>

ዝምተኛ ሕዝብ እና የቅጣት ድንጋዮቹ!!! (እንዳለጌታ ከበደ)

ዝምተኛ ሕዝብ እና የቅጣት ድንጋዮቹ!!!
እንዳለጌታ ከበደ
በደለኞች የትም አሉ – ድኩማንን ገፍተውና ገፍትረው የሚጥሉ፣ ምንዱባንን አስጨንቀው ጉቦና መማለጃ የሚቀበሉ አሉ፡፡ በሚያስተዳድሯቸውና በሚመሯቸው ሰዎች ልብ ውስጥ የሣቅ ሣይሆን የለቅሶ ድምጽ ማድመጥ የሚወዱ፣ በሕዝብ ‹ፍቃድ› ወይም በአመጽ ብዛት ስልጣን ከያዙ በኋላ የራሳቸውን የድልና የድሎት መዝሙር እንጂ የሕዝብን ብሶትና የሀዘን እንጉርጉሮ የማይሰሙ፣ ዕንባዎቻቸውን የማያብሱ፣ አሉ፤ የትም አሉ፤ በደለኞች እዚህም እዚያም፣ እላይም እታችም አሉ፡፡
አንዳንድ በዳዮች የበደላቸውን ልክ አያውቁትም፡፡ ሚዛኑን አይለኩትም፡፡ ቀን የጣላቸው እንደሆነ ግን በሕዝባቸው ላይ ከጣሉት ቀንበር  ይልቅ እነሱ ትከሻ ላይ የሚወድቀው መከራ የከበደ ይሆናል፤ ‹እሱም ጨካኝ ነበር፤ ጨካኝ አዘዘበት›ብሎ የሚዘፍንባቸው እና የሚዘባበትባቸው ይበዛል፡፡
ታሪክም የሚነግረን እውነት ይሄ ነው!!!
አንዳንዴ እነዚህን፣ ‹በደለኞች›ን የሚያስጠነቅቁ፣  ሕዝብን ማስቀየም ልክ አይደለም የሚሉ፣ የመፍትሔ ሃሳብ አመንጭተው አማራጭ መንገድ የሚጠቁሙ የበደለኛው የቅርብ ወገኖችና ሊቃውንት ይኖራሉ፡፡ የእነዚህ፣ መሪዎቻቸውን በምክር፣ በተግሳጽ እና በዘወርዋራ መንገድ  ፈር ለማስያዝ  የሚሞክሩ ሊቃውንት እጣ ፈንታም የታወቀ ነው፡፡ በደለኞቹ እነዚህ ሊቃውንት እንዳይደርሱባቸው  እና ከእቅዶቻቸው እንዳያናጥቧቸው  ከአፍንጫቸው ስር ያርቋቸዋል፤ ሊቃውንቱ ግን የሚያምኑበትን በመናገራቸው እስር እና እንግልት እንደሚጠብቃቸው  ቀደም ብለው ቢገምቱም የሚሰማቸውን ከመናገር ወደኋላ አይሉም፡፡ በደለኛው ቀን እስኪጥለው፣ በቅሎውን ሌላ ሰው እስኪጭነው፣ የሹመት ወንበሩን ሌላ ሰው እስኪነጥቀው አይጠብቁም፤ በደለኛው ውሃ ወደማያመነጭ ጉድጓድ ተጥሎ  የሁሉም (የከሳሽ ወገን) ቅጣት እስኪዘንብበት አይጠብቁም፡፡ እነዚህን ዓይነት ሰዎች ለመሆን ጀግንነት ይጠይቃል፡፡
‹እናውቃለን፤ ብንናገር እናልቃለን›  ማለት በለመዱ ሰዎች መካከል ውለው፣ የመሪዎቻቸውን ሃሳብ ለመገዳደር የሞከሩ ብዙ አይደሉም፤ ይህን አንቀጽ በምጽፍበት ጊዜ እንኳን ለበደለኞቹ ‹ቅርብ› ሆነው የታወሱኝ  ከአንድ እጅ ጣት  አይሞሉም፡፡
ሰሞኑን አቶ ከተማ ይፍሩ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሆነው ይሠሩ በነበረበት ዘመን፣ ማለትም በ1963 ዓ.ም ለቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የጻፉላቸው፣ ባለሦስት ገጽ ሰነድ አነበብኩ፡፡ ሰነዱ አጼው ከመቼውም በላይ እንዲነቁ እና ስለ‹አልጋቸው› ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግና ከበደለኞች ወገን ተፈርጀው ክብራቸው እንዳይወድቅ አብዝቶ የሚያስጠነቅቅ ነበር፤ አልጋ ወራሻቸው  በመንግሥቱ ስልጣን  ተካፋይ እንዲሆን፣ ሕገ መንግሥቱ ብዙ ክፍተትና ያልተብራሩ ጉዳዮች ስላሉበት ተሻሽሎ ሕዝቡ ከሞግዚትነት ወጥቶ እራሱን ለማስተዳደር የሚያስችል ሌላ ሕገ መንግሥት እንዲታወጅ አበክሮ የሚያስረዳ ነበር፡፡
