>
5:13 pm - Friday April 19, 0396

“የትግርኛ ተናጋሪዎቹ ቋሚና ተለዋዋጭ የማንነት መገለጫዎችና ሁለቱን ሕዝቦች በማቀራረቡ ረገድ የሚኖራቸው ሚና” (ዩሱፍ ያሲን) 

“ የትግርኛ ተናጋሪዎቹ ቋሚና ተለዋዋጭ የማንነት መገለጫዎችና ሁለቱን ሕዝቦች በማቀራረቡ ረገድ የሚኖራቸው ሚና ”

ዩሱፍ ያሲን ኦስሎ/ኖርዌይ

የዛሬ 19 ዓመት ገደማ ከኢትዮጵያ ሙሉ ነጻነቷን በማወጅ ኤርትራ ተብላ የዓለም የመንግሥታት ማሕበረሰብ የተቀላቀለችው የአህጉራችን አዲሲቷና የመጨረሻይቱ ሃገር በታሪክ ወስጥ በተለያዩ ስሞች ነበረ የምትታወቀው።

ነገር ግን ኤርትራ በተሰኘው መጠሪያ ተጠርታ አታውቅም ነበር ። ከበርካታዎቹ በታሪክ ከምትታወቅባቸው ስሞች ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ምድረ ባሕሪ፤ ባሕረ ነጋሽ፤ መረብ ምላሽ የተባሉት ስያሜዎች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።

ክፍለ ግዛቱ በሙሉ ሓማሴን ተብሎ የሚጠራበት ጊዜም ነበረ። ሐማሴን የተሰኘው የአንድ አውራጃ ስም ለጠቅላላው አካባቢ መጠሪያና መታወቂያ የተሰጠበትን ሁኔታ አልፎ አልፎ እንመለከታለን። በመሐል ኢትዮጵያም ሆነ በአጓራባቿ ትግራይ ሐማሴን ትናንትም ዛሬም ለደጋው ኤርትራ ነዋሪ በተለይም ለክርስቲያኑ ማሕበረሰብ መለያ አድርገው መጠቀማቸው ከዚሁ አጠራር የመነጨ ነው።

በመሃል ሃገርም አልፎ አልፎ ሓማሴን የሚለውን ስያሜ ለአካባቢው ሁላ በጥቅም ላይ ሲውል ይታያል። አንድ እውነታ ግን ሊያከራክረን አይገባም። በ1890 ጣልያን ይህንን አካባቢ በቁጥጥሩ ሥር አውሎ ለአዲሲቷ ቅኝ ግዛቱ ኤርትራ የተሰኘ ስያሜ ከመስጠቱ በፊት ኤርትራ የሚባል ቦታ፤አካባቢ ወይም ሃገር አልነበረም። አራት ነጥብ። ይሁንና ከዚያ በፊት ኤርትራ እንደ ሃገር ኤርትራውያንም እንደ ሕዝብ በዚህ አካባቢ ነበሩ ከሚሉት ጋር ጉንጭ አልፋ ክርክር ለመግጠም ዝግጁ አይደለሁም።

በዚህ እውነታ ላይ ስምምነት ከተደረሰ ዛሬ ኤርትራ ውስጥ ካሉት 9ኙ ብሔሮች አንዱና ዋነኛው የሆነው ትግሪኛ የተሰኘው በሔረሰብ ጣልያን ከመምጣቱ በፊት የነበረው ነው ወይ ? የሚለው ነው ቀጣዩ ጥያቄያችን።ታዲያ አስቀድሞ ካልነበረ እነዚያ በኤርትራ ደጋ አካባቢ በትክክል በሐማሴን፤በሠራዬና በአከለጉዛይ አውራጃዎች ነዋሪ የሆኑ ወገኖቻችን በምን ስም ነበረ የሚጠሩት ወይም የሚታወቁት?

