>
5:13 pm - Saturday April 19, 9169

ለከንቲባነት  እና ለማዘጋጃ ቤት ሓላፊነት የእኔ እጩዎች!?! (ኤርሚያስ ለገሰ)

ለከንቲባነት  እና ለማዘጋጃ ቤት ሓላፊነት የእኔ እጩዎች!?!
ኤርሚያስ ለገሰ
               ***
 #ታሪካዊ መንደርደሪያ
ወቅቱ የኢትዮጵያ የሚሌኒየም አመት (2000 ዓም) መገባደጃ አካባቢ ነበር። የአዲስ አበባ ዳግም ምርጫ ተካሂዶ የከተማው ከንቲባ፣ ካቢኔ ፣ የክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚና ካቤኔዎች በኢህአዴግ ቢሮ የምንመድብበት ነበር። ስራው በፍጥነት መሰራት ስለነበረበት አቢይ ኮሚቴ እና ንዑስ ኮሚቴ ተደራጅቶ የሚፈፀምበት ነበር።
አቢይ ኮሚቴው የሚመራው በአቶ በረከት ሲሆን ተመልማዬችን ፕሮፓዛል ይዘን የምንመጣው የኮሚቴው አባላት አቶ አርከበ እቁባይ፣ ህላዌ ዬሴፍ፣ ካሚል አህመድ፣ ፀጋዬ ኃ/ማርያም፣ ፍሬህይወት አያሌው፣ ይሳቅ አበራ(ቆሪጥ) እና እኔ ነበርን።
እናም አቢይ ኮሚቴው በበረከት ቢሮ ተቀምጠን ለመዲናይቱ ከንቲባ፣ ምክትል ከንቲባና ካቢኔ የሚሆኑትን መምረጥ ጀመርን። ለአዲስ አበባ ምክርቤት ከተወዳደሩት አባላት ውስጥ ለከንቲባነት እጩ ሆነው የቀረቡት አቶ ኩማ ደመቅሳ፣ ወይዘሮ አስቴር ማሞ እና አቶ መላኩ ፈንታ ነበሩ።
 በመጀመሪያው ዙር  በረከት በአቶ መላኩ ፈንታ ላይ ቅሬታ በማንሳቱና ብአዴን ባለበት እንዲቀጥል ትፈልጋለች በማለቱ መላኩ ፈንታ ውድቅ ተደረገ።በክርክሩ ወቅትም ሳይነሳ ቀረ። እናም የተቀሩት ሁለቱ ኦህዴዶች ሆኑ። ኩማ ደመቅሳና አስቴር ማሞ። አሁንም በረከት የድርጅቱ (የባለቤቱ ወይዘሮ አዜብ በተለይ) ፍላጐት ወይዘሮ አስቴር ማሞ ከንቲባ እንድትሆን ነው በማለት እንቅጩን ነገረን። ሁላችንም ተቃወምን። በተለይ አርከበ በንዴት እየተንጨረጨረ ቅሬታውን አቀረበ። ይህም ሆኖ የድርጅቱ እና የሚስታቸው ውሳኔ በመሆኑ የሚቀለበስ ነገር እንደሌለ ተነገረን። የመጨረሻ ቀጠሮ ለሚቀጥለው ሳምንት አስረን ተለያየን።
 የቀጠሮው ቀን እስኪደርስ የነበሩት ቀናት የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ለነበርን ሰዎች ከፍተኛ ሴራ ከጠነሰስንበት ጊዜያቶች የላቀውን የሚይዝበት ነበር።
 በአንድ በኩል በካድሬዎች አማካኝነት የአዲስ አበባ ሕዝብ በወቅቱ የመከላከያ ሚኒስትር የነበረው ኩማ ደመቅሳ ከንቲባ እንዲሆን መፈለጉት አሰራጨን። ከሰላሳ ሺህ በላይ መጠይቆችን በማዘጋጀትና በመሙላት 75 በመቶ ኩማን፣ 15 በመቶ መላኩ ፈንታንና 3 በመቶ ወይዘሮ አስቴርን ከንቲባ ሆነው ማየት እንደሚፈልግ አመላከትን።
