>

የትግራይ ህዘብ አማራጭ ህወሓት ወይም ባርነት ነው! (ስዩም ተሾመ)

የትግራይ ህዘብ አማራጭ ህወሓት ወይም ባርነት ነው!

ስዩም ተሾመ

በዚህ ፅሁፍ የቀድሞ የኢትዮጵያ መረጃ መረብ እና ደህንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል፣ ዶክተር ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይ ከድመፀ ወያነ ራድዮ ጋር ባደረጉትን ቃለ ምልልስ ዋቢ በማድረግ በህወሓትና የትግራይ ሕዝብ መካከል ያለውን ቁርኝት እንመለከታለን። በዚህ መሰረት የህወሓት የፖለቲካ አይዲዮሎጂ ምን ያህል ፀረ-ዴሞክራሲ እና ፀረ-ህዝብ እንደሆነ በዝርዝር እንዳስሳለን።

የቀድሞ የኢትዮጵያ መረጃ መረብ እና ደህንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል፣ ዶክተር ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይ

1) የትግራይ ሕዝብ እና የህወሓት አንድነት

የቀድሞው የኢትዮጵያ መረጃ መረብ እና ደህንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል፣ ዶክተር ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይ ከድመፀ ወያነ ራድዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዲህ ብለዋል፡-

“ህወሓት ማለት እንደሌላው ፓርቲ በሰላማዊ መንገድ እታገላለሁ ገለመሌ ብሎ ፕሮግራም ነድፎ የመጣ ፓርቲ አይደለም። በትግራይ ህዝብ ደምና መስዋት የተገነባ ድርጅት ነው። ህወሓት የትግራይ ህዝብ ነው። የትግራይ ህዝብ ማለት ህወሓት ማለት ነው። ሊወሰድ የሚገባው አንደኛው ግንዛቤ ይህ ነው። ህወሓትና የትግራይ ህዝብ ለያይቶ ማየት አይቻለም። …ስለዚህ ህወሓት የሚያጠፋው ጥፋት ቢኖር የራሱ የትግራይ ህዝብ ጥፋት ነው።

በእርግጥ ከላይ በተጠቀሰው ቃለ ምልልስ ሜጀር ጀነራል፣ ዶክተር ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይ የህወሓት አባል አለመሆናቸውን ገልፀዋል። ይሁን እንጂ፣ ዶክተር ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይ ትግራዋይ ናቸው። በመሆኑም ግለሰቡ የትግራይ ተወላጅ፣ የትግራይ ሕዝብ አካል ናቸው። እንደ እንደሳቸው አገላለፅ፣ “ህወሓት የትግራይ ህዝብ፣ የትግራይ ህዝብ ደግሞ ህወሓት” ስለሆነ፣ ዶክተር ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይ ህወሓት ናቸው።

በድጋሜ “ህወሓት የሚያጠፋው ጥፋት ቢኖር የራሱ የትግራይ ህዝብ ጥፋት” ስለሆነ ዶክተር ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይ በቡድን ሆነ በግል የፈፀሙት ጥፋት የትግራይ ሕዝብ ጥፋት ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ “ህወሓትና የትግራይ ህዝብን ለያይቶ ማየት ስለማይቻል” ከላይ የተጠቀሰዉ የዶክተር ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይ አስተያየት እንደ በአጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ፣ እንደ ፓርቲ ደግሞ የህወሓት የጋራ አቋምና አመለካከት ነው። ስለዚህ በህወሓት የመጣን ሽልማት ሆነ ቅጣት የትግራይ ሕዝብ መቀበል አለበት። ምክንያቱም እንደ ዶክተር ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይ አገላለፅ፣ ህወሓት ማለት የትግራይ ሕዝብ ስልጣኔ ነፀብራቅ ነው፡-

“ህወሓት ማለት የትግራይ ህዝብ በብዙ ሺህ የስልጣኔው ዘመናት ግስጋሴው በአንደኛው ዘመን በፈጠረው ፖለቲካዊ ፍልስፍና ንቃተ ህሊናው በፈጠረው መደራጀቱ የትግራይ ህዝብ የፈጠረው የስልጣኔው ነፀብራቅ ነው። ህወሓት ማለት የስልጣኔያችን ፖለቲካዊ ታሪካችን አንዱና ረጅሙ ክስተት ነው።”

2) ለህወሓት “አንድነት” ማለት ልዩነትን ማጥፋት ነው!

የህወሓት የፖለቲካ አይዲዮሎጂ ራሱን ከትግራይ ሕዝብ ጋር አንድና ተመሳሳይ በማድረግ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ተመልክተናል። በዚህ መልኩ ህዝብና ፓርቲን አንድ የማድረጉ መሰረታዊ ፋይዳ በማህብረሰቡ ውስጥ ምንም ዓይነት የተለየ ነገር እንዳይኖር ማድረግ ነው። በህወሓት የፖለቲካ አይዲዮሎጂ መሰረት ማንኛውም ዓይነት ልዩነት የችግር መንስዔ ነው። ስለዚህ ህወሓት ራሱን ከሕዝቡ ጋር አንድና ተመሳሳይ ከማድረግ አልፎ በፓርቲውም ሆነ ሕዝቡ ውስጥ ምንም ዓይነት ልዩነት እንዳይኖር አበክሮ ይሰራል። ምክንያቱም ልዩነትን ማስወገድ የችግሮች ሁሉ መፍትሄ ነው።

በህወሓት ውስጥ የተለየ ሃሳብና አመለካከት ያላቸው የድርጅቱ አመራሮችና አበላት መጨረሻቸው ሞት፥ ስደት ወይም እስራት ነው። በዚህ ረገድ እንደ ሙሴ፥ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፣ ስዬ አብርሃ፥ ገብሩ አስራት እና የመሳሰሉትን የድርጅቱን ነባር አመራሮች እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። ህወሓት በራሱ ቀርቶ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ውስጥ እንኳን የተለየ ነገር እንዲኖር አይሻም። በትግራይ ሕዝብ ውስጥ ምንም ዓይነት የባህል ሆነ የቋንቋ ልዩነት እንዲኖር አይፈቅድም። ሌላው ቀርቶ የትግሪኛ ቋንቋ አነጋገር ዘየ መለያየት በራያና ወልቃይት አከባቢ ለተነሳው የማንነት ጥያቄና ከዚያ ጋር ተያይዞ ለተፈጠረው የፖለቲካ ችግር መንስዔ ነው። ይህንን ሜጀር ጀነራል፣ ዶክተር ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይ እንደሚከተለው ይገልፁታል፡-

“አንድነታችን የሚከፋፍሉበት መንገድ የአካባቢነት የባህልና የትግሬኛ ቋንቋ አነጋገር ዘየ ልዩነትን የሚያጎሉ ስሜቱን በማጠናከር ነው። …በእርግጥ በደምብ ሳንሰራበት የቀረ ክፍተት በተለያዩ ቦታዎች ያሉ የንግግር ዘየ፥ ባህል ምናምን ጥናት አድርገን አንድ የሚያደርጋቸውን ስራዎች ሳይሰራ ነው የቆየው። በሁለቱም የትግራይ ጫፎች የወልቃይት ማንነት ጥያቄ እና የራያም ማንነት ጥያቄ እያነሱብን ያሉት ቀደም ብየ እንደገለፅኩት የበለጠ የመከበብ የመቀርቀር ስሜት እንዲሰማን ነው።”

3) ህወሓት የጥሩነትና መጥፎነት መለያ ነው!

ከላይ በተገለፀው መሰረት ህወሓት እና የትግራይ ሕዝብ አንድና ተመሳሳይ ከመሆናቸው በተጨማሪ ከህወሓት የተለየ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ማራመድ በትግራይ ሕዝብ ላይ ክህደት እንደመፈፀም ይቆጠራል። ለህወሓት ጥሩ የሰራ ለትግራይ ሕዝብ ጥሩ እንደሰራ ይቆጠራል። ህወሓት የማይፈልገውን መጥፎ ነገር የሰራ ደግሞ በትግራይ ሕዝብ ላይ መጥፎ እንደሰራ ይቆጠራል። “ህወሓት የትግራይ ህዝብ ነው። የትግራይ ህዝብ ማለት ደግሞ ህወሓት” ስለሆነ ህወሓትን መቃወም ፀረ-ሕዝብ መሆን ነው። ይህን አስመልክቶ ዶክተር ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይ የሚከተለውን ብለዋል፡-

