>

ስለፌዴሬሽን ወይም ኮንፌዴሬሽን ማውራቱ ከፈረሱ ጋሪውን ማስቀደም እንዳይሆን?!? (ፋሲል የኔአለም)

ስለፌዴሬሽን ወይም ኮንፌዴሬሽን ማውራቱ ከፈረሱ ጋሪውን ማስቀደም እንዳይሆን?!? 

 ፋሲል የኔአለም

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በመካከላቸው የነበረውን ጥላቻ በፍቅር አፍርሰው አዲስ ግንኙነት ለመጀመር መወሰናቸው ታሪካዊ ነው። ከኤርትራ ጋር የተጀመረው የፍቅር ግንኙነት በሰበብ አስባቡ እንዳይበጠስ ጠንካራ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋል። ግንኙነቱ የአውሮፓ ህብረት እንደተጓዘበት ከማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ( social and economic integration ) ቢጀመር ጥሩ ነው እላለሁ። የፖለቲካ እና የጸጥታ ትስስሮች በሁለተኛ ደረጃ የሚመጡ ናቸው። በቅድሚያ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በባህል ልውውጥ፣ በሙዚቃና በስፖርት ውድድሮች ማሳደግ፣  ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቱን ደግሞ የአሰብ ወደብን በጋራ ከማልማትና ከመጠቀም ጀምሮ አንድ አይነት የቀረጥ ስርዓትና አንድ የጋራ ገበያ በማቋቋም እንዲሁም የገንዘብ ልውውጡን ቢያንስ ለሁለት አመት በዶላር ደረጃ አድርጎ በሂደት ሁለቱም አገራት አንድ የመገባበያ ገንዘብ እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል።  በድንበር አካባቢ የመንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎችም በፍጥነት በጋራ መጀመር አለባቸው።
 የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ እየጠነከረ ሲሄድ፣ አለማቀፍ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም የሚያስችሉ የጋራ የጸጥታ ተቋማትን በጋራ ማቋቋም፣ ተመሳሳይ የውጭና የጸጥታ ፖሊሲዎችን መቅረጽ፤ ከእነዚህ ልምዶች ትምህርት በመውሰድና በህዝቡና በመንግስት መካከል ያለው መተማመን ከፍ ሲል ደግሞ፣   ሁለቱ አገራት ወደ ፖለቲካ ጥምረት የሚወስዳቸውን መንገድ በጋራ ሊቀይሱ ይችላሉ። ይህ የ10 ወይም የ20 ወይም የ50 አመታት ፕሮጀክት ሊሆን ይችላል። የፈጀውን ጊዜ ይፍጅ ግንኙነቱ በዚህ መንገድ መቀጠል እንዳለበት አምናለሁ። አሁን ስለፌዴሬሽን ወይም ኮንፌዴሬሽን ብናወራ ከፈረሱ ጋሪውን ማስቀደም ይሆናል።
የፖለቲካ ጥምረት ( political integration) ለመመስረት  ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት እጅግ አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ ራሱዋን ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ከለወጠች፣ ኤርትራም ተመሳሳይ ስርዓት ከመመስረት አታመልጥም።  ዲሞክራሲ የጉንፋን አይነት ባህሪ አለው። በዲሞክራሲ ጉንፋን የተጠቃ አገር ለጎረቤቱ ማስተላለፉ የግድ ነው። በአለም ላይ ተሳክቶላቸው ጥምረት ያደረጉ አገሮች ዲሞክራሲን የገነቡት  ናቸው። እናም ኢትዮጵያ በፍጥነት ዲሞክራሲን ገንብታ በዙሪያዋ ያሉ አገራትን እያጣመረች መጓዝ አለባት።  ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ጸሃይ ናት፤ ጸሃይ ብትከስም በዙሪያዋ ያሉት ፕላኔቶች እንደሚከስሙት ሁሉ፣  ኢትዮጵያ ትርምስ ውስጥ ብትገባ ጎረቤት አገራት ሁሉ ከመተራመስ አያመልጡም። ስለዚህ ኢትዮጵያ ጸሃይነቷን አውቃ በፍጥነት ወደ ዲሞክራሲ ሽግግር በመግባት ለአካባቢው አገራት ሁሉ ብርሃኗን በሰፊው መለገስ መጀመር አለባት።  በነገራችን ላይ የፍቅር ሃዋርያው ዶ/ር አብይ አህመድ እስካሁን በሰሩት ስራ ብቻ የ2019 የኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆን ይችላሉ። በዚህ በኩል ኢትዮጵያውያን ዘመቻ መጀመር አለብን ።
Filed in: Amharic