 በሌላ በኩል ተነባቢ ለነበሩ የግል ጋዜጦች ቀጣዩ ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ እንደሚሆን የውስጥ መረጃ በመስጠት ጋዜጦቹን በኩማ ፎቶ አደመቅናቸው። አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ድርጅቱ ሃሳቡን ቀይሮ ኩማ ደመቅሳን ከንቲባ ለመመደብ ተገደደ።
ከሁሉም አስቂኙ ነገር አቶ ኩማ ከንቲባ እንደሚሆን የተነገረው ምክርቤቱ ሊጠራ በዋዜማው ስለነበር ድንግርግሩ ወጥቶ ነበር። በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ያነበበው የአስተዳደሩ የአመቱ መሪ እቅድ የተመለከተው የእለቱ እለት ነበር። በአካልና በስም የማያውቃቸውን የካቢኔ አባላት ጽብፃብ ኮስተር ብሎ ሲያነብ ራሱ ያዘጋጃቸው ይመስል ነበር። ኩማ ደመቅሳ እንዲህ ነበር።
                    ***
ከላይ የተጠቀሰውን ታሪክ ወደ ኃላ ሄጄ የማነሳበት የተወሰኑ ምክንያቶች አሉኝ። እስከ አሁን ድረስ የአዲስ አበባ ከንቲባነት የሚገኘው በህዝብ ምርጫ ሳይሆን በፓርቲ ምደባ እና ክፍፍል ነው። ከንቲባውም ተጠሪነቱ ለፓርቲውና ለመደበው ግለሰብ ነው። ይሄ ባልተለወጠበት ሁኔታ የፓርቲ ምደባ ላይ መሻኮትና እርስ በራስ መደባደብ የለውጥ ሂደቱን እንዳይፋጠን ከማድረግ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም። ከዚህ አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ “ በሁሉም መራጭ ህዝብ ያልተመረጠ ሰው ፕሬዝዳንት (“ከንቲባ”) ነኝ ሊል እንደምን ይቻለዋል?” በማለት የተናገሩትን ማስታወስ ይበጃል።
 እናም ጠቅላይ ሚኒስትሩን መጨቅጨቅ ያለብን በቀጣዩ ምርጫ የአዲስ አበባ ከንቲባ የሚሆነው ከ1 ሚሊዬን የአዲሳባ መራጭ ውስጥ ከግማሽ ሚሊዬን በላይ የመረጠው ብቻ እንዲሆን ቻርተሩን እንዲያሻሽሉልን ነው። የአዲስ አበባ አጠቃላይ መራጭ ህዝብ ወደ አንድ ሚሊዬን ይጠጋል የሚል ታሳቢ ወስጄ ነው። እናም ይሄ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ ፍፁም ፍላጐት ከመሆኑም በላይ የመዲናይቱን የፓለቲካ ሽኩቻና የዘር መጓተት ተቋማዊ በሆነ መንገድ የሚፈታ ይሆናል። አንድ ድምፅ ለአንድ ሰው የሚል መርሆ ያለው የፕሮፌሰር መረራ ፓርቲም በውሳኔው ደስተኛ እንደሚሆን አልጠራጠርም። መቼም በዚህ የውሳኔ ሃሳብ የሚከፋ ሰው ካለ ወይ ዲሞክራሲ አልገባውም አሊያም ለአዲስ አበባ ህዝብ ክብር የለውም። አልፎ ከሄደም የአዲስ አበባን ህዝብ ይጠላል። ድፍን የአዲስ አበባ ህዝብ በግሉ የምርጫ ውሳኔ ከንቲባውን መርጦ ሲደሰት የሚከፋው ከሆነ ቦታው አማኑኤል መሆን አለበት።
ከዚህ በተጨማሪም ከግማሽ ሚሊዬን በላይ የሚሆነው የአዲስ አበባ ህዝብ የመረጠው ከንቲባም ደረቱን ነፍቶ “ ሕዝብ የመረጠኝ ነኝ!” ማለት ይችላል።ትችላለች።
              ***
 ወይዘሮ ዳግማዊ ሞገስ 
የአዲስ አበባ ከንቲባ