ሰበረ፤ሰብ ቅድሚ ሚስባሩ ስሙ እንታይ ነበረ፤

ጓያ (ሰበረ) ሰውን ከመስበሩ በፊት ስሙ ምን ነበረ? እንደሚሉት አይነት መሆኑ ነው።

ይህ አባባል የዬትኞቹ ትግርኛ ተናጋሪዎች አባባል እንደሆነ አትጠይቁኝ። በትክክል አላውቀውም። አሁንም ለክርክር መቅረብ የሌለበት አንድ ሌላ ጉዳይ አለ። ስማቸው ምን ይሁን ምን ጣልያን በመጣበት ጊዜም ሆነ ዛሬ ይህ ማሕበረሰብ የሚናገረው ቋንቋ ምንነት ላይ ብዥታም ሆነ ጥያቄ አይነሳም። ቋንቋቸው ልክ በአጎራባቹ ትግራይ የሚነገረው ትግርኛ ቋንቋ ነውና። ልክ በአጎራባቹ ትግራይ ወንድሞቻቸው የሚናገሩበትን ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው ፤ያለጥርጥር። ስለዚህ እነሱም ትግሪኛ ተናጋሪዎች ናቸው። በኢትዮጵያ ትግራይ ነዋሪ የሆነው ብሔረሰብ ራሱን ተጋሩ ወይም ትግራዎት ብሎ ይጠራል።ይህ ብሔረሰብ በአጎራባች ብሔረሰቦች በተለያዩ መጠሪያዎች ይታወቃል። ይህም በኢትዮጵያችን በብሔረሰቦች መካከል ያልተለመደ አይደለም።በመሃል ሃገር በአማርኛ ተናጋሪው ዘንድ ትግሬ ተብሎ ይታወቃሉ።

ብሔረሰቡ በራሱ ማንነትም ሆነ ስለሚናገረው ቋንቋ የሚያሻማና የሚያነታርክ ቁም ነገር የለም። የሚያከራክርም ጉዳይም የለም። በአንፃሩ በኤርትራ ስላሉት ተመሳሳይ የትግርኛ ተናጋሪዎች ይህንኑ ማለት አንችልም፤አያስኬድምም። የሚናገሩት ቋንቋ ያው ከመረብ ወንዝ ባሻገር በትግራይ የሚነገረው ራሱ ትግርኛ መሆኑን አይክዱም። የእኛው የትግርኛ አነጋገር ዘዬ የጠራና የተለየ ነው የሚሉት እንደተጠበቀ ሆኖ ማለታችን ነው። የሚያከራክረን፤የሚያነታርከንና አሻሚ ሆኖ ለጽሁፋችን መነሻ የሆነው ግን በኤርትራ ውስጥ ያሉት ትግርኛ ተናጋሪዎቹ ልዩ ማንነት መለያና የብሔረሰቡ አሰያየም ጉዳይ ብቻ ነው።ሁለቱ የትግርኛ ተናጋሪዎች እንደ ማሕበረሰብ አንድ ቋንቋ እንጂ አንድ መጠሪያ ስም የላቸውም።

ይህንን በአጽንኦት የሚናገሩት የኤርትራ የፖለቲካ አድራጊዎች/አጋፋሪዎች? ማለት የፖለቲካ ፓርቲው፤መንግሥትና የሕብረተስቡ መሪዎች ናቸው። ሕዝቡም ይህንን ተከትሎ የጋራ መጠሪያ ስም የለንም ባይ ነው። ስለ ሁለት በምናወሳበት ወቅት ትግሪኛ ተናጋሪዎች ብለን ለመጥራት የተገደድነውም ለዚሁ ነው።

ለምን ትግሪኛ ተናጋሪዎች እንላቸዋለን?? ሌላ የወል መጠሪያ የላቸውም ወይ?? ለምን የላቸውም? ከሌሎቹ ከድንበር ባሻገር ከሚገኙት ብሔረሰቦች በምን ይለያሉ? በምንስ ይመሳሰላሉ??በዚሁ ረገድ ድንበር ዘለል ከሆኑት ከኩናማ፤ከአፋርና ከሳሆዎቹ በምን ይመሳሰላሉ? በምን ይለያያሉ? ለጹሑፋችን መንደርደሪያነት መነሳት ያለባቸው ጥያቄዎች ናቸው።የሁለቱ ሃገሮች ድንበር ሸገር የሆኑት ሌሎቹ እንደ ኩናማ፤ሳሆና አፋሮቹ ዘንድ ይህንን ዓይነቱ አንድ የመሆንና ያለመሆኑ ጉዳይ ሲያከራክር ወይም ሲያሻማ አንመለከትም። አያከራክርምም አይሻማምምና። ኤርትራ እንዳንድ ነጻ ሃገር ሆና እውቅና ከተጎናጸፈች በኋላ እንኳን በሁለት ሃገሮች የምንኖረው አንድ ሕዝብ ነን ማለታቸው አልቀረም።አፋሮቹ በጀቡቲም ጭምር ቅርንጫፍ ስላላቸው በሶስቱ ሃገሮች የምንገኝ አንድ ሕዝብ ነን ማለታቸውን እንዳልተውት ሁሉ ፣ለት ነው፡፡

