>
5:13 pm - Saturday April 19, 8673

ከ"ግንቡን እናፍርስ፣ ድልድዩን እንገንባ!"  የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ (በፍቃዱ ጌታቸው)

ከ”ግንቡን እናፍርስ፣ ድልድዩን እንገንባ!”
 የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
በፍቃዱ ጌታቸው
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አሕመድ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለማነጋገር ወደ አሜሪካ ያቀናሉ፡፡
ግንቡን እናፍርስ፣ ድልድዩንም እንገንባ(Break the wall, Build the Bridge)
በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ይህ ጉዞ ዋና ዓላማው በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በመነጋገር በሀገራቸው ዲሞክራሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዞ ውስጥ ተገቢውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ፤ እነርሱም ከሀገሪቱ ዕድገት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚቻልባቸውን መንገዶች ከዳያስጶራው ወገናችን ጋር ለመወያየት ነው፡፡
በዋሽንግተን ዲሲና በሎስ አንጀለስ ከተማ ሁሉም ወገኖች የሚሳተፉባቸው ሕዝባዊ ጉባኤያት ይደረጋሉ፡፡ ከልዩ ልዩ አካላትጋርም የተለያዩ ውይይቶች ይደረጋሉ፡፡
ሕዝባዊ ጉባኤዎቹ በዋሽንግተን ዲሲ ሐምሌ 21 ቀን (July 28, 1018) ከሰዓት በኋላ፤ በሎስ አንጀለስ ደግሞ ሐምሌ 22(July 29,1018)ከሰዓት በኋላ ይደረጋሉ፡፡
ሁለቱ ከተሞች የተመረጡት በምሥራቁና በምዕራቡ የአሜሪካ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ወደ አቅራቢያ ማዕከል ለማሰባሰብ እንዲመች ተብሎ ነው፡፡
ምንም እንኳን በተለያዩ ግዛቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በየአካባቢያቸው ለመቀበል ፍላጎት ቢኖራቸውም ካለው ጊዜ አንጻር ሁሉንም ለማዳረስ ስለማይቻል ሁለቱ ቦታዎች ተመርጠዋል፡፡ በመካከለኛው አሜሪካ የሚገኙትም ወደሚያመቻቸው አቅጣጫ በመሄድ መሳተፍ ይችላሉ፡፡ በጉባኤያቱ ላይ ለመሳተፍ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ካሁኑ የሥራ ሁኔታቸውንና ጉዟቸውን እንዲያመቻቹ እንጋብዛለን፡፡
በእነዚህ ሕዝባዊ ጉባኤያት ላይ የፖለቲካ አመለካከት፣ ሃይማኖት፣ ብሔር፣ ወዘተ ሳይለያያቸው ሁሉም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉ ተጋብዘዋል፡፡ ዋናው ዓላማ ግንቡን በማፍረስ ድልድዩን መገንባት ስለሆነ፡፡
ይህንን ጉዞ የሚያስተባብር በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያና የሚመራ ዐቢይ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ተቋቁሞ ከግንቦት መጨረሻ ጀምሮ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡ ኮሚቴው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎች የኅብረተሰብ አካላት የተውጣጣ ነው፡፡
በተመሳሳይም በዋሽግተን ዲሲና በሎስ አንጀለስ ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው ሥራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በዋሽንግተን የተቋቋመው ኮሚቴ በአምባሳደር ካሣ ተክለ ብርሃን የሚመራ ሲሆን በሎስ አንጀለስ የተቋቋመው ኮሚቴ ደግሞ በቆንስል ጄኔራል አቶ ብርሃነ ኪዳነ ማርያም የሚመራ ነው፡፡
እነዚህ በዋሽንግተንና በሎስ አንጀለስ የተቋቋሙ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ሁሉንም የፖለቲካ አመለካከቶች፣ ማኅበረሰቦች፣ የእምነት ተቋማት፣የብሔር ስብጥሮች፣ ጾታዎች፣ የእድሜ ልዩነቶች ወዘተ ባካተተ መልኩ እንዲዋቀሩ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
