>
5:13 pm - Saturday April 20, 3033

ለዝች አገር የስጋት ምንጭ "ዘረ-እኛ"ነት ወይስ "ጽንፈኛ"ነት?!!? (በፍቃዱ ሞረዳ)

ለዝች አገር የስጋት ምንጭ “ዘረ-እኛ”ነት ወይስ “ጽንፈኛ”ነት?!!?
በፍቃዱ ሞረዳ
ይህች ‹‹ ዘረኝነት›› ወይም ‹‹ ዘረ እኛነት›› የምትለዋ ነገር ትርጉሟ ሳይረዳኝ ላረጅ ነዉ መሰል፡፡ አሁን አሁንማ አትገባበት ቦታ የለም፡፡ ሳቅም፣ ለቅሶም፣ ማስነጠስም፣ ማግሳትም፣ … መተቸትም…መፃፍም…
  አንድ አርቲስት፣ጋዜጠኛ፣ አክቲቭስት፣ ፖለቲከኛ፣ ሰባኪ…ጊዜና ሁኔታ በፈቀደለት መጠን የወገኑ አንደበት ሆኖ ቢዘፍን፣ቢዘምር፣ ቢጮህ…ምኑ ኃጥያቱ?
ሃጫሉ ዛሬ በሐረርጌ፣በባሌ፣ በቦረና…‹‹ወገኖቻችን በግፍ እየተገሉ ነዉ ፤ እናንት የመንግሥት ሹማምንት፣ የሕዝብን ሠላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት አለብን ያላችሁን ሰዎች እልቂቱን አስቁሙልን፡፡ ካልሆነም እራሳችንን ለመከላከል እንገደዳለን…›› ሲል አቤቱታ አቀረበ፡፡ አስፈላጊ መስሎ በታየዉ መንገድና መድረክ፡፡ ትክክልም ነዉ፡፡
ነገ ደግሞ ከሱዳን የተነሳ እብሪተኛ የጎንደርና የጎጃምን ወገኖቻችንን ቢጨፈጭፍና መንግሥት ለአፀፋ ቢያመነታ ወዳጄ መሀሪ ደገፋዉ በሙያዉ ተመሳሳይ መልዕክት ቢያስተላልፍ፣ ጥሪ ቢያሰማ፣ ስለወገኑ ቢጮህ ‹‹ ዘረኛ›› ሊባል ነዉ? ሃጫሉስ የሱዳኖችን ወረራ አዉግዞ ስለተጎዳዉ ሕዝብ ቢጮህ?  መሀሪ ስለሀረርጌ ወገኖቹ ተቆጭቶ ቢያንጎራጉር…?
     ወይስ አጫሉ መድረክ ላይ ከያዛት የአባገዳ ባንዲራ ጋር ነዉ ሰበቡ?  እርሱም ቢሆን መረራ ጉዲና ይዞት ሲገኝ፣ አብይ አሕመድና ለማ መገርሳ ኮት አሰርተዉ ሲለብሱት ኃጥያት ያልሆነ ሃጫሉ ሲይዘዉ አቧራ ማስነሳቱ ለምንድነዉ?
   ከአሁን ቀደም በአንዳንድ መድረኮች ላይ ለመናገር እንደሞከርኩትና እንደማምንበትም ‹‹ዘረ እኛነት›› አያስፈራኝም፡፡ አደጋም አይደለም፡፡ ለመሸነጋገያ ካልሆነ በስተቀር ‹‹ዘረ እኛነት›› የሌለዉ ዘረሰዉም የትም የለምና፡፡
 ይልቁንስ አደጋ የሚያስከትለዉ በእያንዳንዱ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ፍልስፍና፣ አመለካከት…ዉስጥ ያለዉ ፅንፈኝነት ነዉ፡፡ ራስ ወዳድነት፣ ተኮፋሽነት፣ ስግብግብነት፣እሳቤ የበላይነት፣ ሕልመኝነት… የሚመነጨዉ ከፅንፈኛ አመለካከት ነዉ፡፡ እርግጥ ለፅንፈኝነት የሚገፋፉ ምክንያቶች የሉም ማለት አይቻልም፡፡ በተለያዩ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ ምክንያት ወደጎን መገፋት፣መዋረድ፣ ፍትህ አልባነት… ሲሰፍን ፅንፈኝነት ይፈጠራል፤ ይገናልም፡፡ ዛሬ በዓለማችን ላይ ገንኖ የሚታየዉ ሁኔታም ይኼዉ ነዉ፡፡ የተዛባዉን ሚዛን በማስተካከል አደጋዉን መቀነስ ግን ይቻላል፡፡
  ዓላማዬ ስለፅንፈኝነትና ዘረ እኛነት ለማስተማር አይደለም፡፡ዛሬ ከምናየዉና ከምንሰማዉ ነገር በመነሳት ወደአሳሳቢ አቅጣጫ እየመሩን የሚመስሉ ነባርና አዲስ አቆጥቋጭ አደገኛ አመለካከቶች በሀገራችን መኖራቸዉን ማስተዋሌን ከስጋቴ ጋር ለማካፈል ነዉ፡፡ የግሌን በጎ ፍርሃት፡፡ አንድ ማናችንም የማንክደዉ ሀቅ አለ፡፡ ዛሬ በሀገራችን ዉስጥ ማንም ማንንም በጉልበት ወይም በብልጠት አሸንፎ ፍላጎቱን ማስፈፀም አይችልም፡፡
     ለራስ የሚመኙትን መብትና ነፃነት ሌላዉን ለመከልከል መሞከር ትርፉ ሥርዓተ አልበኝነት ፈጥሮ ነገሮችን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊመራዉ ይችላል፡፡ ዉጤቱም ማንንም ላይጠቅም ይችላል፡፡ ከአዙሪትም አያወጣንም፡፡ ሁሌም በጎ ማሰብ ጥሩ ነዉ፡፡‹‹ ሰከን›› ለማለት ያህል ነዉ፡፡ የሰከናችሁ አስክኑ ፡፡ ይኼዉ ነዉ የአንዳንድ ጋዜጠኞች ቅዠት፡፡ይህችም ጎጠኝነት ናት?
Filed in: Amharic