>

የክፋት ዋጋው ስንት ነው? የንስሃስ መግቢያስ ከወዴት አለ? (አሰፋ ሀይሉ)

የክፋት ዋጋው ስንት ነው? የንስሃስ መግቢያስ ከወዴት አለ?
አሰፋ ሀይሉ
— ዊኒ፣ ዊኒ፣ ዊኒ…?! ‘Mother of the Nation’?!
ዊኒ ማንዴላን ድፍን ዓለም ያውቃታል፡፡ የኔልሰን ማንዴላ ሚስት ናት፡፡ ባሏን ከነእንከኑ ከነምናምኑ ከመቀበል አልፋ፤ የራሱንና የልጆቹን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሎ የተሠለፈበትን ትግል እንኳን ልትቃወመው ከጎኑ ሆና አይዞህ፣ አትጨነቅ፣ ለልጆቹም ለሁሉም ነገር እኔ አለሁልህ እያለች ባሏን ከራሷና ከልጆቿ አስበልጣ – ለመላ ደቡብ አፍሪካውያን ነፃነት አሳልፋ የሰጠች – ድንቅ፣ መንፈሰ-ፅኑ ሴት ናት፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ የወጣላት ቆንጆ፣ እና አመለ-ሸጋ፡፡ የተማረች፡፡
እንዲያውም – ደቡብ አፍሪካውያንን ከጥቂት ነጮች የዘር የበላይነት አገዛዝ ወይም ባርነት ሥርዓት (አፓርታይድ) አውጥቶ – በገዛ ሀገራቸው እኩልነትን እንዲቀዳጁ ለማስቻል – ለበርካታ ዓመታት በተደረገው እልህ አስጨራሽ – እና ብዙ ዋጋ የተከፈለበት – የሞት ሽረት የነፃነት ትግል እንቅስቃሴ ውስጥ – ይህች ደመግቡ ሴት ሴት – ዊኒ ማንዴላ – እንዲያውም – ለ27 ዓመታት ሙሉ በከርቸሌ ታጉሮ እንዲኖር ከተፈረደበት – ከባሏ ከኔልሰን ማንዴላ ይልቅ – ወይም ይበልጥ – ከፍተኛ ድርሻ ያለውን የለውጥ ትግል የመራችው፣ እና ያደረገችው፣ እና ከፍተኛውን መሥዋዕትነት በተግባር የከፈለችው፣ የአፓርታይድ ጠባቂ አርበኞችን ግፍ በቆራጥነት ያስተናገደችው – እርሷ እንደሆነች – ብዙዎች – ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከሩላታል – በአደባባይ ቆመው ይመሰክሩላታል፡፡
ያን የጥንታዊውን የአይሁድን ህግ – የጥንታዊውን የሃሞራቢን ህግ ተከተለች እያሉ የሚያሟት የሚያወግዟትም ብዙ ናቸው፡፡ ‹‹ዓይን ያጠፋ ዓይኑ ይጥፋ›› የሚለውን በመተግበር፡፡ በእርግጥም ዊኒ – በመጀመሪያ ልቅም አርጋ የተማረች – አስገራሚ የፖለቲካ ንቃት ያላት – በምንም መስፈርት ራሷን ችላ ፍርጥም ባለ አንደበት መናገር የምትችል – ሰላማዊ፣ ሽቅርቅር ሴት ነበረች፡፡ አስገራሚ አፍቃሪም ነበረች፡፡ በኔልሰን ማንዴላ ውስልትናና ቤተሰቡን ለአደጋ የሚያጋልጥ ህቡዕ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተስፋ የቆረጠችው የመጀመሪያ ሚስቱ ልጆቹን ይዛ ወጊድልኝ ብላ ትዳሩን አሽቀንጥራ ስትጥለው.. ዊኒ ነበረች – ራሷሁሉን ረስታ – እርሱም ሁሉን እንዲረሳ – እንደመልዓክ ተመስላ ለህይወቱ የደረሰችለት፡፡
