>
5:13 pm - Tuesday April 20, 1441

የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ነገር (አቻምየለህ ታምሩ)

የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ነገር

አቻምየለህ ታምሩ

የ«ያ ትውልድ» ግብታዊ የፖለቲካ ንቅሳቄ በርካታ አቋም የሌላቸውን ምሁራንና የፖለቲካ ተዋናዮች ፈጥሯል። ከነዚህ አቋምና integrity የሌላቸው የ ያ ትውልድ የፖለቲካ ንቅናቄ ካፈራቸው ሰዎች መካከል ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ቀዳሚው ናቸው። ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በተለያየ ጊዜ የሚጣረሱ አቋሞችን የሚሰጡና የሚጋጩ ምስክርነቶችን የሚናገሩ ሰው ናቸው።

ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ እ.ኤ.አ. በ2015 ዓ.ም. አሜሪካን አገር ከርመው ወደ አገር ቤት ከመመለሳቸው በፊት ባቀረቡት «የጥናት ወረቀት» በወያኔ ሕገ መንግስት እንደሚኮሩና ሕገ መንግስቱ ሲዘጋጅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደተወከለ ተናግረው ነበር።

ከዚያ ቀደም ብሎ ግን አንድነት ለፍትሕና ለዲሞክራሲ ፓርቲን ሲቀላቀሉ የወያኔ ሕገ መንግሥት አርቃቂ ጉባኤ በነበሩበት ወቅት በሕገ መንግሥቱ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይወያይበት እንደተወያየበት አድርገው ሕገ መንግሥቱ ሲጸድቅ በመናገራቸው መጸጸታቸውን ገልጸው «ከወያኔ ጋር ሳለሁ ላጠፋሁት ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ ያድርግልኝ» ብለው ጠይቀው ነበር። ዶክተር ነጋሶ ይህንን አንድነት ለፍትሕና ለዲሞክራሲ ፓርቲን ሲቀላቀሉ ይቅርታ የጠየቁበትን ንግግር ወደኋላ ብለው NED የሚባለው የአሜሪካኖች ተቋም እ.ኤ.አ. በ2015 ዓ.ም.ባዘጋጀላቸው ፕሮግራም ላይ ወረቀታቸውን ሲያቀርቡ ግን በሕገ መንግሥቱ እንደሚኮሩና በረቂቁ ዝግጅት ላይም ሁሉም [ቡድኖች] እንደተሳተፉ ተናገሩና አንድነትን ሲቀላቀሉ የጠየቁትን ይቅርታ አፈረሱ።

ከሁለት አመት በፊት በMARCH 11, 2016 ደግሞ ለአዲስ ስታንዳርድ በሰጡት ቃለ ምልልስ እ.ኤ.አ. በ2015 ዓ.ም. አሜሪካን አገር NED ባዘጋጀላቸው ፕሮግራም ላይ የተናገሩትን ተቃርነው «Do you think this procedure [ of drafting the constitution] was properly communicated? Do you think the majority of the people of Ethiopia knew what was happening? If so what was the response?» ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ «That is one of the major points where, looking back in retrospect, I criticize myself. We didn’t think properly. We knew that there was no proper atmosphere where different parties could organize meetings with their community members to discuss on the draft constitution before it became final. That was one of the biggest shortcomings in the process of the making of our constitution» ብለው በመመለስ ለሶስተኛ ጊዜ ራሳቸው ከተናገሩት ቃል ጋር ተላተሙ።

ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ አንድነት ለፍትሕና ለዲሞክራሲ ፓርቲን እንደተቀላቀሉ በፓርቲው ልሳን ፍኖተ -ነፃነት ጋዜጣ ማክሰኞ መስከረም 30 2004 ዓ.ም. በወጣው 2ኛ ዓመት ቅጽ.2 ቁ.11 ነጻ አስተያየት አምድ ላይ «አሰብን ለማስመለስ ለሚደረገው ትግል ንቁ ተሣትፎ እናድርግ» በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጽሑፍ፤

