>

ጽሞናን አንግበን፣ በኅብረት፣ በብርታት – ወደፊት እንራመድ! (አሰፋ ሀይሉ)

ጽሞናን አንግበን፣ በኅብረት፣ በብርታት – ወደፊት እንራመድ!
አሰፋ ሀይሉ
 
ፍቅርን አንርገጥ፣ 
ግብታዊነትን እንጠንቀቅ፣ 
በአጥፍቶ-ጠፊነት አንመካ፣ 
ፈጣሪን እንፍራ፣ 
እነዚህ ቀይ ቀበሮዎች በኢትዮጵያችን ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ የዱር አራዊት ናቸው፡፡ እንዲያውም በቅርቡ ወደሃገራችን የመጡ ተመራማሪዎች የቀይ ቀበሮዎቹን ‹ዲ.ኤን.ኤ.› አጥንተው መልካቸው ቀበሮ ቢመስልም የዘር ቅንጣታቸው ግን ከተኩላ (‹ዎልፍ›) ጋር ተመሣሣይ እንደሆነ አረጋግጠናል፣ እነዚህ ፍፁም የተለዩ ዝርያዎች ናቸው፣ በእነርሱ ላይ ልዩ ሣይንሣዊ ጥናትና ምርምር ለማድረግ ፍላጎት አድሮብናል… ሲሉ መደመጣቸውን ከአፍሪካ የጉዞ ጆርናል ላይ አንብበናል፡፡
እኚህ ቀይ ቀበሮዎች የሰሜን ተራሮችን እነዳሸንን፣ የመንዝን ተራሮችን፣ የባሌን ተራሮችን መኖሪያ አድርገው በመላ ሃገራችን የሚገኙ – በክልላችን ብለን ራሳችንን ካጠርነው ከብዙዎቻችን በብዙ መልኩ የሚሻሉ – የቱሪዝም መስህቦቻችን – ድንቅዬ የተፈጥሮ ሀብቶቻችን ናቸው፡፡
እንግዲህ ከእነዚህ ዝርያቸው ሊጠፉ የተቃረቡ አመራማሪ የሀገራችን ፍጡራን – ከቀይ ቀበሮዎቹ – ጠባብነት ያልጎበኘው ኢትዮጵያዊነትን፣ የክልል ግንብን ተሻጋሪነትን፣ ዘመን አስቆጣሪነትን፣ ራስን መሆንን፣ ፍቅርን፣ ነፃነትን፣ አብሮነትን፣ መደመርን፣… – ልንማር ሲገባን – ከቀይ ቀበሮዎቹ እንደመማር – የእነዚህን ቀበሮዎች (ወይም ተኩላዎች..) ኃውልት ማፍረስ – እጅግ የሚያሣዝን እና ፈጽሞ ሊስተካከል የሚገባ ግብታዊ ተግባር ነው፡፡
የምንመካባቸውን ልዩ እንስሳት ኃውልት በማፍረስ የሚገኝ ጉዳት እንጂ አንዳች ጥቅም የለም፡፡ ይህንም የሚያደርግ ለረገጠው ሥፍራ ክፋትን የሚመኝ ብቻ ነው፡፡ ወደፊት እንሂድ፡፡ ከአጥፍቶ ጠፊነት አስተሳሰብ ራሳችንን እናርቅ፡፡ ከማጥፋትና ከመጠፋፋት ፈጽሞ እንራቅ፡፡
ማንኛችንም ሰዎች ነንና ፍፁማን አይደለንም፡፡ ስህተት እንሠራለን፡፡ የሰውን ህይወት በስሜት እና በስህተት ብናጠፋ አንመልሰውምና የማይመለስ ስህተት እንዳንሠራ ልባችንን በፈጣሪ ቃል እንግራ፡፡ ነግ-በኔ እንበል፡፡ በራሳችን ቢደረግ የማንወደውን በሌላው ለማድረግ አንቸኩል፡፡
‹‹ወደ ፈተናም አታግባን›› ማለት ትልቅ ፀሎታችን መሆኑን አንዘንጋ፡፡ ፈጣሪን እየፈራንና እያሰብን መዋልም ትልቅ በረከት እንደሆነ እናስበው፡፡ ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ክፉ ሥራን እያወቅን እንዳንሠራ እንጠንቀቅ፡፡ የፍቅርን ሸማ በሁለመናችን እናጥልቅ፡፡ ጥላቻንና ቁጣን ከላያችን እናውልቅ፡፡
ይህን የመሰሉ ስሜታዊ እና ግብታዊ ስህተቶች የፈጸሙ ግለሰቦችና ወጣቶች በድርጊታቸው ሊያዝኑና ሊፀፀቱ ይገባል፡፡ የቀይ ቀበሮዎቹን ኃውልት ያፈረሱት ወጣቶች – ለፍቅር ኃይል ተሸንፈው – ከቀድሞው የተሻለ – የብርቅዬዎቹን ቀይ ቀበሮዎች ድንቅ ፍቅር፣ የህብረተሰቡን ድንቅ ጥበብ የሚያበስር – ድንቅ ኃውልት በማነፅ – ስህተታቸውን እንደሚያካክሱ – እና እውነተኛ ሰብዕናቸውን በምግባራቸው እንደሚያረጋግጡ – ፅኑ ዕምነት እና ተስፋ አለን፡፡
/በነገራችን ላይ:- እነዚህ አንድ የቀይ ቀበሮ/ተኩላ ኃውልት ያፈረሱ ወጣቶች ብቻ ሣይሆኑ፣ አንድ ሚሊየን የገዛ ወገኖቻቸውን ቤት አፍርሰው ከሚኖሩበት ቀዬ ያፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም – በቅርቡ – ከስሜታቸው ሰክነው – ከጥፋታቸው ተምረው – የወገኖቻቸውን ቀዬ ከቀድሞው በተሻለ መልክ አንፀው – ወደቀደመ ሠላም የመላበት ህይወታቸው በመመለስ – በስሜት የሠሩትን ታላቅ ሀገራዊ ጥፋት እንደሚክሱ – እውነተኛ ሰብዓዊ ማንነታቸውን ለዓለም እንደሚገልጡ – በምንም አሉታዊ ድርጊትና ሃሳብ የማይነጥፍ – ታላቅ እምነትና ተስፋ አለን፡፡/
ማጥፋት፣ መጠፋፋት – በኛ ብቻ ይብቃ! 
ሰው-ሠራሽ ሞት – ባለፈው ብቻ ይብቃ!
ወገን ይዳን፣ ትውልድ ይዳን! 
መተሳሰብና ወገናዊነት ይለምልም! 
በፍቅር እንደመር!
ፍቅር ያሸንፋል! 
እደግመዋለሁ – ፍቅር ያሸንፋል! 
አምላክ በኢትዮጵያውያንን ሁሉ ልብ ውስጥ ኃያሉን ወገናዊ ፍቅር አብዝቶ እንዲያኖርልን ተመኘን፡፡ አምላክ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ይባርክ፡፡ እናት ኢትዮጵያ – በፍቅር፣ በኅብረት፣ በብልፅግና ፀንታ – ለዘለዓለም ትኑር፡፡
አሜን፡፡
ፎቶግራፍ (ከከበረ ምስጋና ጋር)፡-
“Discover the wildlife of Ethiopia with Trevor Jenner, author of Ethiopia Travellers’ Handbook – No lack of life – Travel Africa Magazine – HR_Will-Burrard-Lucas_willbl-3.2.jpg”
Filed in: Amharic