ከላይ የተቀመጠው የቻርተር ማሻሻያ የውሳኔ ሃሳብ ወደ ተግባር እስኪለወጥ ድረስ የሚመደበው ከንቲባ በህዝብ ያልተመረጠ በመሆኑ ራሱን እንደ ሽግግር ከንቲባ መውሰድ ይኖርበ(ባ)ታል። ይሄ(ቺ) ከንቲባ ጊዜያዊ እንደመሆኑ(ኗ) መጠን በተቻለ መጠን የህዝቡን ውስን ፍላጐቶች ቢያ(ታ)ሟላ ጥሩ ይሆናል።
በመሆኑም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨዋውን ፣ ያላሳፈሮትን፣ በችግር ጊዜ ከጐኖ ቆሞ ያኮራዎትን የአዲስ አበባ ነዋሪ ፍላጐት ለማሟላት ወይዘሮ ዳግማዊ ሞገስን በከንቲባነት ፣ ኢንጂነር ታከለ ኡማንን ደግሞ በማዘጋጃ ቤት ሓላፊነት እንዲመርጡ ፍቃድሆ ይሁን። የዛሬ ውሳኔዎትን መልሰው አጢነውት ሽግሽጉን በአስቸኳይ ይፈፁሙ። አለበለዚያም ምክንያቶን ያስረዱ።
ወይዘሮ ዳግማዊ ሞገስ የአስተዳደሩ ከንቲባ እንድትሆን የማቀርባቸው ምክንያቶች ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው።
#ምክንያት አንድ :- ዳግማዊት አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገች ናት። የኮልፌ ቀራንዬ ልጅ የሆነችው ዳግማዊት አዲስ አበባን ከግር እስከ ራሷ ታውቃታለች። የህዝቡን ማንነት እና ስነ ልቦና ጠንቅቃ ትገነዘባለች።
#ምክንያት ሁለት: – ዳግማዊት ወደ አዲስ አበባ መስተዳድር ስናመጣት የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ መምህር ነበረች። በዛን ሰአት እድሜዋ ከ21 እስከ 23 አመት ውስጥ እንደነበር አስታውሳለሁ። በአሁን ሰአትም እድሜዋ ከ33 የሚበልጥ አይመስለኝም። ዳግማዊት በዩንቨርስቲው መምህር ሆና ልትቀር የቻለችው በትምህርቷ በጣም ጐበዝና የከፍተኛ ማዕረግ ምሩቅ ስለነበረች ነው። የዩንቨርስቲ መምህርነቷን ለቃ ስትመጣ በፍፁም ህዝብ የማገልገል ፍላጐት ሰንቃ የመጣች ሲሆን በዝዋይ አላጌ በነበረው የሁለት ወር ስልጠናም በቅርበት ማረጋገጥ የቻልኩት ሁለንተናዊ እይታዋን ነው።
በነገራችን ላይ በአንድ ወቅት ዩንቨርስቲውን ለቃ መምጣቷ ቅር እንደሚያሰኘኝ ሳልደብቅ ነግሬያታለሁ። ያለምንም ጥርጥር በዩንቨርስቲ ቆይታዋ ቢራዘም ኖሮ ሶስተኛ ዲግሪዋን ይዛ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት የምትወዳደርበት አቅም ታዳብር ነበር።
#ምክንያት ሶስት :- ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የአዲስ አበባ ምክርቤትና የካቢኔው አባል ስለሆነች ክቡርነትዎ እሷን ጊዜያዊ ከንቲባ ለማድረግ ህገ መንግስትና ቻርተር መጣስ አይጠበቅቦትም። በአዲስ አበባ ታሪክም የሚያስቀምጡት ጥቁር ጠባሳ ሳይሆን የተስፋ ብርሃን ይሆናል። ወጣቷ ወይዘሮ ከክፍለ ከተማ ጀምሮ የመዲናይቱን ቢሮክራሲና አሰራር የተመለከቱት ስለሆነ የእሮሶ ድጋፍ ከተጨመረበት በአጭር ጊዜ የለውጥ ሃዋርያው መሪ ትሆናለች።