«እስካሁን የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት፣ ጥቅምና መብት ኢሕአዴግ ማስከበር አልቻለም። ኢሕአዴግ ይህን ለማድረግ ያለመቻል ብቻ ሳይሆን ከዚህ አኳያ ትላልቅ ስህተቶችንም ፈጽሟል። የመጀመሪያው ጥፋት የኤርትራ ጥያቄ የኮሎኒያሊዝም ጥያቄ ስለሆነ ኤርትራ ነፃነት ይገባታል የሚለውን አመለካከት መያዙ እንደነበር ይታወሳል። በዚህም ምክንያት የኮሎኒያሊዝምም ሆነ የሌላ ዓይነት የብሔር ጭቆና በኢትዮጵያ የሚፈታው አንድነትን፤ ፌደሬሽንን፣ ኮንፌደሬሽንን፣ ነፃ መንግሥት የሟቋቋም አማራጮች ቀርበውላቸው በሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ማስከበር መሆኑ ግልጽ ቢሆንም፤ የኤርትራ ሪፈረንደምና የሪፈረንደሙን ውጤት ተከትሎ ለኤርትራ እውቅና መሰጠቱ የሽግግር መንግሥትና በሕዝብ የተመረጠ ሕጋዊ መንግሥት ሳይቋቋም መፈጸሙ ሌላው ስህተት ነበር።

[ሌላኛው] የኢሕአዴግ ስህተት በባድመ ጦርነት ማገባደጃ ወቅት ኢትዮጵያ የተፈፀመባትን ወረራ ለመቀልበስ ስታደርግ በነበረው እንቅስቃሴ አሰብንና ምጽዋን ጨምሮ ሌሎች የኤርትራን የቀይ ባሕር ጠረፍ አካባቢዎች የመያዝ አቅም ነበራት። ኢትዮጵያ ይህን አቅም በመጠቀም አሰብን የማግኘት ድርድርና ስምምነት ማድረግ ትችል ነበር። ሆኖም ግን “አሰብ የአንድ የሉዓላዊ አገር ይዞታ ስለሆነች አሰብን ከያዛችሁ ጥሉ [ጠቡ] ከኤርትራ ጋር ሳይሆን ከኔ ጋር ነው” ብላ አሜሪካ አስጠንቅቃናለች በማለት የኢትዮጵያ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ኤርትራ ድንበር አልፎ አሰብን እንዳይዝ ታዘዘ። ይህ ትልቅ ስህተት ነበር። » ብለውናል።

ይህ የዶክተር ነጋሶ አስተያየት እንደ አንድ የወያኔ ዘመን ባለ ሥልጣን ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል ስትደረግ ሚናቸው ምን ነበር ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል። ዶክተር ነጋሶ ኤርትራ ከኢትዮጵያ በምትገነጠልበት ወቅት የወያኔ አገዛዝን ወክለው የኤርትራን «ሕዝበ ውሳኔ» ታዛቢ ነበሩ። «ሕዝበ ውሳኔ» የተባለውን ጨዋታም አሰብን ጨምሮ በኤርትራ ከተሞች ሁሉ እየተዘዋወሩ ታዝበዋል። በመጨረሻም አሰብን የሚጨምረውን የኤርትራን «ሕዝበ ውሳኔ» አስመልክተው አስመራ ላይ ለጋዜጠኞች አስተያየታቸውን ሰጥተው ነበር። በሜዲያ በተላለፈው በዚህ አስተያየታቸውም «የኤርትራ ሕዝብ ለመገንጠል ሕዝበ ውሳኔ አያስፈልገውም ነበር!» ሲሉ በድፍረት ተናግረዋል። የሚገርመው ነገር በወቅቱ የሻዕብያው አምበል ኢሳያስ አፈወርቂ እንኳን የኤርትራን እጣ ፈንታ ለመወሰን ሕዝበ ውሳኔ የግድ እንደሚያስፈልግ በስፋት ይናገር ነበር።

«የኤርትራ ሪፈረንደምና የሪፈረንደሙን ውጤት ተከትሎ ለኤርትራ እውቅና መስጠቱ የሽግግር መንግሥትና በሕዝብ የተመረጠ ሕጋዊ መንግሥት ሳይቋቋም መፈጸሙ ሌላው ስህተት ነበር» እያሉ ራሳቸውን ንጹህ አድርገው ወያኔን የሚከሱት ዶክተር ነጋሶ የኤርትራ ሕዝበ ውሳኔ በሚካሄድበት ወቅት «የኤርትራ ሕዝብ ለመገንጠል ሕዝበ ውሳኔ አያስፈልገውም ነበር» ያሉን ሰውዬ ናቸው።

