>

 የትግራይ ክልል ም/ቤት መፈክር "ህገ-መንግስቱ ይከበር!!!" (ታየ ደንደዓ)

 የትግራይ ክልል ም/ቤት መፈክር
ህገ-መንግስቱ ይከበር!!!
ታየ ደንደዓ
ከሁለት ቀን በፊት ነበር። የሆነ መግለጫ ነገር አንብቤ እጅግ ተገረምኩ። ያወጣዉ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ነበር። መግለጫዉ ስለህገ-መንግስት ጥሰት በአንክሮ ያማርራል። ስለየትኛዉ ህገ-መንግስት እንደሚያወራ ግን እግዜር ያዉቃል። እኛ የሚናዉቀዉ ህገ-መንግስት መከበር ከጀመረ ገና ሦስት ወር ይሆናል።
ትንሽ ነገሮችን ዘርዘር ማድረግ ያስፈልጋል። በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 15 የተከበረዉ በህይወት የመኖር መብት ተጥሶ ዜጎች በየመንገዱ በአጋዚ ሲጨፈጨፉ ነበር። በአንቀፅ 18 የተከበረዉ ከስቃይ ነፃ የመሆን መብት ተገፎ ዜጎች በማዕከላዊ በእሳት እና በብረት ሲገረፉ ነበር። አካላቸዉ የተቆራረጠም አሉ። በአንቀፅ 25 ስር የተደነገገዉ የእኩልነት መብት ተጥሶ በኢትዮጵያ ሁሉም ነገር የወያኔ፣ በወያኔ እና ለወያኔ ሆኖ ነበር። በአንቀፅ 29 የተከበረዉ ሀሳብን በነፃ የመግለፅ መብት ተጥሶ የራስን ችግር መናገር በአሸባሪነት ሲያስከስስ ነበር። የህገ-መንግስቱ ምሰሶ የነበረዉ ራስን የማስተዳደር መብት ተገፎ 8 ክልሎች በሞግዚት ሲተዳደሩ ነበር። ይህን ሁሉ ሲፈፅም እና ሲያስፈፅም የነበረዉ ደግሞ ህወሀት ነዉ። የህወሀት ጄኔራሎች እና ኮሎኔሎች ህገ-መንግስቱን እንዲያከብሩ ሲጠየቁ “ቅደዱና…” ሲሉ ነበር። በዝህ ሦስት ወር ዉስጥ እነዝህ የህገ-መንግስት ጥሰቶች በመጠኑም ቢሆን ቆሟል። ታዲያ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ህገ-መንግስቱ በግላጭ ሲጣስ ተኝቶ ህገ-መንግስቱ መከበር ሲጀምር ለምን የጥሰት መግለጫ ያወጣል? አሁን በዝህ መልክ መቀለድ ምን ይጠቅማል? በእርግጥ ህወሀት ሁሉም ነገር የህወሀት በህወሀት ለህወሀት የሚል ያልተፃፈ ህገ-መንግስት እንዳለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ያዉቃል። አሁን ያ የአፓርታይድ ህግ መደርመስ ጀምሯል። ወደፊትም ይበልጥ ይደረመሳል። የዜጎችን ነፃነት እና እኩልነት የሚያረጋግጠዉ የተፃፈዉ ህገ-መንግስት ብቻ ይከበራል።
Filed in: Amharic