>
5:13 pm - Friday April 19, 5658

እጃቸውን በብዙኃን ደም የነከሩ ‹‹ፖለቲከኞች›› መቼ ይሆን የሚያድቡት? (ከይኄይስ እውነቱ)

እጃቸውን በብዙኃን ደም የነከሩ ‹‹ፖለቲከኞች›› መቼ ይሆን የሚያድቡት?

ከይኄይስ እውነቱ

ጎሠኝነት መርዛማ አስተሳሰብ መሆኑ ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡ መነገርም አለበት፡፡ ጎሣና ፖለቲካ በጭራሽ ኅብረት የላቸውም በማለት ከማለዳው የያዝኩት አቋም ጽኑዕ እና ዘላቂ ነው፡፡ እንዳየነው ጎሣና ፖለቲካን ማዛመድ ለአገር ጥፋት ለሕዝብ እልቂት መሠረት እንደሆነ የወያኔ ትግሬ አገዛዝ መራራ ተሞክሮ ከበቂ በላይ አሳይቶናል፡፡ ባጭሩ የጎሣ ፖለቲካ የዕብደት ፖለቲካ ነው፡፡ ኦነግን ጨምሮ ወያኔ (ሕወሓት) ጠፍጥፎ የሠራቸውና ‹‹ኢሕአዴግ›› በሚል ሽፋን የሚጠራቸው ሦስቱ ድርጅቶች እንደ ድርጅትና ግለሰብ እጃቸው በንጹሐን ኢትዮጵያውያን ደም የተጨማለቀ ለመሆኑ በቂ ምስክሮች/ማስረጃዎች አሉ፡፡ ንጹሐንን ከመጨፍጨፍ በተጨማሪ አገርን ከመክዳትና ተወዳዳሪ ከማይገኝለት ንቅዘት/ዝርፊያ ጋር የተያያዙ አስነዋሪ ድርጊት የፈጸሙ አካላት ንስሓ ገብተው ሕዝብንና አገርን መካሥ ሲገባቸው በተቃራኒው ለተጨማሪ ሽብር ሲሰናዱ ማየት፤ አንዳንዶችም ተረፈ-ወያኔዎች ያለ ይሉኝታ ዓይናቸውን በጨው አጥበው  “በትግራይ ስም እንደራጅ እንጂ የኛ አመለካከት ቀድሞውንም ኢትዮጵያዊ ነው››፣ ‹‹እኛም እንዋደድ ብለን መጥተናል››፣ ‹‹ተደምረናል›› በማለት እነ አረጋዊ በርሄ የክፍለ ዘመኑን ታላቅ ፌዝ እያፌዙብን ነው፡፡ ጨለማ ከብርሃን ጋር ምን ኅብረት አለው? አካታች ወይም አሳታፊ መሆን ወንጀለኞችን ያውም በይርጋ የማይታገድና በምህረትም/ይቅርታም የማይታለፍ ወንጀል በመፈጸም የሚጠረጠሩትን ምንም እንዳልተፈጸመ ቆጥሮ በነፃነት እንዲፈነጩና የፈለጉትን እንዲዘባርቁ መፍቀድ አይመስለኝም፡፡ የቀድሞ ሕወሓት ታጋዮች የነበሩ በሰጡት የምስክርነት ቃል እንዲሁም ሰነዶችና ግዙፍ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት፣

  • ኢትዮጵያችንን ወደ ሦስት ዐሥርት ለሚጠጋ ዘመን ምድራዊ ሲዖል ላደረጋት የወንበዶች አገዛዝ ውጥኑን/ዕቅዱን (blueprint) ያዘጋጀው ‹‹መሐንዲሰ›› (architect) አረጋዊ አይደለም እንዴ?
  • ተዋሕዶ ሃይማኖትን እና አማርኛ ተናጋሪውን ማኅበረሰብ በጠላትነት ፈርጆ ከኢትዮጵያ ምድር ለማጥፋት መክሥተ ደደቢትን የጻፈው አረጋዊ አይደለም እንዴ?
  • ‹‹ባዶ ስድስት›› የሚባለውን የስቃይ መፈጸሚያ ያቋቋመና በማዕከላዊ እና በልዩ ልዩ ስውር ‹‹ወህኒ ቤቶች›› ወያኔና ተረፈ-ወያኔዎች ለፈጸሟቸውና አሁንም እየፈጸሙ ላሏቸው ተወዳዳሪ ለሌላቸው የስቃይ ድርጊቶች አብነት የሆነው አረጋዊ እንጂ ሌላ ማነው?
  • ገና በጠዋቱ ለተጎዱ ወገኖቻችን የመጣውን ዕርዳታ ዘርፈው አሁን ኢትዮጵያን ላራቆተው ተወዳዳሪ ለሌለው ሌብነትና ንቅዘት መሠረቱን የጣለው አረጋዊ በበላይነት ሲመራው የነበረው የወንበዶች ቡድን አይደለም ወይ? ወዘተ…

