>
5:13 pm - Tuesday April 18, 0586

ሞሳድ እና ካሳ ከበደ!!! ክፍል 3

ሞሳድ እና ካሳ ከበደ!!! ክፍል 3
| ሮነን በርግማን (Ronen Bergman)| ትርጉም፡ ካሳ አንበሳው |
በ1976 ካሳ ከበደ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ አንባሳደር ሁኖ ወደ ጄኒቫ ተላከ፤ የኢትዮ እስራኤል ግንኙነት አሁንም ካሳ እጅ ላይ ነው ያለው፤ ያ የደስ ደስ ያለው እና የሂብሩ ቋንቋን አቀላጥፎ የሚናገረው ጥቁር አፍሪካዊ ጄኒቫ በገባ ማግስት እዛ ካሉ እስራኤላዊያን ጋር እጅ እና ጓንት ሆነ፤
ጄኒቫ የነበረውን ሁኔታ ካሳ እንዲህ ያስታውሳል:-
“በሞሳድ በኩል ለአሜሪካኖች መልዕክት ማስተላለፍ አስፈላጊ ነበር፤ አብረን ስራ መስራት እንደምንችል ማሳየት ነበረብኝ፤ ይህን ለማድረግ እየጣርኩ ሳለው አንድ እድል ተፈጠረ፤ የኢትዮጵያ ደህንነት መስሪያ ቤት አንድ የCIA ወኪልን ኢትዮጵያ ውስጥ ሲንቀሳቀስ ይዞት በማይታወቅ ሰፍራ አሰረው፤ ሰውየው የት እንዳለ CIA አላወቀም፤ የተገደለ መስሏቸው ነበር፤ እኔ ከሞሳድ ጋር ቅርርብ እንዳለኝ አሜሪካኖቹ ስለሚያውቁ ሰውየውን እንዳስለቅቅ በሞሳድ በኩል ጥያቄ አቀረቡልኝ፤ ጊዜ ሳላጠፋ ወደ መንግስቱ ኃይለማሪያም የስልክ ጥሪ አደረኩኝ፤ ሰውየውን ብንለቅላቸው ከዋሽንግተን ጋር ያለን ግኙነት እንዲሻሻል ይረዳል ብዬ  ሀሳብ አቀረብኩ፤ ሀሳቤን ተቀብሎ ሰውየውን ለቀቀው”
በሙሴ ዘመቻ (Operation Moses) 20 ሺህ የሚሆኑ ቤተ እስራኤሎች ከኢትይጵያ የተጓጓዙት ካሳ ጄኒቫ እያለ ነው፤ ሰዎቹ መጀመሪያ ወደ ሱዳን ከዛም ወደ እስራኤል እንዲጓጓዙ ነበር የተደረገው፤ የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ጃፋር ኒማይሪ (Gaafar Nimeiry) ኢትዮጵያ ዜጎቿን በጦር መሳሪያ ቀየረች ብሎ ለአለም መገናኛ ብዙሀን ለፈፈ፤
ጉዳዩን ካሳ እንደሚከተለው አጫወተኝ:-
“ይህን ወሬ ሲሰማ መንግስቱ ኃይለማሪያም ደወለልኝ፤ እስራኤል ወሬውን እንድታስተባብል ለሞሳድ ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ አደረኩ፤ ስልኬን የሚመልስ ጠፋ፤” ሌላ ዘዴ መፈለግ እንዳለብኝ አመንኩ፤ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት የሶቭየት ኅብረት ጋዜጠኞችን ጠራው፤ የሙሴን ዘመቻ በተመለከተ የኢትዮጵያ ደህንነት መስሪያ ቤት የሰበሰበውን መረጃ ለጋዜጠኞቹ ዘረገፍኩላቸው፤ የኒማይሪ መንግስት እና እስራኤል የነበራቸውን ትብብር ጭምር ነው በማስረጃ አስደግፌ ይፋ ያደረኩት፤ ይህ መግለጫ አለምን አነቃነቀ፤ ስልኬን አልመልስ ያለው ሞሳድ ከጋዜጣዎው መግለጫ በኋላ ትዝ አልኩት፤ የረሳኝ ሞሳድ አስታወሰኝ፤ እኔን ለማረጋጋት በልዩ በረራ ወደ ጄኔቫ መጡ፤ ሲዊዘርላንድ የሚገኛው የእስራኤል አንባሳደር፣ በአውሮፓ የሚገኙ የሞሳድ አባላት፣ ከእስራኤል የተላከው ቡድን ተሰባስበው መጡ፤ ጮሁብኝ፤ መልሼ ጮውኩባቸው፤ እኔ የናንተ መጫወቻ አሻንጉሊት አይደለሁም፤ ከፈለጋችው ሲኦል ግቡ፤ የሱዳንን መግለጫ ካላስተባበላችው ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ እውስደዋለው” አልኳቸው፤
ይህ ሁሉ ሁኖ የኢትዮ እስራኤል ግንኙነት እንደቀጠለ ነው፤ በኢትዮጵያ በኩል ካሳ ከበደ በእስራኤል በኩል የሞሳድ ዋና ድሬክተር ናሁም አድሞኒ (Nahum Admoni) ግንኙነት ያደርጋሉ፤
በ1981 ሶቭየት ኅብረት ለኢትዮጵያ የምታደርገው ድጋፍ ተቋረጠ፤ መንግስቱ ኃይለማሪያም ከእስራኤል ጋር ድርድር ጀመረ፤ ኤርትራ የመሸጉትን አማጽያን ለመደፍጠጥ የሚረዳውን የጦር መሳሪያ ከእስራኤል ፈልጓል፤ በ1982 በውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዋና ድሬክተር ሩቨን ሜርሀቭ (Reuven Merhav) ሁኔታዎቹን ለመገምገም ወደ ኢትዮጵያ አቀና፤ የደርግ መንግስት እንዳለቀለት ለመረዳት ጊዜ አልውሰደበትም፤ የቀሩትን ቤተ እስራኤሎች ከኢትዮጵያ ማውጣት ለነገ የማይባል ጉዳይ እንደሆነ ተገንዝቦ ወደ ሀገሩ ተመለሰ፤
 
