>

ኮሎኔል አጥናፉ አባተ! ባጎረሳቸው እጆች.. አሣዛኝ ዋጋ የተከፈለው…ገራም የቁርጥ ቀን ሰው!!!  (አሰፋ ሀይሉ)

ኮሎኔል አጥናፉ አባተ!

ባጎረሳቸው እጆች.. አሣዛኝ ዋጋ የተከፈለው… ገራም የቁርጥ ቀን ሰው!!! 
አሰፋ ሀይሉ
ይህ ሰው እነ ሌ/ኮ መንግሥቱ ኃይለማርያምን ከሐረር ወደ አዲስ አበባ ያስመጣቸው፣ ደርግን የመሠረተውን የበታች መኮንኖች ጉባዔ በሊቀመንበርነት የመራ፣ የአፄው ሥርዓት ከናካቴው ለመገርሰስ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተ፣ በታጠቅ ጦር ሠፈር የሕዝባዊ ሚሊሺያ ማሠልጠኛ ዋና አዛዥ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያን ቀደም ሲል በኤርትራ ጉዳይ ባነሱት ተቃውሞ በቤታቸው እንዳሉ በታንክ ተጨፍልቀው ከተገደሉት ከጄ/ል አማን ሚካኤል አንዶም ጋር፣ በመቀጠል ደግሞ በቤተመንግሥት ቢሮአቸው ባሉበት በመትረየስ ተኩስ እንዲገደሉ ከተደረጉት ከሊቀመንበሩ ከጄ/ል ተፈሪ ባንቲ ጋር ሀገሪቱን እንዲመሩ ከተመረጡ ሁለት የወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ምክትል ሊቃነመናብርት አንዱ በመሆን (ከሌ/ኮ መንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር) ሀገሪቱን በተከታታይ በምክትል ሊቀመንበርነት ያስተዳደረ በአንድ ወቅት ከፍተኛ የሀገር አደራን ተሸክሞ ያለፈ ሰው ነው፡፡
ይህ ሰው ኢምፔሪያሊስት ተብለው ከተፈረጁት ሀገሮች ከአሜሪካ እና ከምዕራብ አውሮፓ ሃገራት ጋር በርዕዮተ-ዓለም የተመሠረተ ፀባችንን ትተን ለብሔራዊ ጥቅማችን ስንል የትብብር ወዳጅነት መፍጠር አለብን ብሎ ሽንጡን ገትሮ በደርግ ጉባዔ ላይ የተከራከረ፣ የኤርትራ ጉዳይ ከወታደራዊ አማራጭ ጎን ለጎን ሠላማዊ አማራጮች አብሮ ማፈላለጉ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው በሚል አቋሙ የሚታወቅ፣ የሃገራችንን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ልንነድፍ የሚገባን ‹‹የሦሻሊስት ኢኮኖሚ›› በሚል የርዕዮተ ዓለም ደጋፊነትና አቀንቃኝነት ሣይሆን… ሃገራችንና ሕዝባችን የሚገኙበትን ነባራዊ ሁኔታ፣ ያለፍንበትን ታሪካዊ እውነታ፣ እና ከዓለም ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አዋህደን መሆን ይገባዋል፣ በኢትዮጵያ ልናሰፍን የሚገባን የኢኮኖሚ ፖሊሲ.. አንዳንድ መሠረታዊ ነገሮችን መንግሥት የሚቆጣጠርበትና የሚመራበት.. ሌሎችን ደግሞ ለግለሰቦችና ለባለሃብቶች የሚለቅበት ቅይጥ የኢኮኖሚ ሥርዓት ነው በማለት በቃል ብቻ ሣይሆን ጥናቱንና አቋሙን በጽሑፍ በዝርዝር ገልጾ ለደርግ ጉባዔ ለክርክር ያቀረበ አስገራሚ ምሁራዊነትን የተላበሰ ሰው ነው፡፡
