>
5:13 pm - Saturday April 19, 2127

የዐቢይና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች የጥያቄና መልስ ቆይታ በሰሜን አሜሪካ!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

የዐቢይና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች የጥያቄና መልስ ቆይታ በሰሜን አሜሪካ!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ይህ ዝግጅት ትናንትና ማታ በቀጥታ ስርጭት እንደሚተላለፍ አስቀድሞ ባለመነገሩ በመጠራራት ነበር ከጀመረ በኋላ የተከታተልነው፡፡ እንደተከታተልነውም ዐቢይ ወተርጌት በተባለው ሆቴል (ቤተ እንግዳ) ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ሰብስቦ የጥያቄና መልስ ዝግጅት አኪያሒደው ነበር፡፡
ስሙ “የጥያቄና መልስ!” ተባለ እንጅ አንዳቸውም ጠያቂ በቅጡ ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ አላየሁም፡፡ እያንዳንዳቸው ሦስት ሦስት ደቂቃ ተሰጥቷቸዋል ቢባልም እንኳን ሦስት ደቂቃ አንድ አንድ ደቂቃ እንኳ ያወሩ አይመስለኝም፡፡
ደቂቃ ልይዝ እያሰብኩ መሰንበቻየን “የዐቢይን የተደበቀ ወያኔያዊ ማንነት ተገልጦ ማየት ከፈለጋቹህ እነዚህን እነዚህን ጥያቄዎች ጠይቁትና የሚመልስላቹህን መልስ ስሙት!” እያልኩ ስጽፍ ሰንብቸ ስለነበር “እስኪ ማን እኔ ያሳሰብኳቸውን ጥያቄ ወይም ተመሳሳይ ጥያቄ ያነሣ ይሆን?” የሚለው ጉጉቴ ትኩረቴን ሰረቀውና የአንዳቸውንም ደቂቃ ሳልይዝና የረባ ጥያቄ በቅጡ ሲቀርብ ሳልመለከት ጥያቄዎቹ አለቁና ወደ ዐቢይ መልስ ታለፈ፡፡ ትጠይቃላቹህ ተብለው ተጠርተው ከነአካቴው የመጠየቅ ዕድል ሳይሰጣቸው የቀሩ እንዳሉም ተሰምቷል፡፡
የገረመኝ ነገር አንደኛው ጠያቂ ከሌላኛው ጠያቂ አለመማሩ ነው፡፡ በሁለት ነገር፦
አንደኛው፦ የሰዓት እጥረት ያስከተለውን ችግር በመረዳት ሊጠይቁት ያሰቡትን ጥያቄ የፊተኛው ሰው ካነሣው ሌሎቹ ሌላ ጥያቄ እንደማንሣት ተመሳሳይነት ያለውን ጥያቄ ለማቅረብ ሲንደፋደፉ ሰዓታቸው እያለቀ በርከት ያሉ ጥያቄዎች ሳይቀርቡ በመቅታቸው ሲሆን፡፡
ሁለተኛው፦ ጠያቂዎቹ የፊተኛው ለዐቢይ በሚያቀርበው ውዳሴ የተሰጠው ሰዓት አልቆ ጥያቄው ተቋርጦ ሲቀርበት እያየ ቀጣዩ ሰው ወደነጥቡ በመግባት ሰዓቱን መጠቀም ሲኖርበት ከበፊተኛው ሰው በተሻሉ ቃላቶች ዐቢይን ለማወደስ ሲንደፋደፍ ሰዓቱ አልቆ ለቀጣዩ ሲያስረክብና ቀጣዩም ያንኑ ሁኔታ ሲደግም ማየት ምን ያህል እንደሚያበግን መገመት የሚቻል አይመስለኝም፡፡
ሰዎች ሥልጣን ፍለጋ ለደጅጥናት የቀረቡ ደጀጠኝዎች እንጅ ፈጽሞ ተፎካካሪ ወይም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ (የእምነተ አሥተዳደር ቡድን) መሪዎች አይመስሉም፡፡ ሲፎካከሩ የነበሩት ዐቢይን በተሻለ ቃል አወድሰው በፊቱ ሞገስ ለማግኘት በሚደረግ ጥረት ወይም ፉክክር ነበር፡፡ በጨረሻም መጀመሪያ ላይ ከኢሕአፓ ተወካይ በኩል በቀረበው “እስከ አሁን ማንንም መሪየ ብየ አላውቅም ነበረ አንተ ግን መሪየ ነህ!” በሚለው የውዳሴ ቃል “መሪያችን ነህ!” በሚል ውዳሴ የጋራ የውዳሴ መብአ ለዐቢይ አቅርበው እየተፍነከነኩ በእጅጉ ረክተው ተበትነዋል፡፡
አሁን እነዚህ ናቸው እንግዲህ ወያኔ/ኢሕአዴግን ተፋልመው የኢትዮጵያን ሕዝብና የሀገሪቱን የተወሳሰበ ችግር መፍታት የሚችሉት??? ምኑንስ ተፋለሙት ገና ከወዲሁ “መሪያችን ነህ!” ብለው ዐቢይን ሲመርጡና ለዐቢይ ቅስቀሳ ሲያደርጉ እያየናቸው???