አፋር፣ ሳሆና ኩናማ

O አንድ ቋንቋ ያለን

O አንድ ባሕል ያለን

O አንድ መጠሪያ ስም ያለን

O አንድ ሕዝብ ነን ሲሉ እናዳምጣለን። ትናንትም ዛሬም። አግባብነቱ አጠያያቂ አልሆነም። ለምን ታዲያ የትግርኛ ተናጋሪዎቹ አሰያየም የተለየ አቃቂር አስፈለገው መባሉ አልቀረም። ጉዳዩ ከፍተኛ የፖለቲካ አንድምታም አለው። ዛሬ የኢትዮጵያና የኤርትራን ሕዝብ ለማቀራረብ ከምናደርጋቸው ጥረቶች ጋር ተያይዞ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል የሚል እምነት አለን። ስለዚህ ብዙ ምክንያቶችን መደርደር ይቻላል።

በኤርትራ ያለው ትግርኛ ተናጋሪ ከሃገሪቷ 9 ብሔረሰቦች አንዱ ብቻ ቢሆንም ቅሉ፤ ከኤርትራ ሕዝብ እኩሌታ ይሆናል፤በቁጥር ደረጃ። ቋንቋቸው ትግርኛ የነፃይቷ ኤርትራ አፊሴላዊ ቋንቋ ነው። የኤርትራ ሕዝብ ቁጥርም ሆነ የሕዝቡ የበሔረሰብም ሆነ የሃይማኖት ስብጥር ስሜት ቀስቃሽ የሆነ በነፃይቷ ኤርትራ በከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚያዙት ጉዳዮቹ ዋናው ነው። ምክንያቱ እምብዛም አያመራምርም። ግልጽ ነውና። ትግርኛ ተናጋሪው በአመዛኙ የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ በመሆኑ በዚሁ ወገንና በሙስሊሞቹ መካካል ያለው ግንኙነት ይመለከታል።

የኤርትራ ፖለቲካ ድርጀቶች ብሔራዊ አንድነት የሚሉትን ለሃገሪቷ ሕልውና ሲባል በጥንቃቄ የተያዘ ጉዳይ ነው የሙስሊሙና የክርስቲያኑ የቁጥር ምጥጥን አምሳ፤አምሳ ፐርሰንት ተብሎ የሚታለፈው፤ዝንተ ዓለም። ልክ ስለ ሊባኖሱ ስብጥር እንደሚነገረው መሆኑ ነው። ስብጥሩን ማወቁም ሆነ ይፋ ማድረጉ አይታሰቤና አይነገሬነው። ሰሜን ኢትዮጵያ በተለያዩ ያካባቢ መሳፍንቶች መካከል ሲጧጧፍ በነበረው ቁሩቁስ ባንድ ወቅት እንደ ትግራይ አካል በሌላ ጊዜ ደግሞ ራሱን በቻለ አሰላለፍ ተካፋይና ተዋናይ የነበሩ መሳፍንቶች እንደነበሯት የሚካድ አይደለም።

በኢትዮጵያ ታሪክ ዘመነ መሳፍንት ተብሎ በሚታወቀው የታሪክ ጊዜ ይህንን ግዛት በማስፋፋቱ፤ሌለውን በማስገበሩ፤ካንዱ መስፍን ጋር ወግኖ በሌላው ላይ በመረባረቡ፤እንዲሁም በተለዋዋጭ የወደጅና የጠላት አፈራረጅና አሰላለፍ ውስጥ የደጋው ኤርትራ መሳፍንት ነበሩበት። በዘመነ መሳፍንቱ ማብቂያ ላይ አጼ ቴድሮዎስ ሃያልነቱን በጦር ሜዳ አስመስክረው ሁሉን በመጠረንፍ በአክሱም ከተማ ነጉሠ ነገሥት በተባሉበት ሂደት የሃዘጋ ጸዓዘጋ መሳፍንት ነበሩበት።