ይህ ሰው ከኢህአፓ እና ከሌሎች ደርግን የሚቃወሙ የታጠቁም ሆነ ያልታጠቁ ኃይሎችና አብዮታዊ ፓርቲዎች ጋር.. እነሱም ሆኑ እኛ ሁላችንም የዚህች ሃገር ዜጎች እስከሆንን ድረስ.. ማናችንም በብቸኝነት ባለቤትነት የምንይዘውና የምናስፈጽመው የበላይና የበታች ሃሳብ ሊኖር አይገባውም… የሁላችንም ሃሳብ በነፃ ተንሸራሽሮ መታየት አለበት… እነ ኢህአፓም ሆኑ ሌሎች እናምንበታለን የሚሉትን አጀንዳና ሃሳብ ያምጡና.. በጋራ ተወያይተን.. በጋራ የሚያግባባንንና ለሃገራችን የሚበጃትን መንገድ ቀይሰን.. ልዩነቶቻችን ሳያጫርሱን በጋራ በሚያግባቡን ጉዳዮች… ደጋፊዎቻችንን አሠልፈን ለሃገር ዕድገት በጋራ ልንሠራ.. በጋራ ልንቆም ይገባናል እንጂ… እንደ ውጪ ጠላት ተያይተን… ልንዋጋቸው እና እርስ በእርስ ልንጨራረስ አይገባንም… ዞሮ ዞሮ የሚያልቀው የገበሬው የጭቁኑ ልጅ ነውና.. ብሎ… እጅግ በሚያስገርም ድፍረት… የደርግን የግራ አክራሪ ጉባዔተኞች… ሽንጡን ገትሮ የተከራከረ ልበ-ሙሉና ለወገን የሚያስብ ቅን አሳቢ አዕምሮ ከውስጡ ያልጠፋበት ገራም ኢትዮጵያዊ ነው፡፡
ይህ ሰው…. እና በተለይም በእነዚህ የመጨረሻዎቹ ሁለቱ አቋሞቹ የተነሣ… አብዮቱን የሚጻረሩና የሚሸረሽሩ በሚል በደርጉ ጉባዔ ፊት 12 ክሶች፣ እና ከአድኃሪያን ጎራ ጋር አጋርነትን በማሳየትና አብዮቱን ከሚጠሉ የውጪ ቅጥረኞች ጋር በመገናኘት በሚሉ 5 ክሶች… በአጠቃላይ 17 ክሶች ተነብበውበት (አብዮቱን ለባዕዳንና ለፀረ-ሕዝብ ድርጅቶች አሣልፎ የሰጠ፣ ወላዋይ አድኃሪ መስመርን የሚሰብክ፣ በጭቁኑ የኢትዮጵያ ሕዝብና ባቀጣጠለው አብዮት ላይ ዕምነት የሌለው፣ ለጭቁኑ ሕዝብና ለበታች መኮንኖች ትምክህትን የሚያሣይ፣ የደርግን ምስጢር ለሲ አይ ኤ አሣልፎ የሰጠ፣ አብዮቱን የሚቀለብስ የቅስቀሳ ንግግር በማድረግ፣ ወዘተ ወዘተ በሚል..) በቀድሞ ባልደረባውና ራሱ ወደ አዲስ አበባ ባስመጣው፣ አብረውም ንጉሡንና ባለሥልጣኖቻቸውን ከሥልጣን አውርደው ሲረሽኑ በነበሩት በገዛ ጓደኛው በሌ/ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ተላልፎ ተሰጥቶ… በደርጉ አባላት ክሱ ተዘጋጅቶ፣ በደርጉ ጉባዔ ፊት ክሱ ተሰምቶ፣ በራሱ በደርጉ ጉባዔ በክሶቹ ጥፋተኛ ነው ተብሎ በድምፅ ተወስኖበት፣ በውሳኔውም መሠረት በፈጸመው ‹‹አብዮቱንና ሀገሩን የመክዳት ወንጀል›› በሚል በራሱ በደርግ የሞት ፍርድ የተፈረደበት፣ በመጨረሻም በራሱ በደርጉ ትዕዛዝ በፍርዱ መሠረት የሚወዳቸውን እንኳ የመሠናበት ዕድል ሣያገኝ… ወዲያውኑ የሞት ቅጣት እንዲፈጸምበት የተደረገ… አብዮቱን አዋልዶ፣ ከአብዮቱ ተወልዶ፣ በመጨረሻም በአብዮት የተሰለቀጠ… አብዮት የገዛ ልጆቿን በላች እየተባለ ታሪኩ ሲነገርለት የሚኖር አሳዛኝ የጭቁን መለዮ ለባሾች አብዮተኛ ነው፡፡
ይህ ሰው… በሆለታ ገነት የወታደራዊ አካዳሚ ሠልጥኖ ከተመረቀባት ወቅት አንስቶ.. በምድር ጦር እና በአየር ኃይል.. ይህችን ሀገር እና ይለፍላቸው ያላላቸውን የዚህችን ሀገር ብቃዮች… በምድር በሠማይ ሲያገለግልና ሲከላከልላት.. ብሎም ለህዝብ የጠቀመ መስሎት (ወይም መሆኑን አምኖ) ‹‹ጠላቶቿ›› ካላቸው ጋር ሲዋደቅላት ኖሮ… በመጨረሻ ለሀገሩና ለወገኑ ለዋለው ውለታ… የህይወት ዘመን ብድራቱን… አሣዛኝ የሞት ዋጋ ተከፍሎት… በምድር የሚወዳትን የልጅነት ባለቤቱን ወይዘሮ አስናቀች ከበደን… ከነስድስት ልጆቹ ያለቤሳቤስቲን ትቶ ያለፈ አስገራሚ ትራጀዲያዊ ፍፃሜን ያደረገ ይህችን ሀገር በጭንቅ ቀኗ አለሁልሽ ብሎ በልበሙሉነት የቆመ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው፡፡ የኮ/ል አጥናፉ አባተ… ልጆች 1ኛ) ሳምሶን አጥናፉ፣ 2ኛ) ቴዎድሮስ አጥናፉ፣ 3ኛ) ሱራፌል አጥናፉ፣ 4ኛ) ጌታሁን አጥናፉ፣ 5ኛ) ሰለሞን አጥናፉና 6ኛ) መክብብ አጥናፉ… ናቸው፡፡
