>

አቶ ለማ ኦሮሚያን ለ3 ቀጠና ከፍሎ ስልጣን ዴሌጌት ቢያደርግ ጥሩ ይሻለዋል!!!  (ግርማ ካሳ)

አቶ ለማ ኦሮሚያን ለ3 ቀጠና ከፍሎ ስልጣን ዴሌጌት ቢያደርግ ጥሩ ይሻለዋል!!!
ግርማ ካሳ
ለግል ጉዳይ ዲሲ ነበርኩ።ከአንድ ትልቅ በከተማቸው ከተከበሩ የኦሮሞ አባት ጋር ተገናኘው። የአገር ሽማግሌ ናቸው። የአንድ የኦሮሞ ጎሳ መሪ። ጎሳዉን ወክለው የሚመርቁ። በቅርቡ ነው ከኢትዮጵያ የመጡት።
ለአቶ ለማ መገርሳ ትልቅ ፍቅርና አክብሮት ነው ያላቸው። ብዙ የማላወቀውን ነገሮች ነገሩኝ።  “ኦሮሚያ ትልቅ ክልል ናት። ሰፊ ናት። ሁሉም ቦታ ገነት ሊሆን አይችልም።፡የዘረኝነት ችግር ያለባቸው ቦታዎች አሉ። የኔ ልጅ ወለጋ ሄዶ ኦሮምኛ ማውራት ስለማይችል ሆቴል ቤት አናስተናገድም ብለዉት ነበር”ሲሉ በኦሮሞ ክልል ችግሮች እንዳሉ ነገሩኝ።
ሆኖም ግን እኝህ አባት፣ ችግሩ በተወሰኑ ቦታዎችና በተወሰኑ ቡድኖች የሚፈጸም እንጅ በአብዛኛው የኦሮሞ ክልል ያለ ችግር እንዳልሆነ አስረዱኝ።  “ልጄ እንደሚወራው እኮ  ቢሆን ኖሮ ፣ በኦሮሚያ ከሁሉም ወገን በሚሊዮን የሚቆጠር ሰው ነበር የሚያልቀው። የኦሮሞ ህዝብ ከሌላው ጋር መኖር የለመደ ብቻ ሳይሆን ባህሉም ነው”  ነበር ያሉኝ።
ወገኖች አዎን በኦሮሞ ክልል ሌሎች ዜጎች ኦሮሞ አይደላችሁም መጤ ናችሁ ተብለው ይፈናቀላሉ። አዎን ይሄን ከሚያደረጉት ውስጥ ኦህዴዶች አሉበት። አዎን አስቸጋሪ አፍቃሪ ኦነግ አካባቢዎች አሉ። አዎን የተበላሸ ዘረኛ አመለካከት ያላቸው አክራሪ ኦሮሞዎች አሉ። አዎን ችግር አለ። በወለጋ፣ በባሌ …እያየን ያለነው ይሄንኑ ነው።
ግን ሰባ ፣ ሰማኒያ በመቶ በላይ የሚሆነው ሕዝብ ምን አልባትን ከዚያም በላይ ኢትዮጵያን የሚወድ ፣ ለሌላው ፍቅር ያለው ማህበረሰብ ነው። ሜጋፎኑን ስላያዙና ድምጻቸውን የበለጠ የሚያሰሙት እነርሱ ስለሆኑ ብዙ መስለው ይታያሉ እንጂ እኝህ አባት እንደነገሩኝ ኢመንት ናቸው። የነዚህ ኢመንቶችን ጩኸት እየሰማን አገር ወዳድ በሆነው አብዛኛው የኦሮም ማህበረሰብ ላይ አመለካከታችን እንዲቆሽሽ መፍቀድ የለብንም።
እነ አቶ ለማ መገርሳ ይሄንን ችግር ለማስተካከል ደፋ ቀና እያሉ ነው። እየተንቀሳቀሱ ነው። እንቅስቃሴያቸው በቂ ነው ? በቂ አይደለም። ሆኖም ግን እየጣሩ ነው። ምን ያህል ለነርሱም ከባድ እንደሆነ አምስት ነጥቦችን በማንሳት ለማሳየት ልሞክር፡
፩. ኦሮሚያ ሰፊ ክልል ናት። ለአንድ ለአቶ ለማ በዚያ ክልል ያለውን ችግር በቀላሉ ለመፍታት በጣም አስቸጋሪ ነው።
፪. የአቶ ለማ ደርጅት ወደ አራት  ሚሊዮን አባላት አሉት። አብዛኞቹ በኦነጋዊ አስተሳሰብ የተቃኙ በጥላቻ የተሞሉ ናቸው። እነዚህ በዞን፣ በወረዳ፣ በቀበሌ ደረጃ መንግስት ናቸው። እነርሱን ማስተካከል ወይንም ማጥራት ከባድ ነው። ጊዜ ይወስዳል።
፫. የክልሉ ሕጎችና አሰራሮች ራሳቸው በዘረኝነት ላይ የተቃኙ በመሆናቸው ለችግር አፈታት ዉስብሰብነትን የራሳቸው አሉታዊ ሚና አላቸው።
፬. አሁንም በጥላቻ የተሞሉ አካራሪ የኦሮሞ ድርጅቶችም አሉ፤  ወደ ስንት የሚጠጉ ከኦነግ የወጡ ድርጅቶች።  በዉጭ አገር ያሉ ብዙ ጊዜ በኦሮሞ ሜዲያ ኔትዎርክ እየቀረቡ ዘረኝነትን የሚሰብኩ አክራሪዎችም ቁጥር ቀላል አይደለም። እነዚህ ሃይላት በፊናቸው የሚፈጥሩትም የአይምሮ ማቆሸሽ ጉዳት አለ።
፭. የገንዘብ አቅም ያለው በነ አቶ ለማ ከስልጣን ወደ ጎን የተገፋ እነ አቶ ለማ እንዳይሳካላቸው የሚፈለግ በጥቅም ከሕወሃት ጋር የተሳሰሩል ለሕወሃት ውስጥ ውስጡን የሚሰሩ ሲረኞችም አሉ። የህወሃት አካራሪ ቡድን ለነ ለማ መገርሳ መቼም ጊዜ አይተኛም።
የአቶ ለማ አስተዳደር በቀላሉ በኦሮሞ ክልል ያለውን ችግር የመፍታት ፍላጎት ቢኖረውም አቅም ላይኖረው ይችላል።  አቅምም ካለው ብዙ ጊዜ ሊወስደበት ይችላል። በመሆኑም እነርሱን ቻሌንጅ ማድረጉን እየገፋንበት ፣ ሁሉም ነገር በአንዴ ካልተስተካከል ብለን ማዉገዝ የለብንም።
ችግሮቹን ከመፍታት አንጻር  አማራጭ ሐሳቦችን ማመንጨትና መተግበር አስፈላጊ ነው። እንደ ጊዜያዊ መፍትሄ የሚከተሉትን አቅርቢያለሁ፡
፩.  ወዳጄ ግርማ ሰይፉ ጋር በዲሲ ተገናኘተን ያቀረበልኝ ሐሳብ ነው።፡ጥሩ ሐሳብ።፡በዘላቂነት የኦሮሞ ክልል ለአስተዳደር አመች እንዲሆን መበታተን አለባት የሚል አቋም ነው ያለኝ። ሆኖም ግን በጊዚያዊነት ፣ ትልቁን የኦሮሞ ክልል በብቃት ለማስተዳደር፣ ክልሉን ለሶስት ቀጠና በመክፈል፣ አቶ ለማ ለሶስቱ ቀጠናዎች፣ ለርሱ ተጠሪ የሆኑ፣ እንደርሱ ሆነው የሚያገለግሉ ሶስት አስተዳዳሪዎች ቢሾምና ስልጣን ዴሌጌት ቢያደርግ ጥሩ ሊሆን ይችላል። እርሱ በሁሉም ቦታ ሊገኝ አይችልም።
ለምሳሌ አዳማን የቀጠናው ዋና ከተማ በማድረ፣ የሸዋ ዞኖች ፣ አዳማ ልዩን፣ ቡራዪ ልዩን እና አርሲ ዞንን ቀጠና አንድ ወይንም የሸዋ ቀጠና በሚል ፣  ባሌ ጎባን የቀጠናው ዋና ከተማ በማድረግ የምእራብ አርሲ፣ የባሌ፣ የጉጂ፣ የቦረና፣ የሃረርጌ ዞኖችን ያካተተ ቀጠና ፪ ወይም ምስራቅ ኦሮሚያ የሚባል ቀጠና፣ ዋና ከተማው ነቀምቴ የሆነ፣ የወለጋ ፣ የኢሊባቡርና የጂማ ዞኖችን ያካተተ፣  ቀጠና ሶስት ወይም  የምእራብ ኦሮሚያ ቀጠና  ቢኖር፣ የቀጠናዎቹ አስተዳዳሪዎችም በቅርበት ነገሮችን ሊያረጋጉና የሕዝቡን ችግር ሊፈቱ ይችላሉ።
፪.  ሕግ ወጥ ተግባራት መቆም ስላለባቸው፣ የፌዴራል ጦር በክልሉ በስፋት መሰማራትና የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ፣ ማረጋጋት መቻል አለበት። አክራሪዎች የነ አቶ ለማን ዲሞክራሲያዊነትና ሰላማዊንት መዘበቻና መቀለጃ ማድረግ የለባቸው። ሕግ እንዳለ ማወቅና መረዳት አለባቸው። ማንም በማንም ዜጋ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ሊፈቀድለት አይገባም። እነ አቶ ለማ በሰላም አገር ቤት ግቡ ብለው በር በከፈቱ ከጀርባ የሚወገሩበት ምንም ምክንያት ሊኖር አይገባም። ምግበ ሲቀብላቸው ፋንድያ ነው እያሉ የሚበጠብጡትን ልክ ማስገባት ያስፈለጋል።
Filed in: Amharic