>

የትግራይ ተወላጆች ተገደሉ ስለተባለበት የጃዊዉ ጉዳይ እውነታው ሲገለጥ (ግዮን ፋንታሁን)

የትግራይ ተወላጆች ተገደሉ ስለተባለበት የጃዊዉ ጉዳይ እውነታው ሲገለጥ
ግዮን ፋንታሁን

* «ድሮዉንስ አማራ ጎማና ቤት ማቃጠል እንጅ ሌላ ምን ያዉቃል?» የማህበረሰቡን ስስ ስሜት የነካ ዘለፋ

በጃዊ በማንነታቸዉ አማካኝነት ግለሰቦች ተገደሉ ተብሎ ዜና ተሰራጭቷል፤ በምን ሁኔታ ተገደሉ ለሚለዉ ግን ተዘሎ ታልፏል፤ የግለሰቦች መገደል አድለም መደብደብ በምንም ምክንያት ይሁን በራሱ ትክክል ሊሆን አይችልም፤ ነገር ግን በህዝብ ስስ ስሜት ላይ ቤንዚን እየተርከፈከፈ በተነሳ ግርግር በእሳቱ ለጠፋ ነፍስ ማነዉ ተጠያቂ የሚሆነዉ? ይሄን አይነት ችግርስ መቼ ነዉ መቆሚያዉ?

የችግሩ መነሻ እንዲህ ነዉ:–

አንድ ቤት ተቀምጠዉ ሰዎች የኢንጅነር ስመኘዉ የቀብር ስነስርአትን በመከታተል ላይ ይገኛሉ፤ በመሀከሉ አንደኛዉ ስልክ ይደወልለታል፤ ስልኩን በማዉጣት «አንተ አታቃጥለኝ፤ ዝም ብለህ አጥፋዉ» የሚል ንግግር ተናግሮ ከመጨረሱ መብራቱ ይጠፋል
አንደኛዉ ኮርነር ላይ የነበረ/ች ሰዉ አማካኝነት እንዲህ የሚል ነገር ይነገራል

«መብራቱን ያጠፋዉ ስልክ ያናገረዉ ልጅ ነዉ፤ ከዚ በፊትም እንደዚህ ያደርጋል» ከዚህ ንግግር ቀጥሎ
«ለምን እንደዚ ታደርጋላችሁ?» ከሚል መመላለስ ተነስተዉ አንድ ሁለት ይባባላሉ፤ ችግር መፈጠር የጀመረዉ ይሄኔ ነዉ፤ ያ ስልክ ሲደወልለት መብራት አስጠፋ የተባለዉ ልጅ በምልልሱ መካከል፤ ሰዉን ስሜታዊ ያደረገ እንዲህ የሚል ንግግር ይናገራል:–

«ድሮዉንስ አማራ ጎማና ቤት ማቃጠል እንጅ ሌላ ምን ያዉቃል?» በማለት ሌላ ከባድ መጥፎ ቃል ይናገራል፤ ልጁ ስሜታዊ በመሆን የተሰበሰበዉን ሰዉ ወደ ማይቆጣጠረዉ ስሜት ይከታል፤ ስሜታዊ የሆነዉ የተሰበሰበዉ ሰዉ ወደ እርምጃ ከገባ ደግሞ መከላከል አደገኛ ይሆናል፤ ቤት ዉስጥ የተከሰተዉ አለመግባባት ወደ ዉጭ በማምራት መብራት ለማጥፋት ጥረት እያደረገ የነበረን ሌላ ሰዉ ጨምሮ መሆን የሌለበት ነገር ይሆናል፤ እዉነታዉ ግን ትግሬን በማንነቱ ለማጥቃት ከሆነ ጃዊ የስኳር ፕሮጀክት አካባቢ እጅግ ብዙ ተጋሩ የሚኖርበት አካባቢ ነዉ፤ ህዝቡ የታጠቀ ከመሆኑ አንፃር እጅግ ብዙ እልቂት ሊደርስ ይችል ነበር፤ ከሁለት አመት በፊት በተነሳዉ ህዝባዊ ንቅናቄ መሳሪያዉን በመታጠቅ እስከመደራጀት የደረሰ ቆራጥ ህዝብ ያለበት አካባቢ ነዉ፤ ነገር ግን ያኔም አጥፊዎችን እንጅ እጅግ ብዙ የሆነዉን የጃዊ ስኳር ልማት ተጋሩ ሰራተኛ አልነካም፤ እዉነታዉ የማንነት ጥቃት ለማድረስ ታስቦ ሳይሆን ህዝቡ ላይ አላስፈላጊ ተግባር ከተፈፀመ በኋላ የህዝብ ስስ ስሜትን የሆነዉን የብሔር ጉዳይ አንስቶ በጅምላ ማነወር ያስነሳዉ ችግር ነዉ።

እኔ ከዚህ ነገር የተረዳሁት እዉነታ፤ በህዝብ ስስ ስሜት ላይ ጨዋታ ለመጫወት መሞከር መዘዙ አደገኛ ነዉ፤ የትኛዉም ሰዉ በየትኛዉም ሁኔታ፣ በየትኛዉም ቦታ ብሔርን ያማከለ ሞገደኛ ጭቅጭቅ ዉስጥ መግባት እጅግ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚሄድ ነገር እንዲገጥም ያደርጋልና ሊቆጠብ ይገባል። ህብረተሰቡም ስሜታዊ ከመሆን እነዚህን አጥፊዎች ለህግ አቅርቦ ለፈፀሙት ስህተትና በጅምላ ህዝብን ላነወሩበትና ሁኔታ ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ይቻል ነበር። ሰዉን በጅምላም ይሁን በግል መግደል አድለም መደብደብ ስህተት ነዉ። የምንፈልገዉ ሰላምና ዲሞንራሲ በዚህ መንገድ አይመጣም፤ ሰላምና ዲሞክራሲ እንዲመጣ ስሜትን አርቆ ማሰብ አስፈላጊ ነዉ። ይህ ሁኔታ ህዝብ አንድ ጭንቅላት ኖሮት አንድ ሀሳብ ሊኖረዉ እንደማይችል ያስረዳል፤ የተቆጣ ህዝብ በተለያየ አቅጣጫ ወደ ስህተትና ስርአተ አልበኝነት ሊገባ ይችላልና መጠንቀቁ መልካም ነዉ፤ በተለይ በተለይ ይሄ የቁጨ ፌደራሊዝም የሀገራችንን ህዝብ በተለይም ወጣቱን በዘራበት እኩይ አስተሳሰብ ምክንያት፤ አንድ አንዱን የሚያንቋሽሽበት፣ አንዱ ሌላዉን የሚያጠቃበት የስነ ልቦና መደላድል በመፍጠሩ መጠንቀቁ ይበጃል።
ሒወታቸዉን ያጡ ወንድሞቻችን ነፍሳቸዉን በገነት ያኑርልን፤ ለቤተሰቦቻቸዉ መፅናናትን ይስጥልን!

Filed in: Amharic