እነራስ ወልደ ሚካኤልን ለአብነት መጥቀሱ በቂ ይመስለናል። በኋላ ላይ አጼ ዮሐንስና አጼ ምኒልክ የዘውድ የይገባኛልና የሥልጣን የመነጣጠቁ ቁሩቁስ ወሳኝ ሚና ባይጫወቱም ከጨዎታው ውጭ አልነበሩም።እነዚያ መኳንንትና መሳፍንት የሚወዛገቡት ከላይ በተመለከትናቸው በእነዚያ በአራቱ ወይም በአምስቱ ማዕከላና በዚያኑ ዘመን የሃገሪቷ እንንብርት በነበሩት ትግራይ፤ጎንደር፤ሸዋ፤ጎጃምና ወሎ ባማከለ አካባቢ ነው። እነዚሁ ግዛቶች ናቸው እንግዲህ በተለያዩ መጠሪያዎች ቢታወቁም የታሪካዊቷና ነባሯ ኢትዮጵያ እንብርት ሆነው የሚቆጠሩት፤በታሪክ ጸሓፊዎች ዘንድ።

በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ አበሲኒያ ፕሮፐር፤አበሲኒያ ሃርትላንድ ተብለው የሚታወቁት 5ቱ ኮር ግዛቶች ማለታችን ነው።ላስታና ዋግ ምንም እንኳን የወሎ አንዱ ክፍል ሆኖ ቢታወቅም ቅሉ እንደ አንድ ራሱን የቻለ ግዛት ሆኖ መታየቱ አልቀረም።ከአምስቱ በተጨማሪ ማለታችን ነው። ልክ እንደዚህ ኤርትራም ከላይ በተመለከትናቸው የተለያዩ ታሪካዊ መጠሪያዎች ታውቃ እንደ አንድ ራሱን የቻለ ግዛት ሆና የታየችበት ጊዜ ነበረ ማለት ነው።

ይህንኑ የዘመነ መሳፍንት የእርስ በእርስ መራኮትና ቁሩቁስ ወደ ማብቃቱና አዘንብሎ አጼ ምኒሊክ የነጉሥ ነገሥት ስልጣን ጠርንፈውና አጠቃለው ባንድ ጠንካራ ማዕከል ባማከሉበት ወቅት ላይ ነበረ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ወደ አካባቢው ብቅ ማለት የጀመሩት፡፡ በአድዋ ጦርነት ዋዜማ እኔ ካንተ አላንስም የመሳፍንቶች ፉክክርና በቅኝ ገዢዎቹ አይዞህ ባይነትና የዘመናዊ መሳሪያዎች ዕርዳታ ታክሎበት ቀጥሏል፡፡ ያም ሆነ ይህ እስከ አድዋ ጦርነት ዋዜማ ድረስ

O የጋራ ቋንቋ (እሱም አነጋጋሪ ነው ባዮች አልታጡም)

O በሓበሻነት ላይ የተመሰረቱ የጋራ የእሴቶች ሥርዓት

O የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነትና ቤተክርስቲያን ቁርኝት

O መረብ ሸገር ታሪካዊና ቤተሳባዊ ዝምድናዎችና መወሳሰቦች

O ዓዲ፤ርስቲ የጉልቲ የጋራ ሥሪት

O ልማዳዊ የእንዳ አባ ሕጎችና ትድድር ሥርዓቶች ትሥሥሮች በጥብቅ ያቆራኘው አንድ መለያ ማንነት ያለው ትግርኛ ተናጋሪ ማሕበረሰብ ነበረ ማለት ያስደፍራል። ከጣልያን ቅኝ ግዛትነት በኋላ ግን ትግርኛ ተናጋሪው ከሌላው ድንበር ተሻጋሪ ማሕብረሰቦች በተጻረረ መልኩና አኳኋን በጋራ እንኳን የምንጣራበት ስም የለንም እስከ ማለት የደረሰበት ፖሎቲካዊና ባህላዊ አዲስ ማንነት አፈጣጠርና የመጎልበት ሂ ደት ዋና ዋና ምክንያቶች መመልከቱ ተገቢ ነው። በተለይም ከአድዋ ጦርነት ማግሥት። በቅድሚያ ለዚህ ያበቁ ነባራዊ ሆኔታዎን ገረፍ ገረፍ አድርገን እንመልከት። በኋላ ላይ በፖሎቲካ ኤሌቶች ወይም ልሂቃን ሆን ተብለው የተሃነደሱና/የተፈበረኩ? እንዲፋፉ የተደረጉ ግፊቶችን ለጥቆ መመልከቱ ተገቢ ነው። ሁለቱም ማለት የጣልያን ቅኝ ግዛትነት ያስከተለው ለውጥና በኋላ ለኤርትራ ነፃነት የታገሉ የፖለቲካ ሃይሎች ለየቅል የሆኑ ጫናዎች አሳድረዋል፤ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፤ያለጥርጥር።