እኔ “ለምን ያመሰግናሉ?” አይደለም እያልኩ ያለሁት፡፡ መመሰጋገኑ መልካም ነው፡፡ ፖለቲካችንን ሰላማዊ ያደርጋልና፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት ዐቢይን ያወደሱባቸው ቃላቶች ገና ምንም ሠርቶ ላላሳየና በወሬ፣ በድለላ ብቻ ላለ ሰው የሚገቡ ናቸው ወይ??? ገና ምን ሠርቶ አሳየና??? ሲጀመር የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠብቅበትን ለውጥ የማምጣት ፈቃዱና ፍላጎቱስ አለው ወይ??? የሚያወራውን እንደማያደርግ የሚጠቁሙ ነገሮች ባሉበት ሁኔታና በርካታ የሚሸሸው ነገር ያለ መሆኑ በግልጽ እየታየ፣ አስመሳይ አጭበርባሪነቱን የሚያጋልጡ የሚፈራቸው ጥያቄዎች እንዳይመጡበት እነሱን ራሳቸውን በሰዓት እጥረት እንዴት አድርጎ ደፍድዶ እንደያዛቸውና እንዳፈናቸው እዛው ላይ እያዩት ምን አላስተዋዮች ቢሆኑ ነው ሩጫውን ጨርሶ፣ ሠርቶ አስመስክሮ ሕዝቡን ላረካ መሪ የሚሰጥን ውዳሴ ለማዥጎድጎድ ፉክክር መያዛቸው ተገቢ የሚሆነው??? ነው የኔ ጥያቄ፡፡
ዐቢይን ወጥሮ የመያዙና ልቡ ውስጥ ያለውን የማስተፋቱ ጉዳይ እዚህኛው ዝግጅት ላይ እንደከሸፈ ሳይ ከምሁራን ጋር ያደርገዋል የተባለውን ዝግጅት ጠብቄ ነበረ፡፡ ይሄኛው ደግሞ ጭራሽ የጥያቄና መልስ ዕድል ያልተሰጠበት የዐቢይና የአንዳንድ ሰዎች ወሬ ተሰምቶ የተበተነበትና “ትጠይቃላቹህ ትወያያላቹህ!” ተብለው እንዲገኙ የተደረጉት ምሁራኑ እዚያ ቦታ በመገኘታቸው በጸጸት ጠጉራቸውን የነጩበት መሆኑን ስሰማ በእጅጉ አዘንኩኝ፡፡ በአንድ በኩል ግን በዐቢይ ላይ ከንቱ ተስፋ የጣሉ ሰዎች ከዚህ ሁሉ ሸፍጥ የሚገባቸው ነገር መኖሩ ደስ ብሎኛል፡፡
እኔ ዐቢይ በዚህ አሳፋሪ በሆነ ተራ ማወናበጃ ያመልጣል የሚል ግምት አልነበረኝም፡፡ በማስመሰሉ ታዳሚዎችን ለማሳመን ስለሚፈልግ መድረኩን ነጻ አድርጎ በሁለቱም መድረክ ላይ የታደሙ ታዳሚዎችን እንደፈለጉ እንዲጠይቁ አድርጎ የሚቀርብበትን የተደበቀ ሐሳቡንና ማንነቱን የሚያጋልጡ ጥያቄዎችን በብልጣብልጦች የማምለጫ በር በኩል በማምለጥ አወናብዶና ድል በድል ሆኖ ይመለሳል የሚል ግምት ነበር የነበረኝ፡፡ ዐቢይ ለካ የዚህን ያህል በራስ መተማመን አልነበረውም ኖሯል “ሞኛቹህን ፈልጉ! ስትፈልጉ የፈለጋቹህትን በሉኝ!” ብሎ እንደነገሩ እንደነገሩ አድርጎ ግልጽና ተደራሽ ሆኖ መቅረብን ባልፈለገ አቀራረብ ነገሮችን በርቀት በርቀት ቋጭቶ ለከፍተኛ ትዝብትም ተዳርጎ ሁለቱን ተጠባቂ ዝግጅቶች ጨርሷል፡፡