“…ህወሓት የትግራይ ህዝብ መሆኑን የምታውቀው 750, 000 አባሎት አሉት። እያንዳንዱ አባል አምስት ቤተሰብ ቢኖረው ትግራይ ነው ማለት ነው። ስለዚህ ህወሓትን ስትነቅፍ ራስህን ነቀፍክ ማለት ነው። …ህወሓት ጥሩ ነገር ቢኖረው የራሱ የትግራይ ህዝብ ጥሩነት ነው የሚሆነው። ስለዚህ የህወሓት ጉዳይ የራሱ የትግራይ ህዝብ ጉዳይ ነው። በህወሓት ጥፋትም ጥሩነትም የትግራይ ህዝብ ነው ጉዳይ ነው። ይህ የትግራይ ህዝብ ጉዳይ የራሱ የትግራይ ህዝብ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ የተለያዩ ናቸው እያለ የሚዘርባርቅ ብልጥ ሃይል “እረፍ” ሊባል ይገባል።”

4) ህወሓት እና ዴሞክራሲ
ህወሓት ከተመሰረተበት ዕለት አንስቶ የትግራይ ሕዝብ እና ህወሓት አንድ መሆናቸውን፣ አንድነት ማለት ልዩነትን ማጥፋት እንደሆነና ህወሓትን መደገፍ ጥሩነት፣ መቃወም ደግሞ መጥፎነት እንደሆነ ሲያስተምርና ሲተገብር ኖሯል። በዚህ መሰረት ለእያንዳንዱ የህወሓት አባል፤ አንደኛ፡- የትግራይ ሕዝብ ማለት ህወሓት ነው፣ ሁለተኛ፡- አንድነት ማለት ከድርጅቱ የተለየ አቋምና አመለካከት አለማራመድ ነው፣ ሦስተኛ፡- ህወሓትን መደገፍ ጥሩ፣ መቃወም ደግሞ መጥፎነት ነው። እንደ ዶክተር ተክለ ብርሃን ወልደ አረጋይ አገላለፅ፣ 750, 000 የሚሆኑት የህወሓት አባላት በስራቸው የሚያስተዳድሩ አምስት ቤተሰብ ቢኖራቸው የትግራይ ሕዝብ በሙሉ ህወሓት ነው። ስለዚህ ላለፉት አርባ አመታት አብዛኛው የትግራይ ተወላጅ፤ ህወሓት ማለት የትግራይ ሕዝብ እንደሆነ፣ ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ፀረ-አንድነት፣ ፀረ-ሕዝብ እና መጥፎ ምግባር እንደሆነ ከሌሎች እየሰማና በራሱም እየተናገረ ያደገ ነው።

በእንዲህ ያለ ማህበራዊ ስነ-ልቦና እና አስተምህሮት ውስጥ ተወልዶ፥ አድጎና ጎልምሶ ዛሬ ላይ የደረሰ ግለሰብ፤ እንዴት ሆኖ ህወሓትን መቃወም፥ መተቸት፥ መንቀፍ ይችላል? በምን አግባብ ራሱን ከህወሓት መነጠል ይችላል? እንዴትስ ከህወሓት ተነጥሎ መልካም ነገር መስራት ይቻለዋል? በዚህ ሁኔታ መቼና እንዴት የትግራይ ሕዝብን ከህወሓት መነጠል ይቻላል? ህወሓትን ከትግራይ ህዝብ ትከሻ ላይ መነጠል ካልተቻለ እንዴት ሆኖ የሕዝቡን ፍላጎትና ምርጫ ማስከበር ይችላል? ፓርቲና ሕዝብን መለያየት ካልተቻለ በምን አግባብ የህወሓት አባላትን ከትግራይ ተወላጆች መለየት ይቻላል? ይህ ሁሉ የሆነው የህወሓት ዓላማና ግብ ከትግራይ ህዝብን ጥቅም ከማረጋገጥ ይልቅ መጠቀሚያ ማድረግ ስለሆነ ነው፡፡ የህወሓት የፖለቲካ አይዲዮሎጂ ከስሩ እስካልተነቀለ ድረስ ትግራይ ውስጥ ዴሞክራሲ ይኖራል ብሎ ማሰብ የቢሆን አለም ቅዠት ነው። ስለዚህ የትግራይ ህዘብ ያለው አማራጭ ህወሓት ወይም ባርነት ነው!!

Seyoum Teshome

Filed in: Amharic