ለዚህ ዓለም ሰገድ ዓባይ የተጣመሙ ማንነቶች (Jilted Identities-Re-imagined) በተሰኘውና በ1998 በጻፈው መጽሐፉ ሁለቱ ድርጅቶች ማለትም የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባርና ሕዝባዊ ሓርነት ኤርትራ የየራሳቸውን የተለያዩ የማንነት መለያ አቅጣጫዎች መከተላቸውን ያትታል።

በሌላ በኩል ሸቲል ቱሮንፎል የተባለ ኖርዌጂያዊ ሶሻል አንትሮፖሎጂስት War & the Politics of Identity in Ethiopia በተሰኘው አዲስ መጽሐፉ ከደም አፋሳሹ የ1998/2000 ጦርነት ወቅትና በኋላ ሁለት ወንድማማች ሕዝቦች የጋራ ትሥሥሮች ከሥር መሠረቱ የሚያናጉ እድገቶች እንደነበሩ በሰፊው ተችቶዋል።ጦርነቱ በማንነት ላይ በተለይም የትግራይ ያሉት ተጋሩ ወይም ትግርኛ ተናጋሪዎች በኤርትራውያኑ የቋንቋ ተጋሪዎቻቸው ላይያቋጠሩት ቂም አስመልክቶ ጦርነት በጠላትና ወዳጅም ስልቀረፃ ላይ የሚያሳድረው ጫና በሰፊው አብራርተዋል።

እነዚህ የጋራ ቋሚ የማንነት መገለጫዎቹ የተሸረሸሩ ቅኝ ገዢዎቹ በፈጠሩት አዲስ ፖለቲካና ማሕባራዊ ሆኔታዎች ግፊትና አስገዳጅነት አዲስ የማንነት መፈጠር መጀመሩ አሌ የማይባል ሃቅ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ቅኝ ገዢዎቹ በፈጠሩትና በኋላ ኤርትራን ለማስገንጠል በ 1962 የነጻንት ጦርነት የተያያዙት ነጻ አውጪ ድርጅቶች ለዓላማቸው መምቻ አዲስ ኤርትራዊ ማንነትና አንድ የተለየ ሃገርና የተለየ ሕዝብ ስሜት እንዲያብብ ከፍተኛ ቅስቀሳ አድርገዋል።የተወሰን ውጤትም አስመዝግበዋል ፤ያለጥርጥር። ይሁንና የሁለቱም ተግባራት ተደጋጋፊ ቢሆኑም ቅሉ ለየብቻቸው መመልከቱ ተገቢ ይመስለናል።በተለያዩ የታሪክ መጻሕፍት ተመዝግቦ እንደምናገኘው በአሰብ ወደብ ላይ በዚያን ወቅት አንዲት ትንሽ የዓሳ አጥማጆች መንደር አንድ የጣልያን የመርከብ ኩባንያ ወኪል ከሡልጣን ኢብራሂም ጋር አደረጉ በሚባለው ስምምነት የተወጠነው ኤርትራን ቅኝ ግዛት የማድረጉ ሂደት በ1890 በቀይ ባሕር ዳርቻ ኤርትራ ብለው ስም ያወጡላት መሬት በቀፈፉብት ጊዜ ፍጻሜ ላይ አድርሰዋል። በኋላ በ1893 በውጫሌ ስምምነት በተፈራረሙበት ወቅት ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና ታክሎብታል። በውጫሌ ውል መፍረስ ሳቢያ የአድዋ ጦርነት ተቀስቅሶ ድሉ የኢትዮጵያ ቢሆንም ቅሉ በኤርትራ ጣልያናዊ ቅኝ ግዛትነት ይዞታ ላይ ያስከተለው ለውጥ አልነበረም።

አንድ እውነታ ግን መረሳት የለበትም። ከወራሪው ቅኝ ገዢዎች በማበራቸውና ጎንም በመሰለፋቸው በንጉሡ አይቀጡ የአካል ቅጣት ደርሶባቸው ወደ ዘመዶቻቸው የተመለሱት ኤርትራውያኑ ስለ ኢትዮጵያና ንጉሷ ያስተላለፉት ክፉ የጠላት ምስል እንደነበረ መዘንጋት የለበትም።በአማራ ላይ በጥቅል፤ በሸዋ አማራ ላይ በተለይ ባነጣጠረ ጥላቻ የተበጃጀ ስዕል።

ከሌላው ትግርኛ ተናጋሪ የተለየ ኤርትራዊ ማንነት አፈጣጠር ሂደት

በዚሁ የተለየ ኤርትራዊ ማንነት፤መታወቂያና መለያ መበጃጀቱ ሂደት ውስጥ ከዚህ የሚከተሉት ድርጊቶችና እርምጃዎች ልብ ማለት ሊያስፈልግ ነው፤

O ኤርትራ ከአድዋ ድል በኋላ በአስከሪዎቹ ላይ የተወሰደ ቅጣት እርምጃና በንጉሱ፤በአትዮጵያና በሸዋ ላይ የፈጠረው ጥላቻ፤

O ኤርትራውያን ከተቀረው ሃገሬው (Indigenous) ሕዝብ የተለዩ ማህበረሰብ አድርጎ የፈረጀው በ1937 ጣልያን ቅኝ ገዢዎቹ ያወጡት አዋጅ፤6

O በ1936 ለኢትዮጵያ ተበጅቶ ኤርትራና ትግራይ ባንድነት ኤርትራ ተብለው የተካለሉበት አዲስ የአስተዳደር ክፍፍል፤

O አስከሪ ተብለው የሚታወቁት የኤርትራ ተወላጅ የጣልያን ወታደራዊ ተመልማዮች ወደ ሊቢያና (ትሩፑሊ)ሶማሊያ መዝመት፤

O ኤርትራን ጠቅላላ ኢትዮጵያ ወረራ ማሽኮብኮቢያ መሬት የማድረጉ መሰናዶ በአጧጧፉበት ወቅት በቅኝ ግዛቷ እንዱስትሪ፤የትምህርት፤ የከተማና ታሕታይ መዋቅር ግንባታ ያስከተለው ለውጥ፤

O የአጋሚ አውራጃ ተወላጆች ወደ አሥመራ በብዛት መፍለስና በዝቅተኛ ሠራተኛነት መሰማራት፤

ኤርትራዊ የሚባል ማንነትና ሃገራዊ ስሜትሥር የመሰደዱ ሂደትና የመገንጠሉ ትግል

በዚሁ የተለየ ኤርትራዊ ማንነት፤መታወቂያና መለያ ሥር የሰደደ የመምጣቱ ሂደት ወስጥ ደግሞ ክዚህ የሚከተሉት ድርጊቶችና እርምጃዎች ልብ ማለትሊያስፈልግ ነው

O የኤርትራ ሕዝብ የተ.መ.ድ.የክፍፍሉን ሓሳብ አለመቀበሉና ዕደሉን እንዳንድ ሕዝብና አሃድ ለመወሰን የመረጡበት ሂደት፤

O ከ 1962 እስከ 1991 ለሰላሳ ዓመታት በመጀመሪያ በኢ.አል.አፍ በኋላ በኢ.ፒ.አል.ኤፍ መሪነት በተደረገው የነፃነት ትግል የተፈጠረው ሃገራዊ ማንነትና ስሜት፤

O እነ ኢሳያስ ንሕና ንዓላማና የተሰኘው ማኒፈስቶ በክርስቲያኖች ላይ በኢ.አል.አፍ. የደረሰባቸውን ግድያና ጫና ለብቻቸው ተደረጅተው መመከቱ እቅድ፤በኋላ ላይ የኤርትራ ሕዝባዊ ሃይል(ሻዕቢያ) መፈጠር

O ትግርኛ ተናጋሪው በሔረ ትግርኛ ያሰኘው ፖለቲካዊ ትምህርት ለኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ ምልምሎች መሰጠት መጀመር

O ከወያኔ ሓርነት ትግራይ ምስረታ ወዲህ ደግሞ የኤርትራና የትግራይ ሕዝቦች ትግል ዓላማና መደምደሚያ የመለያያቱ አስፈላጊነት፤

O የ1998.2000 የድንበሩ ጦርነትና ከኢትዮጵያ ኤርትራውያን በጅምላ ማባረሩ በሁለቱ ትግርኛ ተናጋሪዎች መካከል የፈጠረው የጥላቻ ድባብ፤በዚሁ ሳቢያ ትግራይ ትግርኚ አስተሳሰብና መቀራረብ መኮሰሰ፤