#ምክንያት አራት: – እስከማውቀው ድረስ ወይዘሮ ዳግማዊት ሌብነት እና ዝርፊያን የምትጠየፍ እንስት ናት። ሙሉ ፍላጐቷ ህዝብ የማገልገል ስለሆነ እንደዚህ አይነት ራስን ዝቅ የሚያደርግ ወራዳ ስራ ውስጥ እጇን የምትነክር አይመስለኝም። እርሶም በአሁን ሰአት የምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሰጧት ይሄን ተመልክተው ይመስለኛል።
#ምክንያት አምስት: – ወጣት ዳግማዊት የጠንካራ ሴት ተምሳሌት ናት። ይህቺን አርአያ የምትሆን ጠንካራ ሴት እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በከንቲባነት መሾም ትልቅ ክብር ነው። የሴትየዋ ስም በታሪክ ውስጥ ሲነሳ የእርሶም ስም አብሮ ይነሳል። እስቲ ይታዮት  ከእለታት አንዲቷ ቀን የማዘጋጃ ቤት የምክር ቤት አዳራሽ ገብተው የተሰቀሉትን ከመጀመሪያ እስከ ዛሬ የነበሩ ከንቲባዎች ውስጥ የአንዲት ሴት ፎቶ ብቻ ተሰቅሎ ሲመለከቱ የሚሰማዎት ስሜት? ያውም በእርሶ ዘመን። የዛኔ እኛም “ታሪክ በታሪክ ሰሪዎቹ ተሰራ!” ብለን ለመፃፍ እንታደላለን። እናም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይረፍድብዎ ታሪክ ይስሩ።
                ***
    ኢንጂነር ታከለ ኡማን የአዲስ አበባ
                ማዘጋጃ ቤት ሓላፊ
ኢንጂነር ታከለ ኡማንን የማዘጋጃ ቤት ኃላፊ እንዲሆን የምፈልግበት ምክንያት በአጭሩ ልግለፅ። እንደገባኝ ከሆነ ኢንጂነር ታከለን የፈለጉበት ምክንያት በዋናነት የኦሮሞ ብሔረሰብ ተወላጅ በመሆኑ ሳይሆን የእርሶ የለውጥ ሐዋርያ ቡድን ውስጥ የታቀፈ ሰው ስለሆነ ይመስለኛል። ባይሆን ኖሮ የድርጅቶ ፕሮግራም የተገለፀበትን ህገ መንግስት እና ቻርተር እስከ መጣስ የሚያዘልቆት አይመስለኝም። እንደዚህ ከሆነ ዘንዳ ህግ ሳይጥሱ ይሄን የእርሶ የለውጥ ሐዋርያ ቁልፍ ቦታ ላይ መመደብ የሚቻልበት እድል አለ።
በእኔ እምነት በአዲስ አበባ የስልጣን እርከን ውስጥ ሶስት ቁልፍ ቦታዎች አሉ። ከንቲባ፣ የማዘጋጃ ቤት ሐላፊ እና የፓርቲ ጽህፈት ቤት ሐላፊ። እነዚህን ሶስት ቦታዎች በእርሶ የለውጥ ሐዋርያ ቡድን መቆጣጠር ከቻሉ ሌላው እዳው ገብስ ነው። ዛሬ የማዘጋጃ ቤቱ እና የፓርቲው ጽህፈት ቤት የተያዘው የቀን ጅቦች በሆኑት የህውሓት ካድሬዎች በሆኑት ሓይሌ ፍስሃና ተወልደ ነው። እነዚህን አደገኛ ሰዎች ወደ መጡበት ማሰናበት ጊዜ የሚሰጠው አይደለም። ለበለጠ መረጃ አጠገቦት ቺፍ ኦፍ ስታፍ ያደረጉትና የቀድሞ የአዲስ አበባ ጥቃቅን ሐላፊ የነበረውን ፍፁም አረጋ መጠየቅ ይችላሉ።
ግልባጭ:  ለፍፁም አረጋ
 (ቺፍ ኦፍ ስታፍ)
   ለማ መገርሳ
  ( ፕሬዝዳንት)
Filed in: Amharic