አቶ ከተማ ይህንን ማስታወሻ ለአጼው ሲጽፉ፣ ስታሊን በሕይወት ዘመኑ እጅግ የተፈራና የተከበረ እንደነበር፣‹..ከጊዜ በኋላ ግን አስከሬኑ እንኳን እረፍት እንዳያገኝ  ካለበት ከሌኒን ጎን ተነስቶ ተዋርዶ ሌላ ዝቅተኛ ስፍራ እንዲቀበር ተደርጎ ያመልከው የነበረው የሞስኮ ሕዝብ የመጨረሻ ጥላቻ እንዲያድርበት›  እንደተደረገ አትተዋል፤ ‹በሌላ በኩል ደግሞ ካሚል አታቱርክ ለሀገሩ የዋለው ውለታ በሕይወት ዘመኑ ብቻ ሳይሆን ከሞተም በኋላ  የቱርክ ሕዝብ እጅግ የከበደው ስለነበር እስከዛሬ በእያንዳንዱ ቱርክ ዘንድ የተቀደሰና የተመሰገነ ሆኖ ይኖራል፡፡…በሕይወት ሳሉ በየቦታው ሃውልት ማስቀረጽ መንገድና ትምሕርት ቤት እንደዚሁም ሆስፒታል  በስም ማስጠራት ከንቱ ነው፡፡ የእስታሊን ታሪክ ለዚህ መልካም ምሳሌ ነው፡፡ በሞተ በሁለት ዓመት ስሙ የተጠራው ሁሉ እንዲፋቅ ተደረገ….›በማለት ምሳሌ ጠቅሰው ተናግረው ነበር፡፡ ነበር፤ ጃንሆይ ግን ምክሩን ችላ አሉት፤ ችላ ያሉት ጉዳይ ሦስት ዓመት ጠብቆና ‹አብዮት ነኝ› ብሎ፣አይነኬ መሳዩን ሥርዓታቸውን አፈነዳው፡፡
የታወቀ ነው፤ በሕይወት መንገድ ላይ አውቀንም ይሁን ሳናውቅ ገፍተን ገፍትረን የምንጥለው ሰው አናጣም፤ ‹በደለኛ የሚያስብለን ግን አውቀን በድፍረት ሳናውቅ በስህተት የፈጸምነው ስህተት ብቻ አይደለም፤ ሕዝቡን ይቅርታ ሳንጠይቅ፣ ማሻሻያ እና የማቃኛ እርምጃ ሳንወስድ፣ ከሠራነው ሰናይ ሥራ ይልቅ ልንሠራው ሲገባ ችላ ያልነው  መልካም ነገር ከበዛ እና የድክመታችን ቁጥር  በልጦ ከተገኘ ወደ ‹ጉድጓድ› መጣላችን አይቀርም፡፡
…እነዚህ የጠቀስናቸው ‹በደለኞች› ወደ ጉድጓድ በሚወረወሩቡት  ጊዜ ብቻቸውን አይወርዱም፤ ከጉዳዩ ጋር  ንኪኪ የሌላቸው ቤተሰቦቻቸውም እነሱን ተከትለው ዝቅ ይላሉ፡፡ የሥራ ባልደረቦቻቸውንም ያስከትላሉ፡፡ ብቻቸውን አይወድቁም፡፡ በደለኞችን ሲገስጹ እና አቅጣጫ  ሲያመለክቱ የነበሩ ሁሉ ለጊዜውም ቢሆን ሊታሰሩ ይችላል፡፡ ሲወድቁ የማይመለከታቸው  ሁሉ በዚህ የቅጣት ባቡር እንዲሳፈሩ እና የጓድጓዱ ቤተሰብ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ አዲስ መንግሥት ተሰይሞ፣ ስዩመ ዲሞክራሲ ነኝ ብሎ ካወጀ በኋላ፣ ደርግ እነአክሊሉ ሀብተወልድንና መሰሎቻቸውን እንዴት ነበር ያሰቃያቸው? (ሀዲስ አለማየሁ እና ከተማ ይፍሩ ላይ  የገነነ እንግልት እንዳልደረሰባቸው ይነገራል – የአጼው ሹማምንት የነበሩ ቢሆንም ስርአቱን ለመቀናቀን ያደረጉትን ትግልና ትንቅንቅ ቁጥር ውስጥ በማስገባት፡፡) ኢሕአዴግስ ደርግን ካባረረ በኋላ ስንቶቹን ነው፣  በስም መመሳሰልና ታሪክ ወደፊት በሚገልጠው ምክንያት የቀይ ሽብር ተዋንያን ነበራችሁ  ብሎ ለዓመታት ወህኒ ቤት ወርውሮአቸው ሲያበቃ፣  ‹በስህተት ነው የታሰራችሁት›  ብሎ የፈታቸው?