እኔማ እነ አቶ ተክሌ የሻው እንዲያ መሆናቸው በእጅጉ ቢያበግነኝ አብሶ ደግሞ ዐቢይ በአማራ ሕዝብ ላይ የተፈጸመውን ሰፊ የዘር ማጥፋት ጥቃት “አልተፈጸመም!” በማለት እጅግ አሳዛኝ፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የጎደለው፣ ለብሔራዊ መግባባትና ለሀገር ሰላም ፈጽሞ የማይበጅ አቋሙን ይፋ ካደረገ በኋላ ከዚህ ስብሰባ ከወጡ በኋላ ከአማራ ራዲዮ ጋር የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ከዐቢይ ጋር ስላደረጉት የጥያቄና መልስ ቆይታ ተጠይቀው ሲመልሱ የዐቢይን ፍጹም ኃላፊነት የጎደለውንና የአማራን ክብር የሚነካ የሚዳፈር የክህደት መልስ ጨርሶ ሳያስታውሱ ዐቢይን በማወደስ ጀምረው ዐቢይን በማወደስ መጨረሳቸው በእጅጉ ብግን ቢያደርገኝ ለአማራ ራዲዮ (ነጋሪተ ወግ) አዘጋጁ የሚከተለውን ጻፍኩና ላኩለት፦
“ወይ ጉድ! አማራ ስትሉ፣ የዘር ማጥፋት ስትሉ የእውነት ለአማራ የቆማቹህ መስሎኝ ነበር፡፡ ለካ ለጭምብል ኖሯል፡፡ አማራ የተፈጸመበትን አረመኔያዊ የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ጥቃት “አልተፈጸመም!” ብሎ የካደውን ጠላት ይሄንን የክህደት አቋሙን ይፋ ካደረገ በኋላም እሱን በማወደስ ተጠምዳቹህ ታርፉት??? አቶ ተክሌስ እሽ መሪየ ብለው ተቀብለውታልና ከዚህ በኋላ ትኩረታቸው ወደየት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በአማራ ጉዳይ ላይ እንሠራለን ብላቹህ በጋዜጠኝነት እዚያ የተቀመጣቹህት እናንተ ግን ሌላው ቢቀር ቢያንስ እንኳ እንደጋዜጠኛ እንዴት ይሄንን የዐቢይ ክህደት ሳታነሡ ልታልፉት ቻላቹህ??? እንደምታወሩት የአማራ ጉዳይ ጉዳያቹህ ቢሆንና ልባቹህ ውስጥ የተቀመጠ ሐሳብ ቢሆን ትዘነጉት ነበር??? ይገርማል!!! ሁሉንም ጊዜ እየገለጠው ነው፡፡ ለጊዜ ምስጋና ይግባውና!!!” ብየ፡፡
አዎ ጊዜ ሁሉንም እየገለጠ ያሳየናል!!!
ድል ለአማራ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic