>

ማን አሸነፈ? ቤተክርስቲያን ወይስ ወያኔ??? (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው) 

ማን አሸነፈ? ቤተክርስቲያን ወይስ ወያኔ???
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
በሰሜን አሜሪካ የተደረገው በስደት ላይ ያለውን የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ የመመለስ ድርድር “ቀኖና ቤተክርስቲያንን በጠበቀ መልኩ በስምምነት ተጠናቋል!” ተብሏል፡፡
“ቀኖና ቤተክርስቲያን በጠበቀ መልኩ!” መባሉ ቀኖና ቤተክርስቲያን “ፓትርያርክ በሕይወት እያለ ፓትርያርክ አይሾምም!” ይላልና ፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 4 ቁጥር 68-70፡፡
እንዲሁም “የፓትርያርክ ሥልጣን በአንድ ዘመንና በአንድ ሀገር ለ2 ሰዎች ልትሆን አይገባም! በአጋጣሚ በተለያየ ምክንያት ተፈጽሞ ከተገኘ ግን መንበሩ ወይም ሥልጣኑ ቀድሞ ለተሾመው ትጽናለት!” ይላልና፡፡ ፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 4 ቁ.70
በዚህ ምክንያት ሁለት ፓትርያርክ ማድረግ አልቻሉም፡፡ ግን ምን አደረጉ መሰላቹህ ወያኔ ከሥራው እንጅ ከስሙ ጉዳይ የለውምና
የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ቀዳማዊ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያን ሕጋዊ ፕትርክና አጽንቶ የፕትርክና ቦታውን ለሳቸው በመስጠት በኃይል እንዲለቁ ወደ ተደረጉበት መንበረ ጵጵስና ቅድስተ ማርያም ለመመለስ፣ ከቀኖና ቤተክርስቲያን ውጭ ፓትርያርክ የተባሉት አባ ማትያስ ደግሞ ቀድሞም ቢሆን ፕትርክናቸውን ቤተክርስቲያን አታውቀውምና ፕትርክናው ቀርቶ በጵጵስና ደረጃ የቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ መርቆሬዎስ ቀዳማዊ እንደራሴ ወይም ወኪል ሆነው የቤተክርስቲያኗን የአሥተዳደር ሥራ ከቡድናቸው ከወያኔ ካድሬዎች (ወስዋሾች) ጋር ሆነው እንዲሠሩ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
ይሁንና ግን አሁንም ቢሆን ይህ ስምምነት ሥርዓተ ቤተክርስቲያንን ከመቃረን ሙሉ ለሙሉ የጸዳ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የእንደራሴነት አገልግሎት በቤተክርስቲያን ውስጥ ጨርሶ የለምና ነው፡፡ መንፈሳዊ አገለግሎትንና መንፈሳዊ ሥልጣንን የሚጻረር ለቤተክርስቲያን ባዕድ የሆነ አሠራር ነውና፡፡
እንደራሴነት የሚያገለግለው መንፈሳዊ ሥልጣን በሌለበት በቤተ መንግሥት ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም በቤተክርስቲያን ሕግ መሠረት የፓትርያርኩን መንፈሳዊ ተልእኮ አገለግሎትና ተግባር ጳጳሱ፣ የጳጳሱን ኤጲስ ቆጶሱ፣ የኤጲስ ቆጶሱን ቆሞሱ፣ የቆሞሱን ቄሱ፣ የቄሱን ዲያቆኑ፣ የዲያቆኑን አናጎኒስጢሱ፣ የአናጉንስጢሱን ምእመኑ መሥራት ስለማይችልና ፈጽሞ የተከለ ስለሆነ ነው፡፡
ታዲያ እንዴት ሆነው ነው አባ ማትያስ የቅዱስ ፓትርያርኩ እንደራሴ ወይም ወኪል ሆነው የቤተክርስቲያኗን የአሥተዳደር ሥራ ሊሠሩ የሚችሉት??? የአንድ ፓትርያርክ ዋናው ሥራ ምን ሆነና??? ከጾም፣ ጸሎት፣ ሥግደትና ትሩፋት ጋር የተባበረ አሥተዳደር አይደለም ወይ??? ለጸሎትና ለቡራኬውማ ካህን ሞልቶ የለም ወይ???
