>

የደብረማርቆስ እስር ቤት ቃጠሎና ተያያዥ ጉዳዮች!!! (ፋሲል የኔ አለም)

የደብረማርቆስ እስር ቤት ቃጠሎና ተያያዥ ጉዳዮች!!!
ፋሲልየኔ አለም
የደብረማርቆስ እስር ቤት ቃጠሎን በተመለከተ ከማምነው ምንጭ  ያገኘሁትን ላካፍላችሁ ወደድኩ። በአሁኑ ወቅት በፖለቲካ ምክንያት የታሰረውም ያልታሰረውም እስረኛ መፈታት የፈልጋል። በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩ እና አሁንም ድረስ ያልተፈቱ አንዳንድ ሰዎች ቢኖሩም፣ በቅርቡ አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ በየእስር ቤቶች እየዞረ የማጣራት ስራ ለመስራት መታቀዱን ሰምቻለሁ።  በፌደራል ደረጃ ያሉት የፖለቲካ እስረኞች ያልተፈቱት በአቃቢ ህግ በኩል በሚታይ መጓተት ነው፤ ሃላፊነት መውሰድ ያለበት እንዲሁም በፍጥነት ተጠያቄ መሆን ያለበት የፌደራል አቃቢ ህግ ነው። የፖለቲካ አመራሩ አቃቢ ህግ የሚያወራውን ያክል እንዲሰራ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሊሰጥ ይገባዋል። ወደ ደብረማርቆስ እስር ቤት ቃጠሎ ስመጣ ፣ በዛሬው ተቃውሞ የተወሰኑ ቤቶች ፣ ሸማ የሚሰራበት ቦታና መተኛ ፍራሾች ተቃጥለዋል። ተቃውሞውን ያቀጣጠለው ሃዱሽ ተክላይ የሚባል እስረኛ ነው። ሃዱሽ ቀደም ሲል የደጀን ከተማ ቄራ ግንባታ አሸነፍኩ በማለት 800 ሺ ብር ቅድሚያ ክፍያ የወሰደ፣ ቀጥሎም በባሶ ሊበን ወረዳ የመንገድ ስራ ጨረታ አሸንፍኩ ብሎ በተሳሳተ መረጃ 480 ሺ ብር የወሰደ ግለሰብ ነው።  የክልሉ ፖሊስ ግለሰቡን አፈላልጎ ሲይዘው የተለያዩ መታወቂያዎች፣ ክላሺንኮቭ ጠመንጃ፣ የተለያዩ የውጭ አገር የመገበያያ ገንዘቦች ተገኝቶበታል። የደቡብ ክልል ጸረ ሙስና ኮሚሽንም ግለሰቡን በጥብቅ ይፈልገዋል። ከዚህ ግለሰብ ጀርባ ብዙ ሚስጢሮች እንዳሉ የሚታመን ሲሆን፣ ምርመራው ሲቀጥል ብዙ ነገሮች ይፋ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።   የሃዱሽ ጉዳይ ህወሃት ቢያሸልብም አለመሞቱን ሊያሳይ ይችላል።
ወቅቱ መረጃዎችን በጥንቃቄ እንድንመረምር ግድ ይለናል።  መረጃዎችን የራሳችንን የግል ፍላጎት ወይም ስሜት ለማርካት ስንል ከመልቀቅ መቆጠብ አለብን።  መረጃዎችን  ለአገር አንድነትና ለህዝብ መቀራረብ እንዲሁም ለዲሞክራሲ ግንባታ ካላቸው ፋይዳ አንጻር መርምረን ብንለቃቸው ለተጀመረው ትግል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረግን ይቆጠራል።
Filed in: Amharic