O ዛሬ እንደገና በኤርትራ በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል በመፈጠር ላይ ያለው ውዝግብ ክርስትያን ወገችኖችን ማሳሰብ መጀመር፤

እነዚህንና ሌሎች በርካታ አክተሮች በኤርትራ የብሔረ ትግርኛ ኤርትራዊ ብሔርተኛነት እየጎለበተ ነጥሮ እንዲወጣ አመቺ ሆኔታዎችን ፈጥሮለታል።

ከነጻነት በኋላ ብሔረ ትግርኛ የተሰኘው አጠራር ለትግርኛ ተናጋሪው እየተዘወተረና እየተለመደ መጥቷል። ይህ በትክክል መቼ እንደተጀመረ በውል ባይታወቅም ኢ.ፒ.አል.አፍ ድርጅት ፖሎቲካ ትምህርት ማስተማሪያ ብሎ ያዘጋጃቸው ጽሁፎች አካል እንደነበረ መዛግብት ያሳያሉ። በዚሁ ላይ ብቻ መቼ ቆመ።ብሔረ ትግርኛ እነሱ አዲሱ ኤርትራዊነት ማንነት መንፍሰ ማንነት ባለቤቶች መሆናቸው ይበልጡኑ ለማስመስከር ይጥራሉ። በተለይም ኤርትራ ተገነጥላ ቋንቋቸው ትግርኛ የነፃይቱ ሃገር ቋንቋ ከሆነ በኋላ።ትግርኛውን ኤርትርኛ ማሰኘት ይዳዳቸዋል።ከእነሱ ቁጥር እጥፍ ደርብ ቁጥር ያላቸው ትግርኛ ተናጋሪ ትግራዎት በኢትዮጵያ ትግራይ መኖራቸው እየታወቀ።

ኤርትራውያን አዲሱ ሃገራዊ ማንነትና ምንነትን ለማጎልበትና ከትግራዊ ማንነት በተቃራኒው ተለይቶና ነጥሮ እንዲወጣ ልዩነቶችን ሆን ብለው ያገዝፋሉ። በአንፃሩ የጋራ ትሥሥሮችና እሴቶችን ያንኳስሳሉ።

አሁንም ሆን ተብሎ።በጋራ ትግላቸው ጊዜ የተፈጠረው ወዳጅነት ክደው ከጦርነቱ በኋላ አንዱ ሌላውን ጭራቅና የክፉ ክፉ አድርገው ይስላሉ።በኤርትራና በኢትዮጵያ መረብ ባሻገር ያሉትን ሁለቱ ትግርኛ ተናጋሪ ስብስቦችን በመካለልና በማጠር የተለያዩ መለያ መታወቂያዎች የመፍጠሩ ሂደት በምር የተያያዙ ይመስላሉ።ሁለቱም ገዢ ፓርቲዎች በዚሁ በማካለሉና በማጎልበቱ ተግባር ቢጠመዱም በኤርትራ ያለ የትግርኛ ተናጋሪ ወገን ነው ይህንን ሥራዬ ብሎ የተያየዘው።በሁለቱ ሕዝቦች መሃል የነበሩትንና ያሉትን ተመሳሳይነትና ትሥሥሮች የሚክዱትም እነሱ ናቸው።ለዚሁ በቂም ምክንያቶች ማፈላለግና ማግኘት የሚሳነን አይመስልም።አይሆንም?

የተለያዩ ተፎካካሪ ማንነቶች እርስ በርስ እየተላተሙና የእተፋጩ ነጥሮ ለመውጣት ቅርጽ ለመያዝ የሚሞክሩበት /ሂደት ፖሮሰስ እንመለከታለን።አንዳንድ ጊዜ ማንነት የማይዳሰስና የማይጨበጥ ምናብ ወለድ የፈጠረው ውጤት ነው ይሉናል ማሕበረዊ ሳይንስ ተመራማሪዎች።ይህ ደግሞ ሂደቱን ውስብስብ ያደርገዋል። ብሔረ ትግርኛ ማንነት ከተለያዩ አጓራባች ማንነቶች ጋር እየተላተመ ነው። ጥቂቶቹን ለመጠቃቀስ፤

oተመሳሳይ ትግርኛ ቋንቋ ከሚናገሩት ሙስሊም ከሆነው ጀበርቲ ማንነት፤

oትግረ ቋንቋ ተናጋሪ ባመዛኙ ሙስሊም ከሆኑት መታሕት ማንነት

oከኤርትራውያን ቆላ ሙስሊሞች በጅምላ ይፎካከራል፤

oከትግርኛ ተናጋሪው ትግራዋይ ብሔርተኛነትና ማንነት ጋር ይፎካከራል፤

oከሸዋ ኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር ታሪካዊ ፉክክሩ አሁንም ኤርትራ ነጻ ከወጣች በኋላም እንዳለ ነው፤

oከዓባይ ኢትዮጵያዊ ሃገር አቀፍ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛነት ጋር ሕልውናዊ ስጋት አለው