ዶክተር ነጋሶ በዚህ አመት ደግሞ «ኢትዮጵያ የሚገባኝን ጥቅምና ክብር አልሰጠችኝም» ሲሉ ስሞታቸውን አሰምተው ነበር። ይህንን ስሞታ ያሰሙት ዶክተር ነጋሶ ከወያኔ ጋር በመስራቴ ኢትዮጵያን በድያለሁ ብለው ይቅርታ ከጠየቁ ከስምንት አመታት በኋላ ነው። ከወያኔ ጋር በመስራቴ ኢትዮጵያን በድያለሁ የሚል አንድ ሰው እንዴት ብሎ ነው የበደላትን አገር «የሚገባኝን ጥቅምና ክብር አልሰጠችኝም» ብሎ የሚከሰው? እንዴት ነው ነገሩ! ራሳቸው « ከወያኔ ጋር ሳለሁ ስለበደልኳት ይቅርታ ታድርግልኝ» ብለው ሲያበቁ ዛሬ እንዴት በድያታለሁ ባሉበት ምላሳቸው የበደሏትና ያጠፏትን አገር «የሚገባኝን ጥቅምና ክብር አልሰጠችኝም» ሲሉ ባንድ ራስ ሁለት ምላስ ይሆናሉ!

ዶክተር ነጋሶ በዛሬው እለት ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ለንባብ ከበቃው «ግዮን» ከሚባለው መጽሔት ጋር በሰንደቅ አላማ ዙሪያ ባደረጉት ቃለ ምልልስ «የባሕር ዳሩ ሰልፍ ሕገ መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ ይጻረራል» ሲሉ ተናግረዋል። በጣም የሚገርመው ነገር ይህ የዶክተር ነጋሶ የሰንደቅ አላማ አስተያየት ራሳቸው ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ባለፈው አመት በጥቅምት ወር ሁለተኛው ቅዳሜ [Saturday, 14 October 2017] አዲስ አድማስ ከሚባለው አገር ቤት የሚታተም ጋዜጣ ጋር «ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፡- በሰንደቅ ዓላማና በህገ መንግስቱ ዙሪያ» በሚል ካሳተመው ቃለ ምልልሳቸው ጋር ፊት ለፊት የሚጋጭ መሆኑ ነው። ዶክተር ነጋሶ በዚህ የአዲስ አድማስ ቃለ ምልልሳቸው «የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ለሕዝብ ውይይት አልቀረበም» ሲሉ ተናግረዋል።

ጤና ይስጥኝ ዶክተር ነጋሶ! ወያኔ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ሶስት ላይ ስለ ሰንደቅ አላማ ያሰፈረው ድንጋጌ ለሕዝብ ውይይት አልቀረበም ካሉን እንዴት ብሎ ነው ይህ ለሕዝብ ውይይት ያልቀረበ የፖለቲካ ድንጋጌ የሕገ መንግሥት አንቀጽ ሆኖ «የባሕር ዳሩ ሰልፍ ሕገ መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ ይጻረራል» ሊሉ የቻሉት? ዶክተር ነጋሶ ስለየትኛው ሕገ መንግሥት መጣስ ነው የሚያወሩት? «ያለ ሕዝብ ተሳትፎ የተረቀቀ ነው» ብለው ስለመሰከሩለት የወያኔ ፕሮግራምና ስለነበራቸውም ተሳትፎ «አጥፍቻለሁ፤ አገር በድያለሁ!» ብለው ይቅርታ እንዲደረግላቸው በአደባባይ ሕዝብን ስለጠየቁበት ሕገ መንግሥት ነውን? አንድ ራስ አራት ምላስ ሲሆን ሕሊና የሚባል ነገር የለምን? ነው ስንናገርና ስንጽፍ፤ እንደ ወረደ የሚቀበል እንጂ እያንዳንዷን ነገር በአንክሮ የሚከታተል፤ የሚመለከትና የምንገረውንም ሆነ የምንጽፈውን ነገር የሚፈትሽ፤ የትናንትናውን ንግግርና ጽሁፍ ከዛሬው ንግግርና ጽሁፍ ጋር የሚያመሳክር፤ መረጃና ማስረጃ አገላብጦ እውነቱን የሚያወጣና የሚሞግት ሰው አይኖርም በሚል ነው?