የዚህ አስተያየት ዓላማ ዜጎች በፖለቲካ ማኅበር የመደራጀት መብታቸውን ለመንካት ያለመ አይደለም፡፡ ሰብአዊና ዴሞክራሲያው መብቶች በኢትዮጵያችን እውን እንዲሆኑ/በተግባር እንዲገለጡ ከወያኔና ተረፈ-ወያኔዎች በስተቀር የኢትዮጵያውያን ኹሉ ጽኑዕ ፍላጎትና እየታገሉለትም ያለ ዓላማ ይመስለኛል፡፡ ይሁን እንጂ በመደራጀት ስም አንዳንድ ‹‹የፖለቲካ ማኅበራት›› ለወንጀለኞች ዋሻ ሲሆኑ ዝም ብለን አንመለከትም፡፡ በአገርና በሕዝብ ላይ ከይቅርታ በላይ የሆኑ አስነዋሪ ድርጊቶችን የፈጸሙ ግለሰቦች ለፍርድ መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ወንጀል፣ ነውር፣ ንቅዘት፣ ሌብነት የመሳሰሉ ዕኩይ ድርጊቶች ከ‹መደመር› እሳቤ ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም፡፡ እነዚህን ድርጊቶች በመፈጸም የሚጠረጠሩ ኹሉ በፍርድ ነፃ እስከሚሆኑ ወይም ጥፋተኞች ተብለው ቅጣታቸውን ካገለገሉ በኋላ በእውነት መጸጸታቸው ታይቶና የበደሉትን ኅብረተሰብ ለመካሥ በሚያሳዩት ቊርጠኝነት ኅብረተሰቡን ይቅርታ ሊጠይቁ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ኅሊና ካላቸው በገዛ ፈቃዳቸው ከፖለቲካ ሕይወት ተገልለው ስላሳለፉት ሕይወት ከራሳቸው ጋር የሚመክሩበት የጽሞና ጊዜ የሚያስፈልጋቸው ይመስለኛል፡፡  በጎሣ መደራጀቱ በራሱ የአገር ሕመም መሆኑ ሳያንስ፣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በዚህ ዓይነቱ ስብስብ ውስጥ በአገርና በሕዝብ ላይ በተፈጸመ ወንጀል የሚጠየቁ ግለሰቦችን አቅፎ መጓዝ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ድርብ በደል መሆኑ ‹መሪም› ተመሪም ሊያስተውል ይገባል፡፡

በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድና በሕዝባችን ትብብር ለማየት የምንናፍቃት አዲሲቱ ኢትዮጵያ ጎሣን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ማኅበር በሕግ የሚከለክል ሥርዓት እንደሚቆም ተስፋ እያደረግኹ፤ በሃሳብ፣ በመርህ፣ በመርሐግብር፣ በርዕዮተ ዓለምና፣ በፍልስምና ወዘተ ዙሪያ የሚደራጁ የፖለቲካ ማኅበራትም ቢሆኑ የወንጀለኞች መጠለያ እንዳይሆኑ የሚያረጋግጥ ሥርዓት መበጀት ያለበት ይመስለኛል፡፡ በመጨረሻም የጋሼ መሥፍንን አበባል ለመዋስ ‹‹ትናንት ሳይሳካላቸው የቀሩ ጎረምሶች ዛሬ ሽማግሌ መስለው አድፍጠው ይሆናል፡፡›› ያሏቸውና በዕርግና ሽፋን አሁንም አገር ለማወክ ወደ ኋላ የማይሉ አንዳንድ ‹የ ያ ትውልድ› ‹‹ጎረምሶች››  መቼ ይሆን ራሳቸውን ገዝተው ወደ ልቡናቸው የሚመለሱት?

Filed in: Amharic