በዚሁ ሂደት ኤርትራዊው ትግርኛ ብሔርተኛነት ኤርትራዊ ቡሉኮ ለመደረብ ለምን እንደሚሻማ ማወቁ አያስቸግርም።ኤርትራዊነት ወደ ብሔረ ትግርኛነት ለመወሰንና ለማውረድ ሙከራው ግልጽ ነው።ትግርኛ ቋንቋውንም ኤርትርኛ ማሰኘቱ ከዚሁ ፍላጎቱ የመነጨ ሆኖ እናገኛለን።ከላይ ከተመለክትነው በርካታና ውስብስብ ሂደቶች ለምን ኤርትራ ውስጥ ያለው ትግርኛ ተናጋሪዎች ማንነትና አሰያየም አሻሚና አነታራኪ እንደሆነ በመጠኑ እንረዳለን።

ባጭሩ ውስብስብ የማንነት አፈጣጠርና አጎለባበት ሂደት ለመቃኘት ሞክረናል።እውነተኛና ገሃድ የሆኑ ወይም የምናብ የፈጠራ ውጤት የሆኑትም ሁላ።ማንነት በምናብ የተሳለ የፈጠራ ውጤተ ብቻ ሳይሆን ተለዋዋጭና በመቀያየር ያለ ፍርጅ ነው። ውስብስብነቱም ከዚሁ ጸባዩ የሚመነጭ ነው።ከትግራዋይ ጋር የጠመዱበት የፍቅርና የጥላቻ ፍርርቆሹ ለመረዳት ሊረዱን የሚችሉ መንደርደሪያዎችን አቅርበናል።አንዱ ሌላውን ዝቅ አድርጎ የመመልከት የተለያዩ አልባሌ ስሞች መሰጣጠቱ ምስጢርም ገለጥለጥ ይላል ብለን እንገምታለን።

ማጠቃለያ

የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ባንድ ሃገርልጅነትም ሆነ በሁለት ሃገር ልጅነት ጎን ለጎን መኖር የጂኦግራፊና የታሪክ ግዴታቸው ነው።የሁለቱ ሃገር ሕዝቦች እነዚህ ሁለት አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ ሳይነጋገርና ሳይቀራረብ ይቀራረባሉ ብሎ ማሰቡ የዋህነት ነው። እንዲያውም በእኔ እምነት ለሁሉም መቀራረብ ጥረቶች ቅደመ ግዴታ ነው፤የእነሱ መቀራረብ። አንድ የትግርኛ አባባል አለ።እቅጩን አላውቀውም እንጂ። የተጣሉ የአጎት ልጆች ወንድማማች ወላጆቻቸው ሳይነጋገሩ ልጆቻቸው ይነጋገራሉ፤ይደራረሳሉ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው የሚል። ትክክልነው። በአንዳንድ ሃገር ወዳዶች ለኢትዮጵያ ሕልውናና አንድነት ጠንቅ ሆኖ የሚታያቸውን የሁለት ትግርኛ ተናጋሪዎች እንደገና እንዲወዳጁና እንዲቀራረቡ ማድረግ ጸረ-ኢትዮጵያ ቃል ኪዳናቸውን እንዲያድሱ መርዳት የሚመስላቸው የፖለቲካ የዋሃን አይታጡም። አሻግሮ መመልከት የተሳናቸው ናቸው።በተቃራኒው መቀራረቡና መነጋገሩ ወሳኝነት ያለው እርምጃ ነው፤የሁለቱን ሃገሮች ሕዝቦች ለማቀራረብ የሚያስችል ሃሳብ ለመለዋወጥ ዛሬ የዚህ የተሰበሰብንበት ዋናው ዓላማ።

አመሰግናለሁ

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

ለኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝቦች ወዳጅነት ኮንፊረንስ ሳን ሆዜ፣ ካሊፎርኒያ ማርች 12 እስከ 14 ቀን 2010 የቀረበ

Filed in: Amharic