ሕግ የሕዝብ ማገልገያ መሳሪያ ነው። ሕግ የጥቂት ቡድኖች መገልገያ፤ የብዙሃኑ ሕዝብ ደግሞ መጨቆኛ መሳሪያ ሲሆን ወንጀል ይሆናል። ለጥቂቶች ፍላጎት ማስፈጸሚያ የሚዘጋጅ ማንኛምው ሕግ ተፈጻሚነት አይኖረውም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በአራቱም አቅጣጫ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ባካሄዳቸው ሰላማዊ ሰልፎች የወያኔን አምባሻና የሶቭየት ሕብረትን ኮከብ የማውለብለብ ፍላጎት እንደሌላው አድዋ፣ አሸንጌ፣ እንዳባጉና፣ ማይጨው፣ ወልወል፣ ካራማራ፣ባድመ፣ ወዘተ የተሰቀለውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከፍ አድርጎ በማውለብለብ አሳይቷል።

በድሬዳዋ፣ በአርባ ምንጭ፣ በሆሳዕና፣ በቡታጅራ፣ በአዲስ አበባ፣ በባሕር ዳር፣ በጎንደር፣ በደብረ ማርቆስ፣ በደሴ፣በደብረ ብርሃን፣ ወዘተ የተካሄዱ ትዕይንተ ሕዝቦች ግልጽ ያደረጉት ነገር ቢኖር የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ለማገድ ወያኔ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ላይ የጫነው አዋጅ አብዛኛውን ሕዝብ ለመጨቆን ያወጣው ሕገ ወጥ አዋጅ መሆኑን ነው። ያለሕዝብ ፍላጎት የአንድ የተወሰነ ቡድንን ፍላጎት ለማስጠበቅ በአብዛኛው ሕዝብ ላይ የተጣለው እግድ ደግሞ ወንጀል ነውና የኢትዮጵያ ሕዝብ የወያኔን ሕገ ወጥ የሰንደቅ አላማ አዋጅ የራሱን ሰንደቅ አላማ ይዞ በመውጣት መሻር ይችላል!

በአገራችን ሕግና እውነተኛ ዳኛ ቢኖር ኖሮ የአንድ ጠባብ ቡድን ፍላጎትን ለማስፈጸም በአብዛኛው ሕዝብ ላይ የተጫነውን ወንጀለኛ ሕግ ሰርዞ በወንጀለኛው ሕግ ጠባብ ፍላጎቱን ለማስፈጸም የሚታትረውን አገዛዝ ያግደውና ለፍርድም ያቀርበው ነበር። ሕግና ስርዓት በአገራችን ስለሌለ ግን ሕዝቡ የጥቂቶችን ፍላጎት በአብዛኛው ላይ ለመጫን ወያኔ ያወጣውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ያገደበትን አዋጅ ሕዝብ ሉዓላዊ መብቱን ተጠቅሞ በመሻር መብቱን ማስከበር ይችላል፤ ይህን ማድረግ ሕጋዊም ነው።

ዶክተር ነጋሶም ሆነ ወያኔዎች ግን ከፈለጉ በሶቭየት ሕብረት ኮከብ ምትክ ሰንደቅ አላማችን በሚሉት ምልክታቸው የሕወሓቱን ሊቀ መንበር የየመለስ ዜናዊን ምስል ተክተው ማውለብለብ ይችላሉ። በተለይ ወያኔዎቹ ቢያሻቸው የአጋዚያንን ምልክት የሰንደቅ አላማቸው አርማ አድርገው ሊደርቱበት ይቻላቸዋል። የፈለጋቸውን ማድረግ መብታቸው ነው። የነሱን ጠባብ ፍላጎት ለማስጠበቅ ያወጡትን የወንጀል አዋጅ ግን ሕግ አድርገው በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የማይፈልገውን የመጫን ሕጋዊም ሆነ ትጥቃዊ መብት የላቸውም።

Filed in: Amharic