ሜርሀቭ ሁኔታዎቹን እንዲህ ያስታውሳል:-
“ለመንግስቱ ኃይለማሪያም መሳሪያ ብንሸጥለት አማጽያኑ እስራኤልን ለመበቀል ቤተ እስራኤሎቹን ሊያጠቁ ይችላሉ፤ ሁለተኛ አሜሪካኖቹ ይበሳጩብናል፤ መንግስቱን አይወዱትም፤ ሶስተኛ በመሳሪያው ንጽሐን ዜጎችን ሊገልበት ይችላል አራተኛ ሰውየው አይከፍለንም፤ ባዶ ካዝና ታቅፎ ነው የተቀመጠው፤”
ካሳ ወደ ሀገር ቤት ተጠርቶ የኢሰፓ የውጭ ግንኙነት ሃላፊ ሁኖ ተሾመ፤  በእስራኤል በኩል ቤተ እስራኤሎችን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል ለማጓጓዝ ለ“Operation Solomon” ዝግጅት እየተደረገ ነው፤ ካሳ ከበደ ለዚህ ዘመቻ ያደረገው አስተዋጾ አወዛጋቢ ነው፤ ከዚህ ዘመቻ ጋር በተያያዘ ካሳ ከበደን ያገኙት እስራኤላዊያን አጭበርባሪ ነው ይላሉ፤ ጠዋት ቃል የገባልህን ማታ ያጥፈዋል፤ ዘመቻውን ለማዘግየት የቻለውን ሁሉ ሲያደርግ ነበር፤ እንደ ከብት ነጋዴ ሁሉ ያደርገው ነበር፤ ሰዎቹን በመሳሪያና በገንዘብ ለመቀየር ነበር የፈለገው”
የቤተ ስራኤሎቹን ጉዳይ ያንቀሳቀሰችው ሱዛን ፖልላክ (Susan Pollack) ናት፤ ሱዛን አሜሪካዊት ጁ ነች፤ ወደ ጎንደር ተጉዛ ቤተ ስራኤሎችን አነጋገረች፤ ነቅለው ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡና እስራኤል ኢምባሲ አካባቢ እንዲሰበሰቡ ነገረቻቸው፤  እንደተነገራቸው ግማሹ በእግር ቀሪዎቹ በአውቶብስ እየተጫኑ አዲስ አበባ ደረሱ፤ እስራኤል ኢምባሲ አካባቢ ድንኳን ጥለው መኖር ጀመሩ፤
ሜርሀቭ ወደ ጠቅላይ ሚንስትር ሻሚር በመሄድ ቤተ እስራኤሎቹ ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ አስረዳ፤  ዩሪያል ሉብራኒ (በንጉሰ ነገስት ጊዜ በኢትዮጵያ የእስራኤል አንባሳደር የነበረ) ጉዳዩን ተከታትሎ እንዲያስጨርስ በጠ/ሚ ሻሚር ተሰየመ፤ ሲያሰናብቱት “ገንዘብ ብለህ ወደኔ እንዳትመጣ፤ ገንዘብ ካስፈለገህ የአሜሪካ ጁ ማህበርን ጠይቅ” ብለውታል፤
ሉብራኒ ወደ ኢትዮጵያ በረረ፤ ፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት መግቢያ ላይ ከ25 ዓመት በፊት ደጃዝማች ከበደ ተሰማ ያስተዋወቁትን ወጣት አገኝው፤ ካሳ ከበደን፤ ሞቅ ያለ ሰላምታ ተለዋወጡ፤ ዘጠኝ ሰአት የወሰደ ስብሰባ ተደረገ፤ መንግስቱ ኃይለማሪያ ኢትዮጵያ እና እስራኤል ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት በስፋት እና በጥልቀት አብራራ፤ አስከትሎም የጦር መሳሪ እና የኢኮኖሚ እርዳታ ልታደርጉልን ይገባል ብሎ ደመደመ፤
“ጨዋታው ገንዘብ እንደሆን ከመንግስቱ ጋር ከነበረኝ ወይይት ተረዳው” ያላል ሉብራኒ
(ይቀጥላል፟:-ምናልባት አንድ ወሳኝ የመጨረሻ ክፍል)
Filed in: Amharic