>
5:13 pm - Tuesday April 20, 1965

የመብት ጥያቄ አልቀውና ተላልቀው ሳይሆን ኖረው ሲጠይቁት ነው ብልህነት!!!  (ደረጄ ደስታ) 

የመብት ጥያቄ አልቀውና ተላልቀው ሳይሆን ኖረው ሲጠይቁት ነው ብልህነት!!!
 ደረጄ ደስታ 
ምን እየተደረገ እንደሆነ በቅጡ ሳናውቅ ምን መደረግ እንዳለበት እየተወያየን ይሆን? ወይም ምን መደረግ እንዳለበት ሳናነሳ የሆነውን ብቻ መልሰን መላልሰን እናላዝናለን ልበል? በሆነውና እንዲሆን በሚገባው መካከል ያለውን ግንኙነት ተገናኝተንም አገናኝተንም አናየውም። ክፍተት አለ። ይህን ክፍተት የተከፈተ አፍ አይሞላውም። አፍ ተዘግቶ ጆሮ ተከፍቶ ሀሳብ ተብላልቶ ነው መፍትሔ የሚረገዘው እንጂ እንዲሁ ያሉትን ደግሞው ሲሉት ሲያንበለብሉት ቢውሉ ስልቻ ቀልቀሎ ነው።
ማን? መች? የትና እንዴት ሊመልሰው እንደሚችልና እንደሚገባው ሳያውቁ ጥያቄ ማንጋጋት ጀብድ ካልሆነ መልስ አያስገኝም። የመብት -የነጻነት- የፍትህ- የዳቦ- የተቋም- የባንዲራ- የድንበር- የልንገጠል ልተክል ጥያቄ በዝቷል። እውነት ነው ችግሩ አለቅጥ ስለበዛ ጥያቄም ጥንቡን ጥሏል። ከዛፍ ላይ እንደሚሸመጥጡት ፍሬና ቅጠል ጥያቄም የትም እየተነቀነጠሰ እዚህም እዚያም እየተነሰነሰ ነው። ይህ ይመለስ – ያ ይደርመስ! ማለት ብቻውን ምላሽ አያስገኝም።
እንኳን አንድ አብይ፣ አንድ አገር ህዝብ አዳራሽ ውስጥ ቢያጭቁት፣ ተግባብቶም ሆነ ገብቶት ሊመልሰው እማይችል እልፍና እልፍ ጥያቄዎች ሞልተዋል። እንደው አማረብኝ ተብሎ አንደበቴም ተከፍቷል እየተባለ ጥያቄ ሲያንደቀድቁ መዋል እንደወንዝ ጠራርጎ ይወስድ እንደ አውሎ ንፋስ ወጀብ ያወለጋግድ ካልሆነ፣ አገርና ነገር አያቀናም። የባንዲራ ጋጋታና፣ ስልት አልባው ጫጫታ፣ ያን አውርድ ይህን ስቀል እያሳባለ ከቀጠለ፣ ባንዲራውን ስቀለው ቀርቶ የተቃወመውን ሰው ስቀለው ማለትን ያመጣል። በዚያች አገር ምንም ነገር ከሰው መብለጥ የለበትም። ባንዲራ ለሰው ድንበርም ለሚኖርበት ነው። ደግሞም ቢታገሱት ሁሉም ይደርሳል ሁሉም ያልፋል። ግን አሁን እምናስቀድመው ምን ይሁን? የመብት ጥያቄ ጥሩ ነው። ግን አልቀውና ተላልቀው ሳይሆን ኖረው ሲጠይቁት ብልህነት ነው። ካለበዚያ ቢያውቁ አይገዱልንም ፣ ብናውቅ አንሞትም እያስባለ እውቀት አልባ ጩኸት ያስመስልብናል። ገና ለገና የመጠየቅ ነጻነት ተገኝቷል ወይም ሊገኝ ነው ተብሎ አላዋቂ እጅ እንደገባ ጠመንጃ ወደሰማይም ወድምድርም  አይተኮሰም። የምድሩስ መንግስት ይሁን፣ “ይህስ ከሱ ነው እንጂ ከኛ አይደለም” ያልነው የሰማዩ አምላክ ግን ምን ይለናል? አሁን ለውጡን አኔ አመጣሁት ብሎ ብቻውን እሚፎክር እሱ ማነው? ካልሰማችሁኝ እቀለብሰዋለሁ ብሎ ተንጠራርቶ መፎከርስ ተገቢ ነው? ተው እንጂ ወገኔ!
Filed in: Amharic