እና ዊኒ ጋር በፍቅር ቀልድ አልነበረም፡፡ ከልቧ አፈቀረችው፡፡ ከልቧ ወደ እናትነት ማዕረግ ተሸጋገረች፡፡ ከልቧ በፅናት የመጣባትን ሁሉ ለመቀበል ከባሏ እና ከልጆቿ ጎን ትርሷን ንክስ አርጋ ቆመች፡፡ ዊኒ – በማንዴላ ህይወት መቃናትና ማንነት ውስጥ – ከሚስትነትም በላይ የማትተካ የትግል አጋሩ ነች፡፡ የማትተካ ደራሹ፡፡ የማትተካ አዳኝ መልዓኩ፡፡ በተለይ እርሱ ወደማይመለስበት ከርቸሌ ሲወረወር – ልጆቿን እንደካንጋሩ በጉያዋ ሥር ሸሽጋ – እርሷግን – የባሏን የትግል መፈክር አንስታ – ለሰፊው የትግል መስክ – በቆራጥነት – የተነሣች – አስገራሚ – እጅግ አስገራሚ ቁርጠኝነትን የተላበሰች – አስገራሚ ሴት ናት በእውነት፡፡
ግን አፓርታይድ ማለት የዘር የበላይነትን ከሚሰብከውና በግልፅ አደባባይ ሊተገብረው ከተንቀሳቀሰው የ20ኛው ክፍለዘመን ብሔራዊ ሶሻሊዝም (ወይም ናዚ)፣ አሊያም በዘር መድልዎ በተመሳሳይ መልኩ ከተለከፈው የብሄራዊ ፅንፈኞች ሥርዓት (ከፋሺዝም)፣ ባልተናነሰ መልኩ – በአንድ ዘር የበላይነትና በሌላ ዘር የበታችነት እምነት – ከራስ ፀጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ የተለከፈ – ዓለም ናዚዝምን ተባብሮ ሲያጠፋ በዝንጋኤ ሳያጠፋው የተወው – የ20ኛው ክፍለዘመን አስፀያፊ እና አሰቃቂ የሰው ልጅ በሰው ልጅ እንደ እንስሳ የታየበትን ሥርዓት ያራመደ ብሔራዊ የፋሺስቶች ሥርዓት ነበር፡፡  አፓርታይድ በብዙዎች ምንም ዓይነት ስም ይሰጠው፣ በምንም ዓይንት መልኩ ይቅረብ – ነገር ግን – በሃሳብም ሆነ በተግባር – ይህንን ያልነውን ነበር፡፡
እና ያን ያህል አስከፊ መሆኑ ደግሞ – ያን የሚታገሉትን ሁሉ – የመጨረሻውን አስከፊ መንገድ ከመጠቀም ወደኋላ እንዳይሉ ገፍቷቸዋል፡፡ ‹‹ባይ ኦል ሚንስ ነሰሰሪ›› እያሉ ነበር የሚያበረታቱት – እነ ቦብ ማርሌይ፣ እነ ማልኮም ኤክስ፣ እነ ጃንሆይም ሆኑ ሌሎች የወቅቱ የነፃነት አቀንቃኞች፡፡ በማንኛውም መሣሪያ፣ በማንኛውም መንገድ፣ በማንኛውም ዓይነት ሥልት – ያን የደቡብ አፍሪካ የናዚ ሥርዓት – እንታገለዋለን – ብለው የቆረጡ የነፃነት አርበኞችን ነው የፈጠረው – የሥርዓቱ ክፋት፡፡
ያን ሥርዓት ለመታገል ማንዴላ የህሊናውን ልጓም በጥሶ – ሠላማዊ ሰዎችን ጭምር ለፈንጂ አደጋ እስከመዳረግ ለገፋ እኩይ ድርጊት ራሱን አጭቷል፡፡ ያን አስከፊ ሥርዓት ለመፋለም – ማንዴላ – የገዛ ነፍሱን ለሞት ፍርድ አሠልፎ ሰጥቷል፡፡ ያን አስፀያፊ ሥርዓት ለመታገል – ወፍ ዝር በማይልበት – ሰው ሄዶ በማይመለስበት – ሩቅ የደሴት መጣያ – 27 ዓመት ሙሉ ተጥሎ አሣሩን በልቷል፡፡
ዊኒስ? እሷም… እንደዚያው! እንዲያውም ባትብስ?! እይህን ሁሉ የጭካኔ በትር ከልጆቿና ከባሏ፣ ከትግል ጓዶቿና በየዕለቱ በውሻ ክራንቻ በአደባባይ ከሚዘለዘሉት ወገኖቿ ጋር ሆና የተቀበለችው – እና ከሽንፈት ይልቅ የመጨረሻውን መራር መስዋዕትነት ለመክፈል የቆረጠችው – እና ያን በመሆኗም አባታቸው ወደ እስር ከተወረወረባቸው፣ ከእርሷም በቀር የኔ የሚሉት ለሌላቸው ልጆቿ እንኳ ሣያዝኑ – ሰው-ከሌላቸው አቅመ-ቢስ ህጻናት ልጆቿ እጅ እየነጠቁ ወደእስር የተጣለችው፣ የተገረፈችው፣ የተደፈረችው፣ እና በአፓርታያኖቹ – ብዙ ብዙ ተነግሮ የማያልቅ መከራና ግፍን የተቀበለችው – ዊኒ ማንዴላም – የሥርዓቱ ጥርስ ይበልጡን በቆዳዋ ዘልቆ ውስጧን በገዘገዛት ቁጥር – እርሷም ደግሞ ይበልጡን ቆራጥ፣ ይበልጡን ለምንም ነገር የማትራራ፣ ይበልጡን የትኛውንም ዓይነት የትግል አማራጭ መንገድ ለመጠቀም ዓይኗን የማታሽ – በዘረኞቹ የአፓርታይድ ሠልፈኞች ጭካኔ የተነሣ – እርሷም ከእነሱ ያልተናነሰ ጭካኔን ተላብሳ የተገኘች – መራር፣ ቆራጥ፣ አብዮታዊ የነፃነት ታጋይ ሆና ተገኘች፡፡
ይህ ነበረ የዊኒ ማንዴላ ለአፓርታይድ የተከፈለ ከፍተኛ የማንነት መስዋዕትነት፡፡ ከአፍቃሪነት – የመጨረሻውን ጥላቻ ወዳነገበ መራር ተፋላሚነት፡፡ ከተከላካይነት ወደ አጥቂነት፡፡ ዱላን ከሚቀበል ሰለባነት… ዱላውን ለመመከት… ዱላን ወደሚመዝ… አልሞት ባይ ተጋዳይነት፡፡ ይህ በአብዛኛው ሰው ህይወት ውስጥ የተከሰተ፣ በመራራው የፀረ-አፓርታይድ ትግል የሁሉን ሰው አዕምሮ የፈተነ – ለፍትህ የተከፈለ – መራራ የህሊና መስዋዕትነት ነው፡፡ ኔልሰን ማንዴላ በ‹‹ሎንግ ዎክ ቱ ፍሪደም›› መጽሐፉ ይህን የዊኒ ማንዴላን ወደ ምሬት የመቀየር ጉዞ… እንዲህ በማለት ነበር የገለጸው፡-
‹‹አፓርታይድ በግሌ ካደረገብኝ የግፍ ሥራ ሁሉ አልተሸነፍኩለትም፡፡ ለአንዱም ነገር አልተበገርኩም፡፡ ለምንምም ነገር እጄን አልሰጠሁም፡፡ ግን አፓርታይድ በአንድ ነገር ብቻ እኔን አሸንፎኛል፡፡ ልቤን ሰብሮታል፡፡ ከአፓርታይድ ክፉ ድርጊቶች ሁሉ – በታሰርኩበት ሆኘም ሆነ – ከዚያ በህይወት ወጥቼ ልጠግነው፣ ልመልሰው የማልችለው ትልቁ የህይወት ስብራቴም እርሱ ነው፡፡ ዊኒ ማንዴላን ስለነጠቀኝ፡፡ አፓርታይድ ምን ያህል የክፋት አቅም እንዳለው የተረዳሁት – ዊኒ ማንዴላን ያህል የፍቅር ልብ የተሸከመች ሴት – እንዴት አድርጎ ወደማላውቃት ፍጹም አስገራሚ ምሬት የተሞላች ሴት አድርጎ እንዴት እንደቀየራት ስመለከት ነው፡፡ አፓርታይድ የኔይቱን ዊኒ ቀምቶኛል፡፡ ያን አስከፊ ሥርዓት በሁሉ ነገር ይቅር ብዬዋለሁ፡፡ በዚህ ግን በምንም ቃል ከምገልጸው በላይ ልቤን ሰብሮታል፡፡ ይህን ግፉን መቼውንም ይቅር አልለውም፡፡››
ማንዴላ እንዲህ ቢልም – ብዙዎችም የዊኒ ማንዴላን ኃይል ወደተቀላቀለበት ነውጠኛ የጥቁሮች ትግል መቀላቀል (ወደ ራዲካልነት ማዘንበል) በቋሟ ቢኮንኗትም – ብዙዎች ግን – አሁንም ድረስ – ልፍስፍስ አቋምን ከተላበሰውና ጥቁሮችንም በለዘብተኛ አቋሙ ካስጠቃው – ከባሏከኔልሰን ማንዴላ ይልቅ – ለጥቁሮች እውነተኛ መብት የታገለች – እውነተኛውን ከባድ መስዋዕትነት የከፈለች – እውነተኛዋ የጥቁሮች መብት ታጋይ፣ እውነተኛዋ የትግሉ አራስ ግሥላ፣ እውነተኛዋ ፀረ-አፓርታይድ እመጫት ነብር – በትክክል እንፍረድ ካልን – ዊኒ ማንዴላ ናት! እያሉ ያንቆለጳጵሷታል – ሽንጣቸውን ገትረው ይከላከሉላታል!!