ይህ ሁሉ ማለቴ፣ በደለኛው የሀገር መሪም ይሁን የቀበሌ አስተዳዳሪ፣ ቀን መጥቶ በፍርድና ርትእ ምኩራብ በሚቆምበት ጊዜ፣ የራሱን ወደ ጉድጓድ  መወርወር ብቻ ሊያስብ አይገባውም ለማለት ነው፡፡ ‹የሆነው ይሁን እችለዋለሁ፤ እቋቋመዋለሁ›  ወይም ‹ይበለኝ የእጄን ነው ያገኘሁት!› በማለት ብቻ የሚገታ አይደለም፤ ‹ታሪክ የጣለበትን ሃላፊነት›  ለመወጣት ሲዳክር ጊዜ (ፍቅር፣ ጨዋታና ክብር) የነፈጋቸው ቤተሰቦቹስ? መስመር አትለፍ እያሉ ሲያስጠነቅቁትና ለሕልውናው እጅጉን ሲሰጉ የነበሩ የቅርብ  ባለሟሎቹስ? በማይመለከታቸው ጉዳይ ታስረው  በደለኛው መንግሥት ትንፋሽ ተገኝቶባችኋል  ተብለው በጥርጣሬ ብቻ ታስረው፣ መሥራት የሚችል ጉልበታቸውና መብራት የሚችል ዕውቀታቸው  ባክኖ  እንዲቀር  አለፍርድ ባክነው የሚቀሩ ምሁራንስ?
…ስንቱ ነው፣ በእጁ የገባውን ስልጣን መከታ አድርጎ፣ ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለውን ነባር ብሂል እንደማተቡ አክብሮ፣ የማይገባውንና ያልተፈቀደለትን በእጁ ለማስገባት የሚተጋው? ስንቱ ነው፣ ወዳጆቹ ወይም ዘመዶቹ የመምራትና የማስተዳደር ዕድል ስላገኙ ብቻ፣ ስማቸውን መታወቂያ አድርጎ፣ ለሌሎች የተከለከለውን በር አስከፍቶ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ‹ልማታዊ ሀብታምነቱን›  የሚያስመሰክረው? ስንቱ ነው፣ ላይ ያሉት የእኛ ሰዎች ናቸው ብሎ የገዢው  መደብ ብሔር አባል በመሆኑ  ብቻ ቀድሞ የመገኘትን ስልጣን ለራሱ ሰጥቶ፣ በህንጻ ላይ ህንጻ በቤት ላይ ቤት ደርቦ፣ ራሱን ከፍ ባለ ማማ ላይ ሰቅሎ፣ ታች ያሉትን ለማየት እና ሽንቁራቸውን ለመድፈን፣  ጣር የበዛበት የኑሮ ጣራቸውን  ለመክደን የተጸየፈ?
