>

የትግራይን ህዝብ አናግልለው!!! (አፈንዲ ሙተቂ)

የትግራይን ህዝብ አናግልለው!!!
አፈንዲ ሙተቂ
በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች ህወሓትን በተመለከተ ይናገሩት የነበረ አንድ ነገር አለ። ይህም ድርጅቱ የትግራይ ህዝብን ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ለመነጠል ሲል የሚያካሄዳቸው እንቅስቃሴዎች በትግራዮችና በሌሎች ኢትዮጵያዊያን መካከል ውጥረት ፈጥሮ ሀገሪቷን ወደ እርስ በእርስ ጦርነት ያስገባታል የሚል ነው።
በእርግጥም ህወሓት ያካሄዳቸው እንቅስቃሴዎች ለዚሁ ተግባር የታቀዱ ነበር የሚመስሉት። ይሁንና እኛ ኢትዮጵያዊያን በምንም መልኩ መሰሪዎች በዘረጉልን ወጥመድ ውስጥ እንደማንገባ በተግባር ማሳየት አለብን። ገዥዎች ባደረሱብን በደልና ጭቆና ቂም ይዘን የትኛውንም ህዝብ አንወቅስም፣ አናገልም። አናጠቃም። ፍላጎታችን የሁሉም ብሄሮች የማንነት፣ የዲሞክራሲና የሰብዓዊነት መብቶች የሚከበርበት ስርዓት ተፈጥሮ ማየት ነው። ራእያችን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚኖርባትን ሀገር ማየት ነው። ከዚያ ውጪ ማንንም የመበደል ፍላጎትና አምሮት የለንም።
—-
ህወሓት በስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን ብዙ በደሎችና ጥፋቶች ተፈጽመዋል። እንዲያ ማለት ግን የትግራይ ህዝብ ሌሎችን በድሏል ማለት አይደለም። በተደጋጋሚ ጊዜ እንደጻፍነው የትግራይ ህዝብ በህወሓት ተጠርንፎ በአስከፊ ጭቆና ሲማቅቅ እንደኖረ አንረሳውም። ህወሓት ህዝቡ ነፃና ሚዛናዊ ዜና እንዲያገኝ እንኳ አይፈቅድለትም። ህወሓት መረጃን ከማፈኑ የተነሳ በተለያዩ የክልል ከተሞች ውስጥ በገፍ ያለው የኤፍ ኤም ሬድዮ እስከ ዛሬ ድረስ በትግራይ ክልል አይታወቅም። እስከ ዛሬ ድረስ ነፃ ጋዜጣና መጽሔት በትግራይ ክልል እንዲሸጥ አይፈቀድም። በክልሉ ያለው የመልካም አስተዳደር እጦት ስር የሰደደ ከመሆኑ የተነሳ ህዝቡ ጉዳዩን ለማስፈፀም ወደ መንግስት ቢሮዎች በሚሄድበት ጊዜ ባለስልጣኖች ከመንግስት መመሪያ ውጪ የፈለጉትን ውሳኔ ያሸክሙታል። ውሳኔው ተገቢ አይደለም ብሎ አቤቱታ ማቅረብ የለም። በማህበራዊ አገልግሎቶች ረገድም ክልሉ ከሌሎች በተሻለ ሁኔታ ላይ አይደለም። ብዙዎች እንደመሰከሩት ዛሬም ድረስ በትግራይ ከተሞችና ገጠሮች ስር የሰደደ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር አለ።
ህወሓት ሲጨነቅ የኖረው ለትግራይ ልማት ሳይሆን ለኤፈርት ብልፅግና ብቻ ነው። ኤፈርት የትግራይ ህዝብ ንብረት አለመሆኑን ደግሞ በቅርቡ አንድ ቱባ የህወሓት ባለስልጣን ነግረውናል።
—–
ብዙኃኑ ኢትዮጵያዊያን አሁን የተሻለ ዘመን መጥቷል በማለት ያምናሉ። አዲሱ የለውጥ ሂደት የተሟላ የህሊና እርካታ የሚሰጠን የትግራይ ህዝብንም በሂደቱ ስናሳትፍ ነው። ይህ ደግሞ የህዝቡ መብት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በጋራ የተሸከሙት ግዴታ ነው። ስለሆነም አንዳንድ ዋልጌዎች በሚጭሯቸው ትንኮሳዎች ተናዳችሁ የትግራይ ህዝባችንን ልብ የሚሰብር ማንኛውንም የጽሑፍ፣ የድምፅና የምስል መልእክት ከማሰራጨት ራሳችንን መቆጠብ አለብን።
—–
በተደጋጋሚ ጊዜ እንደተናገርነው ህወሓት የ43 ዓመት ጎልማሳ ፓርቲ ነው። የትግራይ ህዝብ ግን ከጥንት ጀምሮ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር እየኖረ ነው። “መንግስታት ያልፋሉ” ብለን ስንናገር እንደከረምነው ሁሉ ህወሓት ያሰፈነው ያልተገባ ስርዓት አልፎ አዲስ የሽግግር ዘመን መጥቷል። የትግራይ ህዝብ ግን ትናንትም፣ ዛሬም፣ ነገም የኛ አካል ሆኖ ይኖራል።
—-
መንግስታት ያልፋሉ። ህዝቦች ይኖራሉ። እኛ ከህዝቦቻችን ጋር ነን።
Filed in: Amharic