ምንም ይሁን ምን – ዕድሜ እነ ማዲባና ዊኒን ለመሣሠሉ ቁርጥ የነፃነት ጀግኖች.. – ያንንም ለደገፉ እልፍ አዕላፍ ነጮችም፣ ጥቁሮችም ይሁንና –  አሁን ዛሬ – ያ ክፉው የ20ኛው ክፍለዘመን የአፍሪካ ናዚዝም – ያ የተጠላ የፋሺስቶች የዘር የበላይነትን – ያለምንም ምንተ እፍረት – በአደባባይ – ሊተገብር በአፍሪካ ሕዝቦች መካከል የቆመ – ያ አሳፋሪ ፖሊሲ – አፓርታይድ – በስም እና ታሪክ – እና አሁንም ካልተቀረፈ የኑሮ አቅም ልዩነት በቀር – በደቡብ አፍሪካ ምድር – ዳግመኛ ላይመለስ – ከስሟል፡፡ ነገር ግን – የመጥፎ ነገር ክፋቱ – ጥሎ የሚያልፈው ቁስል በቀላሉ አለመሻሩ ነው፡፡ ጠባሳው በቀላሉ አለመጥፋቱ ነው፡፡ እና ደግሞ ከምንም በላይ – እንደጉንፋን – በጤነኛውም ላይ – መጋባቱ ነው፡፡ ይጋባል ጥፋትም እንደጉንፋን፡፡ ሰዎች አንተን በዘርህ፣ በቀለምህ እየለዩ የመጨረሻውን የጭካኔ ድጊት ሲፈጽሙብህ – ሁልጊዜ ያን ችለህ፣ ችለህ፣ ችለህ.. ተሸክመህ መኖር ይሳንህና – አንተም መልሰህ – እንደነሱ ያለ – አንዳንዴም የባሰ – የክፋትና የጭካኔ በትር ይዘህ ትነሣለህ፡፡ ይጠሉሃል – አንተም አምርረህ ትጠላቸዋለህ፡፡ ያደሙሃል – አንተም ትዋጋቸዋለህ፡፡ ይገድሉሃል – አንተም ታጠፋቸዋለህ፡፡ ይበቀሉሃል – አንተም ባገኘህበት ትበቀላቸዋለህ፡፡ ይህ ነው የሚጋባብህ፡፡ ልክ እንደ ዊኒ፡፡
አዎ፡፡ ዘረኝነት መጥፎ ነው፡፡ መጥፎ ቫይረስ፡፡ ይጋባል፡፡ ይጋባል ብቻ ሳይሆን ይዛመታል፡፡ እንደ ተዛማች ሀገራዊ ወረርሽኝ፡፡ እንደ አጣዳፊ የማይለቅ አተት፡፡ ሀገር ምድሩ ላይ ይጋባል፡፡ በመጥፎ ሥርዓት ውስጥ መኖር እና ያለመኖር – በአዕምሮህ፣ እና በሰብዕናህ፣ እና በማንነትህ ላይ ያለው አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ተፅዕኖም ያ ነው፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ – ጤነኛ አስተሳሰብ ኖሮት – በተሟላ መልካም ሰብዕና ላይ እንዲገኝ ካስፈለገ – እንዲያ ሆኖ የሚገኝ መልካም ትውልድን መቅረፅ፣ ወይም ያን ዓይነት መልካም ሰብዕናን የተላበሱ ሆኖም መገኘት ብቻውን በቂ ዋስትና አይሆንም፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን – መጥፎ፣ ዘረኛ፣ እና በዘር የበላይነትና የበታችነት የሚያምን፣ የዘር መጠቃቀምን፣ ዘርን የተመረኮዘ ጥቅምንም ሆነ ጉዳትን መቀበልን የሚፈቅድ፣ የዘር መድልዎን እንደ ዓይነተኛ ፖሊሲ የሚያራምድ ሥርዓት፣ ያን ለማራመድ ምቹ የሆነን በር የከፈተ ሀገር፣ የሚሰብክ የፖለቲካ ማህበረሰብ… አስካለ ድረስ – እንዳልነው – የአስተሳሰብ ኢቦላው – ራሱኑ እንዳለ ከነነፍሱ – አሊያም ተቃራኒውን የጥላቻ አቅጣጫ ይዞ – መልካም አስተሳሰብን የተላበሱ ሰዎችን ራሱ – ወደዱም ጠሉ – የልክፍቱ ሰለባ ማድረጉ አይቀርም፡፡ ዘረኝነት – በከአንዱ ወደሌላው የሚጋባ፣ ንፁህ አስተሳሰብ ወደያዘው ሰው ራሱ የሚዛመት ቀሳፊ ቫይረስ እስከሆነ ድረስ – አካባቢው ሁሉ፣ ሀገር ምድሩ ሁሉ – ከአሉታዊው የዘረኝነት ቫይረስ ንፁህ መሆኑን – መቼውንም ቢሆን ማረጋገጥ – የሁሉም መልካም የሰውልጅ አስተሳሰብ እንዲቀጥል የሚፈልግ ሀገርና ትውልድ ኃላፊነት ብቻ ሣይሆን – እጅግ አስፈላጊ የጋራ ህልውና አስተማማኝ መሠረትም ነው፡፡
አሁን ወደ ዊኒ እንመለስ፡፡ የአፓርታይዱን ህገመንግሥት መጣሳቸውን ለማመን፣ በኃይልና አመፅ ተግባር ላይ መሠማራታቸውን ለማመን፣ ያን ያደረጉት የሰውን ልጅ እኩልነት ለማምጣት እስከሆነ ድረስ እንደማይፀፀቱበትና ሞትንም ለመቀበል ዝግጁ እንደሆኑም ጭምር በፍርድ ችሎት ለመናገር አንዳችም ፍርሃት ያላደረባቸው ኔልሰን ማንዴላ – ከ27 ዓመት እስር በኋላ ፍፁም ለዘብተኛ ሰው ሆነው ወጡ፡፡ ዊኒ ማንዴላ ግን – 27 ዓመት ሙሉ አምርረው የታገሉት የአፓርታይድ ሥርዓት – በ27 ዓመት ቆይታ – ጀብደኝነትን የተላበሱ ደመመራራ ሴት አድርጎ ጠበቃቸው፡፡ እና ተለያዩ፡፡ 27 ዓመት ሙሉ በናፍቆትና ሰቀቀን ሲጠባበቁ የኖሩ ፍቅረኞች፣ ባልና ሚስቶች፣ በ27 ዓመታት አለንጋ አንዱ ጠባሳን፣ አንዱ ትኩስ ቁስልን በማፍራቱ – በአቋም፣ በሃሳብ ዓለም፣ በእውን ዓለም፣ በአተያይ፣ በአዕምሮ፣ በስሜት፣ በሁለመናቸው ተለያዩ፡፡ ልጆች ወልደዋል፡፡ የልጅ ልጆችም አፍርተዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ እንዳይለያዩ አላገዳቸውም፡፡ እነሆ አሳዛኙ የማንዴላዎች ስብራት እውን ሆነ፡፡ አፓርታይድ – ነፍስህን አይማረው፡፡
ብቻ ግን ያ ሁሉ እንደምንም አለፈ፡፡ ወይም ታለፈ፡፡ የሆነውም ሆነ፡፡ አትሁን ያለውም ቀረ፡፡ ትናንት አልፏል፡፡ ዘንድሮም ተባጅቷል፡፡ ከፊታችን ያለው የከርሞው ነው፡፡ የአፓርታይድ አራማጆች – እና እነ ኔልሰን ማንዴላ – ለከርሞው መጪ ዘመን ሲሉ – እንዳይሆን እንዳይሆን ያለፈውን ካቻምናን – በንስሃ ተሻግረው ማለፍን መረጡ፡፡ በሐይማኖት አባቶቹ በእነ ዴዝሞን ቱቱ አጋፋሪነት – በኅዝብ ሸንጎ ፊትም እየቀረቡ – ብዙዎች የአፓርታይድ ሠላቢዎች – እና ብዙዎች የአፓርታይድ ሰለባዎች – ንስሃ ገቡ፡፡ ንስሃ ማለት ሶስት ነገር ነው ያለው፡፡ ጥፋትን በይፋ ማመን፣ በጥፋቱ መፀፀትና፣ ለወደፊቱም መቼም ወደዚያ ዓይነቱ ድርጊት ድርሽ ላለማለት ከራስ ጋር ቁርጥ ምህላን መፈጸም ነው፡፡ እና በዚያ የንስሃ መንገድ ብዙዎች የአፓርታይድ ፖሊሶች በድለናል፣ ጥፋተኛ ነን፣ አፍረናል፣ አንደግመውም፣ ይቅር በሉን አሉ፡፡ እነ ማዲባም በበኩላቸው በግፍ ተገፋፍተን ለሠራነው መጥፎ ሥራ ሁሉ ከልባችን ተፀፅተናል፣ አንደግመውም፣ አፎ በሉን አሉ፡፡
ዊኒ ማንዴላስ? ዊኒ ማንዴላ ግን – እንዴት ሆኖ ነው ለሠራሁት ፍፁም ተመጣጣኝና በታሪክ ፊት እንደፅድቅ በምቆጥረው ነገር የምፀፀተው? አሉ፡፡ በሠሩት ነገር ሊያፍሩ የሚገባቸው ሌሎች አሉ፡፡ እኔ ለሠራሁት ነገር በፍፁም አላፍርም፣ አልፀፀትም፣ ነገም ተመሣሣይ ግፍ ካጋጠመኝ ያንኑ ነገር ደግሜ አደርጋለሁ፣ ካደረግኩትም በላይ ባደርግ ሁሉ ደስ ይለኛል፡፡ ትናንትም፣ ዛሬም፣ ወደፊትም ይህ ነው የማይናወጥ አቋሜ… ብለው ለያዥ ለገራዥ የሚያስቸግሩ ‹‹ብሔራዊ እናት›› ሆኑ፡፡ የብዙዎችም መነጋገሪያ ሆኑ፡፡ ድፍን ዓለምን አነጋገሩ፡፡ ቆይ ግን ሰው.. ‹‹ብሔራዊ እናት›› ተብሎ ሰው እንዴት እንዲህ ለይቅርታ ይገላገላል? የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ የብዙዎችም ጥያቄም ሆነ ግርምት ያ ነው፡፡
በእርግጥ – ይህች ፅኑ ሴት – ዊኒ ማንዴላ – በአንድ ወቅት ልበ-ስስ አፍቃሪ እና ሰፍሳፋ የልጆች እናት እንደነበረች ለሚያስታውስ ሁሉ – ያቺን ስሱ ሴት ቀምቶ – ያሁኗን ልበ-ደንዳና ሴት የፈጠረው – ምን እና ማን እንደሆነ – በትክክል ይገነዘባል፡፡ ዊኒ ፈልጋ ይህን አልሆነችም፡፡ ይህን ያደረጋት፡፡ ቆዳዋን ዘልቆ የገባው አረመኔያዊው የአፓርታይድ ሥርዓት ነው፡ በውስጧ አመርቅዞ ያልበቃው ጠባሳ ነው፡፡ አፓርታይድ የለኮሰባት – እስካሁንም ከልቧ ሊበርድ ያልቻለው – ያ የዘረኝነት ፍም ነው – ለዚህ ሁሉ ኃላፊነቱም መውሰድ ያለበት፡፡ ዊኒን ምን እንደነካት አትጠይቃት፡፡ እርሷ በቅርቡ ብዙዎችን አስለቅሳ በሞት ተለይታለች፡፡ ከሶስት ቀናት በፊት ደግሞ የባልተቤቷ የማዲባ ሙት ዓመት በደማቅ ሥነሥርዓት እየተከበረ ነበረ፡፡ ማንዴላዎችን ያስታወሰ ሁሉ ያን አስከፊ ሥርዓት ሊረሣ አይገባውም፡፡ እንዴት እንዳለፉትም፣ እንዴት እንዳላለፉትም ጭምር፡፡ አሁንም እደግመዋለሁ – አፓርታይድ – ነፍስህን አይማረው፡፡