ይህ ሰው… ባልተረጋጋ ሀገርና አብዮት ውስጥ፣ ወገን እርስ በርሱ የሽብር ጎራ ለይቶ በሚፋጅበት የአብዮት ወላፈን ውስጥ… ትክክል ነው ብሎ ባመነበት ጎራ… እና በብዙ ትግልና ውጣ ውረድ ውስጥ አልፎ…. ከፋችም ለማችም… የታገለለትንና የቆመላትን.. እና ግን ትሩፋቷ እንደጉም የበነነበትን ይህችን ምስኪን ሀገሩን ከጭቁኑ ሕዝብ እና ርህራሄ ከሌለው የአብዮት ማዕበል ጋር ትቶ… ራሱ ‹‹ሀ›› ብሎ ባቋቋመው የደርግ ጉባዔ… የርሸና ትዕዛዝ መሠረት በገዛ የሥራ ባልደረቦቹና ጓዶቹ ተበልቶ… በህዳር 3 ቀን 1970 ዓ.ም. በተወለደ በ47 ዓመቱ… የኢትዮጵያን ምድር.. በማይመለስበት የሞት መንገድ.. እስከወዲያኛው የተሰናበተ… የ66ቱ አብዮት ዋና ጠንሣሽ፣ ዋና ተዋናይና ግንባር-ቀደም መሪ… እና አሣዛኝ የሞት ባለተራ…ይህ ሰው… ክቡር ኮሎኔል አጥናፉ አባተ.. ከነቤተሰቦቹ እንዲህ ማስታወሻውን ለታሪክ ጥሎልን አለፈ፡፡
ሞት ለማንም አይቀርም፡፡ ሁሉም ሰው ‹‹አለ›› ከመባል ወደ ‹‹ነበር›› መሸጋገሩ አይቀርም፡፡ ‹‹ሀ›› ብሎ ከበቀለባት ምድር… ‹‹ፐ›› ብሎ የመጨረሻ ትንፋሹን ጨርሶ መመለሱም አይቀርም፡፡ ህይወት ያለው ሁሉ ሞት አብሮት አለ፡፡ ሞት ለማንም አይቀርም፡፡ ነገር ግን እንዲህ እንደ ኮ/ል አጥናፉ አባተ.. ላመነበት ሀገራዊ አቋም… በሞት መንጋጋ ውስጥ እንኳ ቢሆን… ለህይወት መሥዋዕትነት ጭምር… ደረቱን በግላጭ ሰጥቶ በመቆም… ልጆቹ ቀና ብለው የሚራመዱበትን አኩሪ ታሪክ ትቶ ማለፍ ግን.. በህይወት ዘመን ከምንመላለሰው መሐከል… ለጥቂቶች ብቻ የተሰጠ… ልዩ ፀጋ ነው፡፡ በመሆኑም ነው.. ከሰው ሁሉ መሐል ነጥለን… በሞት ከእኛ በአካል ቢለዩም…  ከታሪካችን የማትለይ ስማቸውን ግን… ስለሠሯት በጎ ነገር ስንል.. እንዲህ ደግመን የምናነሳቸው፣ የምናወሳቸው፡፡
አምላክ ለሀገራቸው ሲሉ… ለወገናቸው ሲሉ… በሞት ሸለቆ ውስጥ እንኳን ሆነው.. የታያቸውን የተስፋ ጭላንጭል ለሕዝባቸው አመላክተው… እነርሱ ግን አስከፊ ሞትን የሞቱትን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ሁሉ… ለሥጋቸው ዕረፍትን፣ ለነፍሳቸው ሠላምን፣ ስለበጎ ነገራቸውም መወሳትን አይንፈጋቸው፡፡ አምላክ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ሁሉ አብዝቶ ይባርክ፡፡ እምዬ ኢትዮጵያ – በልጆቿ መተሳሰብ፣ በወገኖቿ መተዛዘን፣ በሕዝቦቿ መፋቀር፣ በትውልዶቿ ታላቅ ራዕይ – በጋራ በልጽጋ፣ አብባ፣ ደምቃ፣ ለምልማ… በደስታ፣ በሠላም፣ በትፍስህት – ለዘለዓለም ትኑር፡፡
ፎቶግራፉ (እጅግ ከከበረ ምስጋና ጋር)፡
‹‹ኮ/ል አጥናፉና ባለቤታቸው ወይዘሮ አስናቀች ከበደ ከልጆቻቸው ሳምሶን፣ ቴዎድሮስ፣ ሱራፌል፣ ጌታሁን፣ ሰለሞንና መክብብ አጥናፉ ጋር – Bob Rob saved to Ethiopia››
Filed in: Amharic