በዚሁ አጋጣሚም ሁሉንም ያካተቱ እንዲሆኑ በአሜሪካ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የበኩላችሁን አስተዋጽዖ እንድታደርጉ ጥሪዬን አቀርባለሁ ፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ለመቀበል የሚፈልጉ የተለያዩ ወገኖች ኮሚቴዎችን እያቋቋሙ፣ ዝግጅቶችን እያደረጉ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በቅርቡም እርሳቸው ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ያመጧቸውን ለውጦች የሚደግፉ ሰልፎች በልዩ ልዩ የአሜሪካ ግዛቶች ተደርገዋል፡፡
ሥራው መሠራት ያለበት በተበታተነ መንገድ ሳይሆን መደመርን በሚያሳይ መልኩ በጋራ ስለሆነ፤ ሁሉም ወገኖች በዋሽንግተንና በሎስ አንጀለስ ከተቋቋሙት ኮሚቴዎች ጋር አብረው እንዲሠሩ ጥሪ እናደርጋለን፡፡ ተሳትፎው ለሁሉም ወገን ክፍት ነው፡፡
ጊዜው የመደመር ነው፡፡
በዋሽንግተን ዲሲና በሎስ አንጀለስ ከተማ የሚደረጉትን ሕዝባዊ ጉባኤያትና ሌሎች ውይይቶችን የተሳኩ ለማድረግ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በሀገር ፍቅር ስሜት እንዲተባበሩ፤ በመደመር መንፈስ አንድነታቸውን እንዲያሳዩ፤ የፖለቲካ፣ የእምነት፣የብሔርና የአመለካከት ልዩነቶቻችን እንደተጠበቁ ሆነው ነገር ግን ለሀገራችን ዴሞክራሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት በጋራ የምንነሣበት አጋጣሚ እንዲሆን ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ማንኛውም አፍራሽ የሆኑ ተግባራትን ሁሉ ተቋቁመን፣ በፍቅርና በይቅርታ ሁሉንም አልፈን፤ ጥላቻንና ማግለልን ተጠይፈን ለኢትዮጵያ በጋራ እንሥራ፡፡ ሁሉም ነገር በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ብስለት እንዲከናወን ጥሪ እናደርጋለን፡፡ በሂደቱ የሚያጋጥሙንን ችግሮች እንደ ፈተናዎች ቆጥረን እንማርባቸው እንጂ አናኩርፍባቸው፡፡ ከመደመር የሚያስቀረን ምንም ነገር አይኑር፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከ25 ዓመታት በላይ ተለያይተው የሚገኙትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች ለማስታረቅና ወደ አንድነት ለማምጣት በበጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን አስታራቂ ሽማግሌዎች በተቋቋመ ኮሚቴ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጉዞ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎም የዕርቀ ሰላሙ ሂደት በዋሽንግተን ዲሲ ይካሄዳል፡፡ ይህ የዕርቀ ሰላም ሂደት እንዲከናወን ጥረት ላደረጉት በሀገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙት አስታራቂ ሽማግሌዎችና እነርሱን በልዩ ልዩ መንገድ ላገዟቸው ሁሉ መንግሥት ምሥጋና ያቀርባል፡፡ ዕርቅ ወርዶ ሰላም እንደሚፈጠርም በጽኑ ያምናል፡፡ ለዕርቁ ዝግጁ የሆኑትን የሁለቱንም ወገን አባቶች ያመሰግናል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለዕርቀ ሰላሙ ያላቸውን ድጋፍ በቦታው በመገኘት ይገልጣሉ፡፡ አባቶችንም ያነጋግራሉ፡፡
ቅስቀሳውን በማካሄድ፤ መልካሙንም መንገድ ሁሉ በማመቻቸት ሚዲያዎች የቻላችሁትን ሁሉ አድርጉ፡፡ የእምነት አባቶች፣ የኮሚዩኒቲ መሪዎች፣ የፖለቲካ ልሂቃን፣ ምሁራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ ወጣቶችና ልዩ ልዩ ባለሞያዎች ለፕሮግራሙ መሳካት የበኩላችሁን ሁሉ እንድታደርጉ ጥሪ እናደርጋለን፡፡ እናመሰግናለን፡፡
Filed in: Amharic