶስ ብር 10ሺሕ፣ ለሰቋር ዋልድባ ብር 4ሺሕ ግምት ያላቸው የቁሳቁስ(የዓይነት) ርዳታ አድርገዋል፡፡
በጎርጎራ ገዳም በደሴተ ጣና ለሚገኙ ገዳማት፤ ለማን እንዳባ ገዳም ብር 1ሺሕ880፤ ለብርጊዳ ማርያም ገዳም ብር 1ሺሕ ለበሬ መግዣ እንዲሰጥ አድርገዋል፡፡
ከልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ መምሪያ ርዳታ ሰጪ ድርጀቶች በመጠየቅ አቅም በፈቀደ መጠን በተወሰኑ አብያተ ክርስቲያናት የቆዳ፣ የሽመና፣ የሹራብ ሥራ፣ የልብስ ስፌት፣ የወፍጮ ቤትና የዳቦ ቤት እንዲቋቋምና አገልግሎት እንዲሰጡ አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም ለስብከተ ወንጌል፣ ለሰንበት ት/ቤትና ለሕዝብም መሰብሰቢያ የሚያገለግሉ አዳራሾች በየአብያተ ክርስቲያናቱ አካባቢ አሠርተዋል፡፡ ሕዝቡ ንጹሕ ውኃ ማግኘት እንዲችል የውኃ ጉድጓድ በማስቆፈር ለዚሁ የሚያገለግል ሞተርና ቧምቧ እንዲያገኙ የበኩላቸውን ጥረዋል፡፡
 
ለሀገረ ስብከቱ ያስገኟቸው ሽልማቶች፤
የሰበካ ጉባኤ ቃለ ዐዋዲ ደንብ በትክክል እንዲፈጸም በማድረጋቸውና ሰበካ ጉባኤን በሚገባ በማደራጀታቸው፣በየዓመቱ በሚደረገው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ የሥራ ግምገማ በተደረሰበት ውጤት የጎንደር ሀገረ ስብከት ቅድሚያ ቦታ እንዲይዝ አድርገዋል፡፡
በዚህም መሠረት፡- ከ16ቱ አህጉረ ስብከት፣ ከ1975 እስከ 1977 ዓ.ም. በተከታታይ እንዲሁም በ1979 ዓ.ም. አንደኛ፤ በ1978 ዓ.ም. ኹለተኛ በመኾን በውጤታማነት እንዲሸለም አድርገዋል፡፡ ብፁዕነታቸው፣ ከዚህ በላይ ጠቅለል ባለ መልክ በተዘረዘረው ዓይነት ተልእኳቸውን በትክክል የተወጡ አባት ከመኾናቸውም በላይ በ1979 ዓ.ም. በተደረገው የብሔራዊ ሸንጎ አባላት ምርጫ በጎንደር ዙሪያ አውራጃ ምርጫ ጣቢያ ደንቢያ ከመረጠው 26ሺሕ127 ሕዝብ መካከል 17ሺሕ249 ድምፅ በማግኘት ተመርጠው ሕዝብን አገልግለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ፣ የበላዮቻቸውን መካሪ፣ የበታቾቻቸውን አክባሪ፣ በሥራ ታታሪ፣ መንፈሳዊ አባትነታቸውና ትሑት ሰብእናቸው አርኣያነት ያለው ቁጥብ አባት ናቸው፡፡
ለፕትርክና በከፍተኛ ድምፅ የተመረጡበት ኹኔታ
ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ፣ ለ11 ዓመታት ያህል በመጀመሪያ በኦጋዴን አውራጃ ኤጲስ ቆጶስ ቀጥሎም በጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመኾንና በቅዱስ ሲኖዶስ አባልነት አገልግለዋል፡፡ ለፕትርክና ምርጫው በተዘጋጀው ደንብ አንቀጽ 2 መሠረት፡- የትምህርት ዝግጅታቸው፣ ገዳማዊ ሕይወታቸው፣ የአስተዳደር ችሎታቸው፣ የመንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎታቸው፣ ሥነ ምግባራቸው ተመዝኖ ብቃትና አርኣያነት ያላቸው አባት ኾነው በመገኘታቸው በዕጩነት ተመርጠዋል፡፡
 
የመራጭ አባላት ቁጥር፤
በምርጫው ደንብ መሠረት፣ 32 የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ 7 የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፣ 48 የአህጉረ ስብከት ሰበካ ጉባኤያት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎች ተወካዮች፣ 22 የቀደምት የአንድነት ገዳማትና ታላላቅ አድባራት ተወካዮች በድምሩ 109 መራጮች ነሐሴ 22 ቀን 1980 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ተገኝተው ድምፅ ሰጥተዋል፡፡
በዕጩነት ከቀረቡት ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት መካከል፣ ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ፣ 66 ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት፣ 4ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ኾነው ለመመረጥ በቅተዋል፡፡ ሢመተ ፕትርክናቸው ነሐሴ 29 ቀን 1980 ዓ.ም. የተፈጸመ ሲኾን፣ 4ኛ ፓትርያርክ በመኾን ቃለ መሐላ ፈጽመዋል፡፡ በፖሊቲካዊ ግፊትና ጫና መንበራቸውን እስከለቀቁበት፣ ነሐሴ 28 ቀን 1983 ዓ.ም. ድረስም፣ለሦስት ዓመታት ለቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ አባታዊ አመራር ሰጥተዋል፡፡
Filed in: Amharic