ባጠቃላይ – በደቡባዊ አፍሪካ – የአፓርታይድ አቧራ – የሁሉንም ቤት ነው ያንኳኳው፡፡ ገራም ነጮች እና ቤተሰቦቻቸው ሁሉ – ሀገሪቱን በሞላ ወደናዚ የኮንሰንትሬሽን ካምፕ ሊቀይሯት በዳዳቸው የለየለት የአፓርታይድ ሥርዓት አራማጆች አኳኋንና ነገረ-ሥራ ሁሉ – የኋላ ኋላ – በስተመጨረሻ – ህሊናቸው እስኪደማባቸው ድረስ – ተፀፅተዋል፡፡ ተፀይፈውታል፡፡ ከጥቁሮቹ እኩል – ያረጉት ይገቡበት ጨንቋቸዋል፡፡ እና የጥቁሮቹ ንዴት መወጫም ሆነዋል፡፡ እና ያልተጋራው አልነበረም በእውነቱ ጠባሳውን፡፡
ጥቁሮች በእርግጥ ዋነኞቹ አበሳቸውን ቆጣሪ፣ አበሳቸውን አወራራጅ ሰለባዎች እንደሆኑ ምንም ጥያቄ አያስፈልገውም፡፡ ተበልተውበታል፡፡ ተለብልበውበታል፡፡ ተገድለውበታል፡፡ የዋሃኑ አፍሪካውያን ጥቁሮች – በአፓርታይድ – የማይፈልጉትን እንችለዋለን ብለው ያላለሙትን ክፋት አላብሷቸው – እንደ አውሬ ተናካሽ፣ ተናዳፊ ሆነዋል፡፡ በቃ ያለፈውን ሁሉ የጨረገደ፣ ርህራሄ የሌለው የዘረኝነት ቫይረስ – ሁሉንም አበላልቶ – ሁሉም ተበላልቶ – ከመተላለቁ በፊት ግን – ንስሃ – በእነ ማዲባ በኩል – በእነ ዴክለርክ በኩል- በእነሊቀጳጳስ ዴዝሞንቱቱ በኩል – በፈጣሪ አምላክ በኩል – ሁሉንም ሊሠርይ – ሁሉንም ሊዋጅ – ጣልቃ ገባ፡፡
ይህን ልብ ብለን እንሰነባበት፡፡ ወፍጮ ቤት የገባ ሰው ዱቄት ሳይለብስ አይወጣም፡፡ እኛም የሰው ልጆች የረገጥነውን አካባቢ አየር ሳንምግ ህልውናችንን ማስቀጠል አንችልም፡፡ ልክ እንደዚያው ሁሉ – በግፍ ሥርዓት ያለፈ ሰው ሁሉ ደግሞ – በአንድ ወይም በሌላ መልኩ – የዚያን ሥርዓት አስከፊ ቡናኝ ሳይምግ- የዚያን ሥርዓት አስጠሊታ አምቡላ ሳይጋት – አሊያም የዚያን ሥርዓት አተላ ሳያጣጥም  – ከቶውን ማለፍ አይቻለውም፣ አይሆንለትም፡፡ ይህ የምርጫ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ማንም ቢሆን – ያለፈበት ህይወት – ወይም ያለፈበትን ህይወት ውጤት ነው፡፡ እና በሕይወት ስንኖር – ማናችንም በማናችንም ላይ ለመፍረድ የዘገየን፣ ለይቅርታና ምህረት የፈጠንን፣ ለንስሃ የማናመነታ ሆነን – ህይወታችንን የምር – ብንኖራትስ?!! ‹‹ለመልካም ህይወት እንትጋ፤ ክፋትን ከውስጣችን ነቅለን እንጣል! ለንስሃ ልባችንን እንክፈት!›› በዕለቱ ለስንብት የመረጥኳቸው ቃላት ናቸው፡፡ የኖሩትን ያሳርፍ፡፡ ያሉትን ይባርክ፡፡ መልካም ጊዜ፡፡
ፎቶግራፉ (እጅግ ከከበረ ምስጋና ጋር)፡-
‹‹Makholu Matete saved to Winnie Mother of the Nation››
Filed in: Amharic