ልክ እኮ ወያኔ ፕሬዘዳንት ወይም ርእሰ ብሔር እያለ በስም ብቻ እዚያ ላይ ቆልሎ እየደለለ እንግዳ መቀበልና መሸኘትን ሥራ አድርጎላቸው በማጃጃል የመንግሥት ሥልጣንን ለጠቅላይ ሚንስትር (ዋና ሹም) ጠቅልሎ በመስጠት ሲያቄል የከረመበትን ዘዴ እኮነው ወደ ቤተክርስቲያን ያመጣው፡፡
እናም እንግዲህ ቅዱስ ፓትርያርኩ ቤተክርስቲያን ወይም ክርስቶስ ከጣለባቸው አደራና ተልእኮና ተግባር ታቅበው በበዓታቸው ተዘግቶባቸው በጸሎትና በቡራኬ ብቻ ተወስነው “ፓትርያርክ!” በሚለው ስም ብቻ ተወስነው ይኖራሉ፡፡ እነ አቦይ ማትያስና መዝባሪ ጠንቀኛ የወያኔ ጭፍራ ቡድናቸው ደግሞ የቤተክርስቲያኗን የአሥተዳደር ሥራና ኃላፊነት በእንደራሴነት ይዘው እስከዛሬ በቤተክርስቲያን ላይ ሲያደርሱ የነበሩትን ወደር የለሽ አረማዊ ጥፋት መፈጸማቸውንና ወያኔን ማገልገላቸውን ይቀጥላሉ ማለት ነው፡፡
ታዲያ ማን አሸነፈ ትላላቹህ??? በነፍስ ቤተክርስቲያን በሥጋ ወያኔ ወይም በመንፈሳዊው ቤተክርስቲያን በሥጋዊው ወያኔ አሸነፉ እንበል ይሆን???
ስደተኛው ሲኖዶስ አሳዛኙና ቤተክርስቲያንን በእጅጉ የፈተነ ያንገላታ ይህ የክፍፍል ታሪክ መዘጋት እንዳለበት ስላመነበትና ስለፈለገ ነው እንጅ ስምምነቱ ፈጽሞ አግባብነት የሌለው መሆኑ ጠፍቷቸው እንዳልሆነ ሁላቹህም ልብ ልትሉት የምትችሉት ጉዳይ ይመስለኛል፡፡
ከዚህ ስምምነት አንድ ልብ ልንለው የሚገባን ጉዳይ ግን አለ፡፡ እሱም ቤተክርስቲያን አሁንም ከአገዛዙ ጫናና ጣልቃገብነት ነጻ አለመሆኗንና ቀኖና ቤተክርስቲያን በሚያዘው መሠረት ሐዋርያዊ ተልእኮዋን መወጣት ማፋጠን የማትችል መሆኗን፣ የአገዛዙ ጥቅም ዓላማና ፍላጎት በቤተክርስቲያን የተጠበቀ ሆኖ የሚቀጥል መሆኑን ያሳያል፡፡
በመሆኑም እኛ ክርስቲያኖች ይሄ ቤተክርስቲያንን ከቀኖናዋ ውጭ ያደረጋት የወያኔ አሉታዊ ጫናና ጣልቃገብነት ተወግዶ ቤተክርስቲያን ነጻነቷ ተመልሶ ያለ ማንም አሉታዊ ጣልቃገብነት ወንጌልና ቀኖናዋ በሚያዛት መሠረት ሐዋርያዊ ተልእኮዋን እንድትወጣ ለማስቻል መታገል፣ መጣር፣ መጋደል ይኖርብናል እንጅ ፈጽሞ አግባብነት ለሌለው አረማዊ አገዛዝ ጣልቃገብነት ዛሬም እጅ ሰጥተን ቤተክርስቲያን ከቀኖናዋ ውጭ በሆነ መንገድ እንድትጓዝና ኢፍትሐዊነትና ግፍ የበዛበት አሠራር እየተጎሳቆለች፣ እየተመዘበረች፣ እየከሰረች፣ እየተሰበረች ጨርሶ እስክትጠፋ ድረስ እንድትቀጥል ፈጽሞ መፍቀድ አይኖርብንም!!!
እንግዲህ ቅዱስ አባታችን ከልጆችዎ ብፁዓን አባቶች ጋር በሰላምና በጤና ለናፈቋት ሀገር ያብቃዎት አባቴ!!! እንግዲህ ዘመነ ሠማዕታትም ደረሰ አይደል??? “እባክህን አያምልጠኝ ለሀገሬ አብቃኝ???” ብለው የለመኑትን ልመና ሰምቶ ሠማዕትነት እንዳያመልጥዎት መድኃኔዓለም ክርስቶስ መግቢያ መንገድ ፈጥሮ ወደ ሀገርዎ እንዲገቡ ስላስቻልዎት በጣም ደስ ብሎኛል አባቴ!!! እንኳን ደስ አልዎት!!!
ስለ ሁሉም ነገር እግዚአብሔር ይመስገን!!!
Filed in: Amharic