በዚህ ጊዜ ነው፣ ‹እውነት ሆይ የት ነው ያለሽው?›  የምንለው፤ ታሲሳ ኤባ (በ1938 ዓ.ም) ያስነበበን ግጥም በለሆሳስ የምናነበንበው፡፡
             እመንገድ ሄጄ ብመለስ
             እህቴ ጠፍታ ሲለቅስ 
             አልገባህ አለኝ ነገሩ
             እውነት ስትጠፋ ካገሩ
             አታገኛትም እያሉ
             ያስፈራሩኛል ሰዎች ሁሉ
             አምላክ የለሞይ  በመንበር
             እውነት ስትጠፋ ስትቀር፡፡
ያም ሆኖ አንድ ቀን አለ፤ ይሄ፣ ‹ቀን ያነሳው ቅል ድንጋይ ይሰብራል› ብሎ መተረት የለመደ ማኅበረሰብ፣ አንድ ቀን የፍትህ ጸሃይ ወጥታ እውነት በዳዩንም ተበዳዩንም ወደ አንድ ምኩራብ ጋብዛ አውጫጭኝ  እንደምትጠራ ያምናል፤ በዚህ ምኩራብ የተረሱና የተዘነጉ እንዲሁም  አቧራ ለብሰው የከረሙ ፋይሎች ይገለጣሉ፡፡
…የሆነው ሆኖ ‹በደለኛው›ን የሚከስሱ ይመጣሉ፤ከየጓዳቸው ወጥተው፣ ወደ ጉድጓድ ሊወረወር ወደተዘጋጀው ሰው ይቀርባሉ፡፡ ሰውየው ስልጣኑን በአግባቡ ባለመጠቀሙ ሰበብ፣ በሕይወት ዘመናቸው ምን እንዳጎደለባቸው ማስመዝገብ ይጀምራሉ፤ በሥራ እጦት ምክንያት  ስንት ሰው ተምሮ ተንከራታች እንደሆነ፣ ዩኒቨርስቲ ገብቶ ‹ባለዲግሪ ሆንኩ፤ የተማርኩትን ተግብሬ ራሴንም ቤቴንም ሀገሬንም ልለውጥ ነው› የሚለው ምኞታቸው እንዴት ውሃ እንደበላው ይመሰክራሉ፤ ምሁሩ ሃሳቡን የሚገልጽበት፤ አቋሙን የሚያውጅበት መገናኛ ብዙኃን ተነጥቆና በከንቱ ባክኖ እንደቀረ ማሳያ እየጠቀሱ ይናገራሉ፤ ፍዳውን ሲቆጥር የቆየ ሁሉ የሚያወጣው  ጉድ አያጣም፤ በዚህም የተነሳ እውነት ራሷ በደለኛውን ትሞግተው ትይዛለች፡፡
…በዚህ ጊዜ ነው፣ አንድ ሰው ከየት እንደመጣ ሳይታወቅ በበደለኛው ፊት ፊት ላይ ምራቅ መትፋት ሳይበቃው፣ ክፉ ቃል ተናግሮ ቅስሙን አንክቶ መስበር ሳይበቃው፣ ድንጋዩን አንስቶ የበደለኛውን ግንባር የሚፈነክተው፡፡
ይኼ ቅጣት ሰንዛሪ፣ተረቱ ላይ እንዳገኘነው ለሃያ ምናምን ዓመት ነው ድንጋዩን በልቡ ይዞ ሲዞር  የቆየው፡፡ (እንደዚህ ዓይነት ሰዎች የምንበዛ ይመስለኛል፤ ቂም የምናቁርበት፣ በቀል የምናቆይበት ጉድጓድ በልባችን ውስጥ የተቆፈረልን) ዝም ስንል፣ የሚደረግብንን፣ የሚጫንብንን ልብ ያላልን እንመስላለን፤ ግንድ ሆኖ ከደስታችን ሲጋርደን ቆየው መሪ/ፓርቲ ተገንድሶ ሲወድቅ ግን ሁላችንም ምሳራችን ከየደበቅንበት አውጥተን ግንዱ ላይ እንረባረባለን፡፡
‹ሕዝብ ዝም ሲል ያስደነግጠኛል› የሚሉ አሉ አይደል? እውነት ነው፣ ዝም ያለን ሕዝብ ነው መፍራት! ‹ሰቀቀኑን በሆዱ አጥሮ› የሚውለውን ሕዝብ ነው መጠንቀቅ! በእነዚህ ሕዝቦች ልብ ውስጥ እልፍ  ድንጋዮች አሉ፤‹ድንጋዮቹ› ግን አይታዩም፤ ፊታቸው ላይ አንዳች ቅሬታ ስለማይስተዋልም አስተዳዳሪዎቹ  እነዚህ ሰዎች ይቀጡናል፤ ይበቀሉናል ብለው አይገምቱም፡፡ የፓርቲው ደጋፊ ይመስላሉ፤ በአባልነትም ይመደባሉ፤ ለድጋፍ ሰልፍ ይወጣሉ፤ ተቃዋሚዎችን ይቃወማሉ፡፡ የልባቸውን  የሚያስተውል ግን የለም፡፡
የ‹በደለኛው› ከሳሾች ‹ሞልቶላቸው› የሚገባውን ፍርድ ለመስጠት ሲያኮበኩቡም፣ የበደለኛው ገረሜታና ድንጋጤ ግን ባልጠበቀው አቅጣጫ በመጣው ክስ እና በተወረወረበት ድንጋይ ይሆናል – ይሄኔ ነው፣ ‹እናንተ ደግሞ እነማን ናችሁ፤  ምን አጎደልኩባችሁና ነው የምትወግሩኝ?› የሚለው ጥያቄ የሚመጣው፡፡
Filed in: Amharic